ኮትዲቯር ከባግቦ በሕዋላ | ኢትዮጵያ | DW | 13.04.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ኮትዲቯር ከባግቦ በሕዋላ

መንበሩን ሴኔጋል ያደረገዉና RADDHO በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ የመብት ተሟጋች ድርጅት የበላይ አልዮኔ ቲኔ ግን በኮትዲቯር ዘላቂ ሠላም ለማስፈን የዉጪዉ ርዳታና ድጋፍ ብቻ በቂ አይደለም።

default

13 04 11

የቀድሞዉ የኮትዲቯር ፕሬዝዳንት ሎራ ባግቦ መታሠር ምዕራብ አፍሪቃዊቱን ሐገር ላለፉት አራት ወራት ያደቀቀዉን ደም አፋሳሽ ብጥብጥ እንዳስቆመ የተለያዩ ወገኖች እየመሠከሩ ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ምዕራባዉያን ሐገራትም ለአዲሱ ፕሬዝዳት ለአላሳነ ዋታራ የሚሰጡትን ድጋፍና ርዳታ እንደሚያጠናክሩ ቃል ገብተዋል።ይሁንና ባግቦ በተያዙ በሰወስተኛዉ ቀን ዛሬም በሐገሪቱ ትልቅ ከተማ አቢዣ ሙሉ በሙሉ ሠላም አልሰፈነም።አንዳድ የፖለቲካ አዋቂዎች እንደሚሉት በኮትዲቯር ዘላቂ ሠላም ለማስፈን የዋተራ መንግሥት ሕዝቡን ለማሳመን አበክሮ መጣር አለበት።ነጋሽ መሐመድ የኮትዲቯርን ሁኔታ ባጭሩ ይቃኛል።

ታሪክ በዚያች ለም ዉብ ሐገር እራሱን መደግሙን በርግጥ ከሳቸዉ በላይ የሚያቅ ብዙም የለም። የታሪክ ፕሮፌሰር ነበሩ።ሎራ ባግቦ።ፖለቲካዉን በተቀየጡ ማግሥት ትልቁን ሥልጣን ነበር የከጀሉት።በርግጥም እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቅጣጠር ጥቅምት ሁለት ሺሕ በተደረገዉ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸዉ ተመሠከረላቸዉ።

ሥልጣን ላይ የነበሩት የቀድሞዉ ጄኔራል ሮበርት ገዬ ግን የምርጫዉን ዉጤት ለመቀበል እና ቤተ-መንግሥቱን ለማስረከብ ፍቃደኛ አልነበሩም።ባግቦ ደጋፊዎቻቸዉን አዝምተዉ ጉዬን ቅሌን ጨርቄን ሳይሉ ከቤተ-መንግሥት አባረሯቸዉ።

ዘመን-ዘመንን ሽሮ በአስራ-አንደኛዉ አመት ሰኞ ሲደርስ አቢዣ ላይ ታሪክ እራሱን ደገመ። የባግቦ ጀምበር ጠለቀች። ከአስር አመት በላይ የለመዱትን ሊሞዝን፥ ተቀምተዉ፥ ሱፍ ኮት ከረባታቸዉን ተገፈዉ ሸሚዝ፥ ከናቴራ እንዳጠለቁ በታንክ እየተነዱ ዘብጥያ ተወረወሩ።የኮትዲቯር ጀምበር አሁን በርግጥ ለአላሳኔ ዋታራ ደምቃለች።የጀርመን መንግሥት የአፍሪቃ ጉዳይ ተጠሪ ቫልተር ሊንድነር እንዳሉት ደግሞ የባግቦ ፍፃሜ ለኮትዲቯር ሕዝብ፥ ለዲሞክራሲም ድል ነዉ።

«ለሐገሪቱ ሕዝብና ዲሞክራሲ በርግጥ ድል ነዉ።ምርጫዉን ያሸነፉት አሁን በትክክል ቤተ-መንግሥት መግባት የሚችሉበት ነዉ።ይሕ አፍሪቃ ዉስጥ ባሁኑ ወቅት ወደ ሃያ ምርጫ ለሚደረግባቸዉ (ሐገራት) አስተምሕሮቱ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።ሁኔታዉ ባይቀየር ኖሮ በምርጫ ብንሸነፍም ቤተ-መንግሥቱን እንደተቆጣጠርን እንቀጥላለን፥ የሚነካን የለም የሚል መልዕክት ነበር የሚያስተላልፈዉ።ለዚሕም ነዉ (የባግቦ መያዝ) ለዲሞክራሲ ድል የሚሆነዉ።ባይያዙ ኖሩ ድም መፋሰሱ ይቀጥል ነበር።»

No Flash Elfenbeinküste Unruhen Abidjan Rebellen

የዋታራ ታማኞች

ትናንት ዋታራን በሥልክ «እንኳን ደስ ያለዎት» ያሉት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማም የጀርመኑን ባለሥልጣን ቃል በሌላ አባባል ደግመዉታል።ለኮትዲቯር ሠላምና ልማት ጥሩ መደላድል፥ ለዲሞክራሲዋም መልካም ጅምር ብለዉ።ባግቦን የማረከዉን ጦር ያዘመቱት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳት ኒካላ ሳርኮዚ፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙንም የዋታራን ድል ከኦባማ በላይ ቢያዳንቁት እንጂ በርግጥ አያሳንሱትም።

ፕሬዝዳንት ኦባማ ለዋተራ እንደነገሩት መስተዳድራቸዉ አዲሲቱን ኮትዲቯርን በየመስኩ ለመርዳት ዝግጁ ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን እንዳሉት ደግሞ ድርጅታቸዉ «ወሳኝ» ያሉትን ሰብአዊ ርዳታ ይሰጣል።የአዉሮጳ ሕብረትና ፈረንሳይም ለኮትዲቫር 580 ዩሮ አስቸኳይ ርዳታ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

መንበሩን ሴኔጋል ያደረገዉና RADDHO በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ የመብት ተሟጋች ድርጅት የበላይ አልዮኔ ቲኔ ግን በኮትዲቯር ዘላቂ ሠላም ለማስፈን የዉጪዉ ርዳታና ድጋፍ ብቻ በቂ አይደለም።

«አሻናፊዉ የዉጊያ ስሜትን ለመቀዝቀዝ ጊዜዉ የሚጠይቀዉን ካላደረገ ማለት በኮትዲቯር ሕዝብ ዘንድ እረቀ ሠላም ካላወረደ ግጭቱ ይቀጥላል።ሥልጣኑን ለሁሉም ኮትዲቮሪያዉያን ማጋራት ያስፈልጋል።የብሔራዊ አንድነት መንግሥት መመሥረት ያሻል።ከዚሕም በተጨማሪ የሐቅ፥ ፍትሕና እርቅን ለማዉረድ አግባቢ እርምጃ መዉሰድ በጣም አስፈላጊ ነዉ።ከግጭቱና ከምርጫዉ በሕዋላ ያለዉ የሐይለኞች ምግባር ነዉ።በዚሕም ሁሉንም የሐገሪቱ ዜጎች እርቀ-ሠላም እንዲያወርዱ መጣር የግድ ነዉ።»

Elfenbeinküste Laurent Gbagbo Verhaftung

ባግቦ

ትልቂቱ የኮትዲቯር ከተማ አቢዣ ዛሬም ሙሉ በሙሉ አልተረጋጋችም።ከተማይቱን የሚጠብቁት የሐገሪቱ ፀጥታ አስከባሪዎች ብቻቸዉ አይደሉም።ከፈረንሳይ ጦር ጋር እንጂ።

ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የተሰኘዉ የፖለቲካ ጥናት ተቋም ባልደረባ ሪናልዶ ዴፓኜ እንደሚሉት የዋታራ ሠላም ለማስፈን ፈጥነዉ ካልዘየዱ የሰከነዉ ግጭት የማያገረሽበት ምክንያት የለም።ከዚሕም በተጨማሪ የተማረኩት ባግቦ ባለፈዉ ሕዳር በተደረገዉ ፕሬዝዳንታዊዉ ምርጫ ሰላሳ-ስምንት ከመቶ ድምፅ አግኝተዋል። ይሕን ድምፅ የሰጣቸዉ ሕዝብ ድጋፍ አላቸዉ።የሚመሩት የፖለቲካ ፓርቲም ጠንካራ ተቃዋሚ መሆኑ አይካድም።በዚሕም ሰበብ ዴፓኜ እንደሚሉት በባግቦ ላይ የሚወሰደዉ እርምጃ ደጋፊዎቻቸዉን የሚያስቆጣ አይነት ከሆነ ኮትዲቯር ሠላም አትሆንም።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ