ኮትዴቩዋር፤ የፍፃሜዉ ዉጊያ ዝግጅት | ኢትዮጵያ | DW | 04.04.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ኮትዴቩዋር፤ የፍፃሜዉ ዉጊያ ዝግጅት

በአይቮሪኮስት የፕሬዝደንትነቱን መንበር ለመቆጣጠር የሚደረገዉ ፍልሚያ ቀጥሏል።

default

ስልጣኔን አልለቅም ብለዉ ባስቸገሩት የሎረን ባግቦ ታማኝ ኃይሎችና፤ በምርጫ ማሸነፋቸዉ ተቀባይነት ያገኘዉ የአላሳን ኡዋታራ ደጋፊዎች መካከል ካለፈዉ ሳምንት አንስቶ በአቢዣን ዉግያዉ በመጠናከሩ ኗሪዎቿ እንደሚሉት፤ ከተማዋ የተወረረች መስላለች። ዛሬ የኡዋታራ ኃይሎች ለወሳኝ ፍልሚያ እየተዘጋጁ እንደሆነ ሲነገር፤ የባግቦ የጦር ኃይል አዛዥ የተጠለሉበትን የደቡብ አፍሪቃ ኤምባሲ ለቅቀዉ ወጥተዋል። በአገሪቱ ምዕራባዊ ግዛት ዱኩዎ ደግሞ ጭፍጨፋ ተካሂዷል፤ የጅምላ ቀብርም ተገኝቷል ተብሏል።

Elfenbeinküste Unruhen nach Wahl

አላሳን ኡዋታራ

የተመድ የደጋፊዎቻቸዉ ተሳትፎ አለበት የተባለዉን ጭፍጨፋ እንዲያጣሩ አላሳን ኡዋታራን ጠይቋል።

ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነፃ ከሆነች የአንድ የጎልማሳ እድሜ የቆጠረችዉ ምዕራብ አፍሪቃዊቱ አገር አይቮሪኮስት ባለፈዉ ህዳር ወር ምርጫ ስታካሂድ ይህን ወደመሰለዉ የወቅቱ ዉጥንቅጥ እንዳትገባ ስጋት ነበር። ብዙ ዘግይቶ በዓለም ዓቀፍ ጫና የተካሄደዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የወቅቱ ፕሬዝደንት ሎረን ባግቦ፤ በአዉሮፓዉያኑ 1999 መፈንቅለ መንግስት ስልጣን የተቀሙት የቀድሞ ፕሬዝደንት ሄንሪ ኮናን ቤዲ እንዲሁም ቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርና በዓለም የገንዘብ ተቋም IMF ባለስልጣን የነበሩት አላሳን ኡዋታራ የተፎካከሩበት የህዳሩ ምርጫ ዉጤቱ የተፈራዉን ስጋት እዉን አደረገዉ። ፕሬዝደንት ባግቦ የምርጫ ኮሚሽኑ ይፋ ያወጣዉንና፤ ዓለም ዓቀፍ ታዛቢዎችም ይሁንታ የሰጡትን ዉጤት ለመቀበል አልደፈሩም። ጉዳዩ ከሽምግልና፤ ወደማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያ የዘለለ መልዕክትን ከአካባቢዉና ከዓለም ዓቀፍ ተቋማት ቢያስከትልም ባግቦ አሻፈረኝ አሉ። ይህ ደግሞ አገሪቱን ወደተፈራላት ግጭት ከተታት፤ በተለይ ባለፈዉ ሳምንት በተለያዩ ከተሞች ዉጊያዉ ተባብሶ የሲቪሉን ህዝብ ህይወት አደጋ ላይ እንደጣለ ከስፍራዉ የሚወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ። የተመድ በተለይ በምዕራባዊቱ የአገሪቱ ግዛት ዱኩዌ በመቶዎች የተጠሩ ሲቩሎች መጨፍጨፋቸዉን በመጠቆም በስፍራዉ የተፈፀመዉን የመብቶች ጥሰት የሚያጣራ ቡድን ወደስፍራዉ ልኳል። በአይቮሪኮስት የዓለም ዓቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ቃል አቀባይ ጆርጅ ኢብራሂም ቱንካራ ቡድናቸዉ በስፍራዉ ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስ የ800 ሰዎች አስከሬም መመልከቱን፤ ይህ የሆነዉም በማኅበረሰቦች መካከል በተከሰተ ግጭት ነዉ ብለዉ እንደሚገምቱ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። ለዚህ ድርጊት ኃላፊነቱን ሊወስድ የሚገባዉ ወገን የትኛዉ ነዉ ለሚለዉ ግን አሁን መልስ የለንም ነዉ ያሉት፤

«አሁን ይህን ጥያቄ ለመመለስ አንፈልግም። የምን ፈልገዉ ዓለም ጉዳዩን እንዲያዉቅና እንዲህ ያለዉ ድርጊት ዳግም እንዳይደገም እንዲያሳስብ ነዉ። እያንዳንዱ ኃላፊነቱን መዉሰድ ይኖርበታል።»

ካሪታስ የተሰኘዉ ግብረ ሰናይ ድርጅት በበኩሉ ወደተጠቀሰዉ ስፍራ የተጓዙ አባላቱ በነበረዉ ዉጊያ አንዲ ሺ የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸዉን ወይም የገቡበት እንዳልታወቀ መረዳታቸዉን አስታዉቋል። ከተማዋን ከባግቦ ኃይሎች ለማስለቀቅ የኡዋታራ ደጋፊዎች መፋለማቸዉንና አሁን በቁጥጥራቸዉ ሥር እንዳስገቧትም ተገልጿል። የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሓፊ ባን ጊ ሙን ኡዋታራ የተባለዉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና ጭፍጨፋዉን እንዲያጣሩ አሳስበዋል። የኡዋታራ ወገን ክሱን ዉድቅ አድርጎታል። በአንፃሩ የባግቦ ቃል አቀባይ የአካባቢዉን 90በመቶ የሚቆጣጠረዉ ወገን ተጠያቂ ነዉ በማለት የእሳቸዉን ጎራ ከደሙ ንፁህ ነዉ ብለዋል። እንዲያም ሆኖ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ዓለም ፊቷን ያዞረችባቸዉ ስልጣን ላለመልቀቅ የሚሟሟቱት ሎረን ባግቦም ሆኑ ፕሬዝደንትነታቸዉን የሚያረጋግጥላቸዉን መንበር ለመረከብ የሚዋደቁት አላሳን ኡዋታራ በሚያደርጉት ፍልሚያ አንዳቸዉም ለሰብዓዊ መብቶች ጥንቃቄ አላደረጉም ሲሉ እየተቹ ነዉ። ከዓመታት በፊት የተካሄደዉ የእርስ በርስ ጦርነት ያሳረፈባት ጠባሳ ባልሻረላት አይቮሪኮስት የባግቦ ታማኝ ኃይል በንግድ ከተማዋ አቢዣን የሚገኘዉን መንበረ መንግስት ላለመልቀቅ የሞት ሽረት ትግል ማድረጉን ሲቀጥል፤ የኡዋታራ ደጋፊዎች በበኩላቸዉ ወሳኝ ያሉትን ጥቃት አቢዣን ላይ ሊሰነዝሩ ማቀዳቸዉ ዛሬ ተሰምቷል። ከተማዋን ለመክበብ ተሳክቶልናል ያሉት የኡዋታራ ጠቅላይ ሚኒስትር ጉላዉሜ ሶሮ ወታደሮቻቸዉ ወደከተማዋ ገብተዉ የባግቦን ወታደሮች ማዋከቡ ተሳክቷል እያሉ ነዉ። በዚህ የተደናገጡት ከባግቦ ጎን በታማኝነት ሲዋደቁ የቆዩ በርካታ ወታደሮችም ወደተቃራኒዉ ጎራ መቀላቀል መጀመራቸዉን በመጠቆምም ዝግጅቱ በመጠናቀቁ የፍፃሜዉን ጦርነት ለማካሄድ ጊዜ መድረሱን አብራርተዋል። ባግቦ ደጋፊዎቻቸዉ በመሸጉበት መኖሪያ ቤታቸዉ አካባቢ እንዲሰለፉ በማድረግ በሰብዓዊ ጋሻነት እንደተጠቀሙ ሲነገር፤ የወሳኙ ፍልሚያ ዝግጅቱ ተጠናቋል በተባለበት ወቅት የጦር ኃይል አዛዣቸዉ ተጠልለዉበት ከነበረዉ የደቡብ አፍሪቃ ኤምባሲ ከነባለቤትና ልጆቻቸዉ መዉጣታቸዉ ተሰምቷል። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸዉ ወገኖችን ጠቅሶ የጀርመን የዜና ወኪል እንደዘገበዉ ምናልባትም ጀነራል ፊሊፕ ማንጉ የቁርጥ ቀን አጋርነታቸዉን ለማስመስከር ወደባግቦ መኖሪያ ሳይገቡ አልቀረም።

Elfenbeinküste Unruhen nach Wahl

 

የቀድሞ የኮትዴቩዋር ቅን ገዢ ፈረንሳይ ለወራት የዘለቀዉ የአገሪቱ የስልጣን ፍትጊያ ማክተሚያዉ መድረሱን በመረዳት ይመስላል ሰላማዊ ሰዎችን ከጥቃት ለመከላከል በሚል ተጨማሪ ወታደሮችን ልካለች። አምስት ሚሊዮን ኗሪ እንዳላት በተነገረዉ ባግቦ በመሸጉባት አቢዣን ወታደሮች ጉዳናዎችን ሲቃኙ፤ በርካታ የዉጭ ሀገራት ዜጎች በፈረንሳይ ኤንባሲ ተጠልለዋል። ከአቢዣን ኗሪዎች አንዱ የከተማዋን ሁኔታ ሲገልፁ፤

«ህይወት እንቅስቃሴ ያቆመች ያለች ይመስላል። ሰዎች መንገድ ላይ አይታዩም፤ ታክሲ የለም፤ አዉቶሞቢል የለም። ጭር ማለቱ ያስፈራል።»

በአቢዣን ሱቆች በመዘጋታቸዉ የምግብ እጥረትም እንደገጠመ እየተነገረ ነዉ።

የምርጫ ዉጤቱን አሻፈረኝ ብለዉ ስልጣን ላለመልቀቅ የቆረጡት ሎረን ባግቦ የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሃብት ማኅበረሰብን ማግባቢያ፤ የአፍሪቃ ኅብረትን ሽምግልና፤ የተመድንም ማሳሰቢያ አሻፈረኝ እንዳሉ ለራሳቸዉ ብቻ ሳይሆን ከጎናቸዉ የቆሙትን ሁሉ የሚጎዳዉን የዉዝግብ መስመር መምረጣቸዉ የክብር ዘመናቸዉን ፍፃሜ እያፋጠነዉ ነዉ።   

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሠ