1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮንራድ አደናወር

ማክሰኞ፣ ሰኔ 27 2009

የኢትዮጵያው ንጉስ አጼ ኃይለ ሥላሴ ከአደናወር ጋር የቅርብ ግኝኙት ከነበራቸው መሪዎች አንዱ ነበሩ። ምዕራብ ጀርመን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተገለለችበት ወቅት የኢትዮጵያው የመጨረሻ ንጉሥ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጀርመንን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የጎበኙ የመጀመሪያው የውጭ መሪ ነበሩ። በአደናወር መቃብርም ላይ ተገኝተው የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።

https://p.dw.com/p/2fvrt
Bonn Palais Schaumburg Bundeskanzler Konrad Adenauer
ምስል picture-alliance/akg-images

የኮንራድ አደናወር የፖለቲካ ሕይወት

የመጀመሪያው የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ ወይም የምዕራብ ጀርመን መራኄ መንግሥት ኮንራድ አደናውር ከሞቱ ባለፈው ሚያዚያ 50 ዓመት አለፈ። መኖሪያ ቤታቸው አጠገብ የሚገኘው የኮናርድ አደናወር ቤት የጥናት ተቋም ቤተ መዘክር የሞቱበትን 50ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ቋሚ ዐውደ ርዕይ እያሳየ ነው። በአምስት መንግሥታት ኖረው ሰርተው አልፈዋል። በጀርመን ዘውዳዊ አገዛዝ ፣ ከዚያ በተከተለው የጀርመን  የመጀመሪያው ምክር ቤታዊ ዴሞክራሲ ስርዓት በቫይመር ሪፐብሊክ፣  በናዚ ዘመነ መንግሥት፣ በድል አድራጊዎቹ የተባበሩት ኃይሎች አስተዳደር እንዲሁም በዘመናዊቷ የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ የመጀመሪያው የፌደራል ጀርመን ሪፐብሊክ መራሄ መንግሥት ኮንራድ አደናወር። 
«የተወለድኩት ጥር 1876 ነው። አንድ ጥያቄ ላቀርብላችሁ እፈልጋለሁ። ምናልባት በአሁኑ ጊዜ እንደኔ በእድሜ የገፋ የጀርመን ምክር ቤት አባል አለን? ብቸኛው እንደሆንኩ ማረጋገጥ እችላለሁ።»
ኮናርድ አደናወር በጎርጎሮሳዊው 1965 የጀርመን ፓርላማ ሥራ ሲጀምር ያሰሙት ንግግር ነበር። አደናወር ይህን ያሉት በ89 ዓመታቸው ነበር፤ ከፌደራል ጀርመን መሪነት ከለቀቁ ከሁለት ዓመት በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት ከመለየታቸው ከሁለት ዓመት አስቀድሞ ነበር ይህን የተናገሩት። ከዛሬ 50 ዓመት በፊት በሞት የተለዩት የመጀመሪያው የምዕራብ ጀርመን መራሄ መንግሥት ኮንራድ አደናወር  ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት በኋላ ለጀርመን ህዝብ ነፃነት ብልፅግና እና ማህበራዊ ዋስትና  ባደረጉት አስተዋጽኦ ክብር  እና አድናቆት የሚቸራቸው መሪ ናቸው። ባለፈው ሳምንት የዶቼቬለ የአፍሪቃ ክፍል የጋዜጠኞች ቡድን የአደናወርን መኖሪያ ቤት እና አጠገቡ የተሰራውን በስማቸው የተቋቋመውን የጥናት ተቋም ቤተ መዘክርን ጎብኝቶ ነበር። ቋሚው ቤተ መዘክር እና የአደናወር መኖሪያ የሚገኘው  በቀድሞው የፌደራል ጀርመን ዋና ከተማ ቦን አጠገብ በምትገኘው በባድሆኔፍ ከተማ  ባለችው የሮንዶርፍ ክፍለ ከተማ ነው። ቤተ መዘክሩ የአደናወርን ፖለቲካዊ እና ቤተሰባዊ ህይወት የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለጀርመን ህዝብ ያበረከቷቸውን  አስተዋጽኦዎች እንዲሁም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ የተደረገላቸውን ስንብት የሚያሳዩ ፎቶግራፎች እና ቪድዮዎችን አካቷል። በዚህ ዝግጅት መግቢያ ላይ የቀረበው አደናወር ከዛሬ 52 ዓመት በፊት ያደረጉት ንግግር ለቤተ መዘክሩ ጎብኚዎች ከሚታዩት ቪድዮዎች የተወሰደ ነበር ። ከርሳቸው እና ከቤተሰቦቻቸው መገልገያዎች እና ማስታወሻዎችም የተወሰኑት ለዕይታ ቀርበዋል። ባለፈው ረቡዕ በስፍራው ለተገኘው የዶቼቬለ የጋዜጠኞች ቡድን ቤተ መዘክሩን ያስጎበኙት እና ገለፃም የሰጡት  የተቋሙ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዶክተር ዩርገን ፔተር ሽሚት ናቸው። ዶክተር ሽሚት ከታላቁ የጀርመን መሪ አደናወር ስኬቶች አብይ የሚባሉትን ገልጸውልናል። 
«ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፣በተለይም ከአምባገነኖቹ የጀርመን ብሔራዊ ሶሻሊስቶች ናዚዎች ሽንፈት በኋላ በጀርመን ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው መሪ ነበሩ። ከጦርነቱ በኋላ ጀርመን ፈራርሳ ህዝቡ ግራ በተጋባበት ወቅት በዚህ መደናገር ውስጥ አዲስ ዴሞክራሲ አዲስ አገር፣ ህዝቡ እስካሁንም የሚኖርበትን ዴሞክራሲ መመስረታቸው ከስኬታቸው መካከል አንዱ እና ዋነኛው  ነው። በሀገሪቱ በዴሞክራሲ ላይ ከተቃጡ በርካታ ጥቃቶች በኋላ  ለ70 ዓመታት ያህል የዘለቀውን ዴሞክራሲ ማስፈን መቻላቸው  ከአደናወር ስኬቶች ውስጥ ትልቁን ቦታ ይይዛል።»
በምዕራብ ጀርመንዋ በኮሎኝ ከተማ  የዛሬ 141 ዓመት የተወለዱት አደናወር ከእድሜያቸው አብዛኛውን ያሰለፉት በሥራም ሆነ በኑሮ በዚህችው ከተማ ነው። የሕግ ትምሕርት ያጠኑት አደናወር ለ16 ዓመታት የኮሎኝ ከንቲባ ነበሩ። በጎርጎሮሳዊው 1933 ናዚዎች ሥልጣን ሲይዙ ከኮሎኝ ከንቲባነታቸው ተነሱ። ከኮሎኝ ከንቲባነት ሲባረሩ ችግር ውስጥ ወደቁ። ችግሩ ያሸማቀቃቸው የቀደሞው ከንቲባ ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ለአንድ ዓመት ያህል ማርያ ላህ የተባለ ገዳም ገብተው ነበር። ከዚያ በኋላ አደናወር ከሰው ባገኙት ገንዘብ በራይን ወንዝ አቅራቢያ በምትገኘው ሮንዶርፍ በተባለችው ከተማ ከፍ ባለ ስፍራ ላይ የሚገኘውን አሁን ለጎብኝዎች ክፍት የሆነው ባለ አንድ ፎቅ መኖሪያ ቤታቸውን ሰርተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መኖር ጀመሩ። ናዚ ጀርመን በተባበሩት ኃይሎች ድል ከተደረገ በኋላ አደናወር በ69 ዓመታቸው የኮሎኝ ከንቲባነታቸውን ሥልጣን መልሰው ተረከቡ በዚሁ ሃላፊነታቸው ወቅት አካባቢውን ይቆጣጠሩ የነበሩት እንግሊዞችን በመተቸታቸው እንደገና ከሃላፊነታቸው ተነሱ። ከዚህ በኋላ አደናወር ትኩረታቸውን እንደተመሰረተ ወደተቀላቀሉት የክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት ፓርቲ አድርገው መንቀሳቀስ ጀመሩ።
«ተፈላጊነታቸው በኮሎኝ ብቻ አልነበረም።ጎን ለጎን በርካታ ሥራዎችንም ያከናውኑ ነበር። በወቅቱ በዋና ከተማይቱ በርሊን ንቁ ተሳትፎ ነበራቸው የኮሎኝ ከንቲባ በነበሩበት ወቅት የፖለቲካ አካሄድ ተማሩ።  ብዙሀኑን እንዴት ከርሳቸው ጎን ማሰለፍ እንደሚቻል ስብሰባዎችንም እንዴት መምራት እንዳለባቸው ተምረዋል ።»
በ1946 የፓርቲው የራይንላንድ ሊመንበር ሆኑ። ብዙም ሳይቆዩ የምዕራብ ጀርመኑ የራይንላንድ ቬስትፋለን ፌደራዊ ክፍለ ሀገር የየCDU ሊቀመንበርነት ያዙ። በ1948 የፌደራል ጀርመን ሪፐብሊክን  መሠረታዊ ሕግ ላጸደቀው ፓርላማ ምክር ቤት አባልነት ተመረጡ። በዚህ እና በቀድሞው ስራቸው ዝናቸው እየናኘ የሄደው አደናወር በመስከረም 1949 ዓ.ም. በ73 ዓመታቸው የፊደራል ጀርመን የመጀመሪያው መራሄ መንግሥት ሆነው ተመረጡ። አደናወር በሥልጣን ዘመናቸው ካከናወኗቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል ጀርመን የምዕራቡ ዓለም አጋር እንድትሆን ያደረጉት ጥረት አንዱ ነው ይላሉ ሽሚት።
«ከአደናወር ውሳኔ መካከል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ምዕራብ ጀርመንን ማለትም የፌደራል ጀርመን ሪፑብሊክ የምዕራባውያን ሀገራት አጋር ማድረጋቸው ነበር። ጀርመን የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅ ኔቶ አባል እንድትሆን አድርገዋል። እስካሁን የድርጅቱ አባል ናት። ከመጀመሪያው አውሮጳን አንድ የማድረጉ ጥረት አንስቶ ምዕራብ ጀርመን የሂደቱ አካል እንድትሆን በማድረጋቸው ጀርመን እስከዛሬ ድረስም በአውሮጳ አንድነት የመሪነቱን ቦታ እንደያዘች ነው።ይህ ደግሞ በጀርመን የውጭ ፖሊሲ የተካሄደ አብዮት ነው ማለት ይቻላል።»
አደናወር በሚመሯት የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ ለህብረተሰብ ከፍተኛ ጥቅም ያስገኘ የገበያ ኤኮኖሚ አበበ። የጀርመናውያን ኑሮ ተሻሻለ። የሐገሪቱም ብሔራዊ ሉዓላዊነት ተረጋገጠ። መንግሥታቸው የአዲስ ዴሞክራሲ ግንባታን በተሳካ መንገድ አከናወነ።  በውጭ ፖሊሲ ረገድም ከምዕራቡ ዓለም ጋር የተፈጠረው የቅርብ ግንኙነት፣ ከፈረንሳይ ጋር የተፈጸመው እርቅ እና አውሮጳን አንድ የማድረግ ጥረት  በርሳቸው ዘመን ነው የተከናወነው። በ1958 ነበር አደናወር እና የያኔው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ሻርል ደጎል ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት። ሁለቱን ጀርመኖች የሚለያየው ግንብ የተሰራው በርሳቸው የሥልጣን ዘመን በ1961ዓ.ም. ነበር። በዚሁ ዓመት ዳግም የተመረጡት አደናወር ከሁለት ዓመት በኋላ ከሥልጣን ወረዱ። በ1966 ደግሞ ከፓርቲያቸው ከCDU ሊቀመንበርነት ተነሱ። በጎርጎሮሳውያኑ ሚያዚያ 1967 በ91 ዓመታቸው መኖሪያ ቤታቸው በሚገኝበት ሮንዶርፍ ውስጥ አርፈው እዚያው ተቀበሩ። የአደናወር መኖሪያ ቤት ብዙ የዓለም መሪዎችን አስተናግዷል። በአደናወር ቤት ከተስተናገዱት መሪዎች መካከል ለአውሮጳ አንድነት ከዚያም ቀደም ሲል በጠላትነት ይተያዩ ለነበሩ ለጀርመን እና ለፈረንሳይ ወዳጅነት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉት ሻርል ደጎል ይገኙበታል። በበአደናወር ቤት ግቢ ውስጥ ርሳቸውና ደጎል ጎን ለጎን ቆመው የሚታዩበት ቅርጽ ይገኛል። የኢትዮጵያው ንጉስ አጼ ኃይለ ሥላሴ ከአደናወር ጋር የቅርብ ግኝኙት ከነበራቸው መሪዎች አንዱ ናቸው። ምዕራብ ጀርመን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተገለለችበት ወቅት የኢትዮጵያው የመጨረሻ ንጉሥ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጀርመንን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የጎበኙ የመጀመሪያው የውጭ መሪ ነበሩ።  አስጎብኝአችን ሽሚት እንዳሉት የአጼ ኃይለ ሥላሴ ጉብኝት በጀርመን ልዩ ቦታ ይሰጠዋል።
 «የመጡት በ1954 ነው። የፌደራል ጀርመን ሪፐብሊክን የጎበኙ የመጀመሪያው የውጭ እንግዳ ነበሩ። የኃይለ ሥላሴ ጉብኝት በጣም ትልቅ ቦታ ይይዛል ምክንያቱም የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክን ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኙ የውጭ መሪ ናቸው። ይህ በርግጥ ከብዙ ዓመታት በኋላም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በናዚ ጀርመን በተፈጸሙት ወንጀሎች ምክንያት ለተገለለችው ለአዲሲቷ ጀርመን ትልቅ ስኬት ነበር። እናም የርሳቸው ጉብኝት የከዚህ ቀደሙን የጀርመን መገለል ያስቀረ እርምጃ ነበር። በ1940 ዎቹም ከጦርነቱ በኋላ ጀርመን በምግብ እጥረት በተቸገረችበትት ወቅትም ኃይለ ሥላሴ ለጀርመን መንግሥት እርዳታ በቆሎ ልከዋል።ኃይለ ሥላሴ አደናወር ከተቀበሩ ከሁለት ሳምንት በኋላ መቃብራቸው ላይ ተገኝተው የአበባ ጉንጉን አኑረዋል። »
በሮንዶርፉ ቤተመዘክር ውስጥ የዚህ ማስታወሻ የሆነው ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ እና ኢትዮጵያ በጀርመንኛ የተጻፈበት ባንዲራ ከሌሎች አገራት ባንዲራዎች ጋር ተሰቅሎ ይገኛል።

Deutschland Konrad-Adenauer-Haus in Rhöndorf
ምስል DW/H. Melesse
Äthiopischer Kaiser Haile Selassie zu Besuch in Bonn 1954
ምስል picture alliance/dpa
Deutschland Konrad-Adenauer-Haus in Rhöndorf
ምስል DW/H. Melesse
Deutschland Konrad-Adenauer-Haus in Rhöndorf
ምስል DW/H. Melesse
Deutschland Konrad-Adenauer-Haus in Rhöndorf
ምስል DW/H. Melesse

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ