ኮት ዲቯር እና አዳጋቹ የዕርቀ ሰላም ሂደት | አፍሪቃ | DW | 22.04.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ኮት ዲቯር እና አዳጋቹ የዕርቀ ሰላም ሂደት

በ 2010 ዓም ከተካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በኋላ አስከፊ ግጭት በታየባት ኮት ዲቯር ውስጥ በነገው ዕለት የከተሞች እና ያካባቢ ምክር ቤቶች ምርጫ ይደረጋል። ታዛቢዎች እንዳመለከቱት፡ በሰሞኑ የምርጫ ዘመቻ ወቅት ደም አፋሳሽ ግጭት ተካሂዶዋል።

ለዚህም አላሳን ዋታራ ያሸነፉበትን የፕሬዚደንታዊ ምርጫ ውጤት የቀድሞው ፕሬዚደንት ሎውሮ ባግቦ አልቀበል በማለት ሥልጣኑን ለዋታራ ለማስረከብ ፈቃደኛ ባልሆኑበት ጊዜ የተከሰተው ቀውስ እና በመፍቀሬ ባግቦ ተጠያቂ ነው። እንደሚታወሰው፡ በዚያን ጊዜ በባግቦ እና በዋታራ ደጋፊዎች መካከል በቀጠለው ግጭት ከ 3000 የሚበልጥ ሰው ሕይወት ከመጥፋቱ ሌላ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩም ለስደት ተዳርገዋል። ቀውሱ በፈረንሣይ ድጋፍ  በ 2011 ዓም የፀደይ ወራት ካበቃ በኋላ ዋታራ የፕሬዚደንትነቱን ሥልጣን ለመያዝ በቅተዋል።

ከሥልጣን የተወገዱት እና በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ የተላለፈባቸው ሎውራ ባግቦም ከዚያን ጊዜ ወዲህ ዘ ሄግ ኔዘርላንድስ  በእስር ላይ ይገኛሉ። የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ዳኞች በወቅቱ ስለኮትዲቯር ድህረ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ግጭት የቀረቡት ማስረጃዎች በባግቦ አንፃር ክስ መመሥረት ማስቻል አለማስቻላቸውን እየመረመሩ ነው።  
በኮት ዲቯር የ 2010 እና የ 2011 ዓም ቀውስ ካበቃ ዛሬ ከሁለት ዓመታት በኋላም በባግቦ እና በዋታራ ደጋፊዎች መካከል በተከፋፈለችው ሀገር ውስጥ ገና ዕርቀ ሰላም አልወረደም። ያኔ የተፈጠረው ልዩነት ምን ያህል ሥር የሰደደ መሆኑ ዛሬም በግልጽ የሚታይ መሆኑን በአቢዦ የሚገኝ የአንድ የኮትዲቯር ሲቭል ማህበረሰብ አባልደረባ የሆነችው አሜሊ ካጃኒ ገልጻለች።


« ፖለቲከኞች ሀቁን እስካልተናገሩ እና ቀድሞ በሥልጣን ላይ የነበሩትም ለተግባራቸው ይቅርታ እስካልጠየቁ ድረስ በሀገሪቱ ዕርቀ ሰላም ይወርዳል ብሎ መናገር አይቻልም። አሸናፊው ወገን ፍትሑን በእጁ ማስገባት የለበትም። አሁን በቕልጣን ላይ ያሉት ከነርሱ በፊት የነበሩት የፈፀሙትን ስህተት መድገም የለባቸውም። »
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናልም ይህንኑ ነው ያሳሰበው። የባግቦ ደጋፊዎች ለፈፀሙት ጥቃት  የፕሬዚደንት አላሳን ዋታራ መንግሥት ጦር በአስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አፀፋ መልስ ምጠታቸውን በተመለከተ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው የካቲት ወር ባወጣው ዘገባ በድጋሚ አስታውቋል። ሌሎች የመብት ተሟጋች ድርጅቶችም በርካታ ተመሳሳይ ጽሑፎችን አውጥተዋል። ይህ መሆኑ እየታወቀ ግን፡ የፕሬዚደንታዊው ምርጫ ተሸናፊ ባግቦ ብቻ አሁን ዘ ሄግ ለፍርድ መቅረባቸውን ብዙ የኮት ዲቯር ዜጎች እና ብዙ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ትክክለኟ ርምጃ ሆኖ አላገኙትም። ዳንየል ጄጅን የመሰሉ የሀገሪቱ ዜጎች ግን ፍትሕ እስኪገኝ ብዙ ጊዜ እንደሚወስድ ነው የሚያምኑት።
« አጥፍተዋል የተባሉ የጦር መኮንኖች፡ የፀጥታ አስከባሪ እና ፖሊሶች ታስረው ለፍርድ ቀርበዋል። ስለዚህ ለውጦች ለማየት ሂደቶችን በትዕግሥት መጠበቅ አስፈላጊ ይሆናል። »
የ2010/2011 ዓም ቀውስ ተፅዕኖ በነገው ዕለት በሀገሪቱ በሚካሄደው የከተሞች እና ያካባቢ ምክር ቤቶች ምርጫ ላይ እየታየ ነው።  በአቢዦ የሚገኘው የጀርመናውያኑ የፍሪድሪኽ ኤበርት ተቋም ባልደረባ የንስ ኡቨ ሄትማን እንዳስታወቁት፡ ፓርቲው መሪው ባግቦ በነፃ እንዲለቀቁ ያቀረበው ቅድመ ግዴታ ባለመሟላቱ ፓርቲው በነገው ምርጫ አይሳተፍም።


ይህም፡ ታዛቢዎች እንዳመለከቱት፡ በሥልጣን ላይ ያለው ገዢው ፓርቲ የማሸነፍ ዕድልን ከፍ ቢያደርገውም፡ በሀገሪቱ ጥምረት በፈጠሩት ቀሪዎቹ ሁለት ትላልቅ ፓርቲዎች፡ ማለትም በዋታራ እና በኮት ዲ ቯር መሥራች አባት ፌሊክስ ኡፌት ቡዋኜ ፓርቲዎች መካከል በወቅቱ ልዩነት እንደታየና ካንዳንድ የምርጫ ቀበሌዎች በስተቀር በጋራ እንደማይወዳደሩ ነው የተገለጸው። ሁለቱ ፓርቲዎች ባግቦ ከታሰሩ በኋላ ባንድነት የሚያቆያቸው አንድም ምክንያት ያለ እንደማይመስል ሄትማን አስታውቀዋል። በምርጫው ዘመቻ ወቅት ባጠቃላይ በኮት ዲቯር በጎሣ እና በሀይማኖት መስመር አሳሳቢ ክፍፍል ቢታይም፡ የሀገሪቱ ሕዝብ ይህን ሁኔታ ለማብቃት የሚያስችል ፖለቲካ እንዲነደፍ በግልጽ መጠየቅ ጀምሮዋል። የባግቦ ጎራ የፕሬዚደንት ዋታራ መንግሥት፡ ምንም እንኳን ደጋፊዎቹም የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈፀማቸውን የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች ቢኖሩም፡ አሁንም ፍትሑን በእጅ ማስገባቱን ቀትሎዋል በሚል መውቀሱን አላቋረጠም።በአቢዦ የሚገኘው የዩኤስ አሜሪካ አምባሳደር ፊሊፕ ካርትየ በድህረ ፕሬዚደንታዊው ምርጫ ከባድ ጥፋት የሰሩ ሁሉ ለፍርድ መቅረብ ይገባቸዋል ብለዋል። ልክ እንደ ኮት ዲቯር ሕዝብ፡ የመብት ተሟጋች ድርጅቶችም በሀገሪቱ ስር የሰደደው ልዩነት ሊወገድ እና ዕርቀ ሰላም ሊወርድ የሚችለው ከሁለቱም ወገን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈፀሙት ሁሉ ፍርድ ፊት ቀርበው ትክክለኛ ፍትሕ ሲሰጥ ብቻ መሆኑን አሳስበዋል።

አርያም ተክሌ

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic