ኮቪድ 19: የወጣት ስራ አጡን ሁኔታ ጭራሽ አባብሷል | ወጣቶች | DW | 22.05.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

ኮቪድ 19: የወጣት ስራ አጡን ሁኔታ ጭራሽ አባብሷል

ድሮም ቢሆን ለአፍሪቃውያን ወጣቶች ጥሩ ስራ ማግኘት ፈታኝ ነበር። አሁን ደግሞ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ብዙ ሰዎች ስራቸውን አጥተዋል። በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ከነዚህ ስራ አጣቶች መካከል የተወሰኑትን እንግዳው አድርጓል። እንዲሁም የኢኮኖሚ ምሁር አልበርት ዘፋክ አጋጣሚውን የአፍሪካ ወጣቶች እንዴት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ይጠቁማሉ። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:01

ኮቪድ 19: የወጣት ስራ አጡን ሁኔታ ጭራሽ አባብሷል

የኮሮና ወረርሽኝ ባስከተለው ቀውስ ምክንያት በዓለም ዙርያ በርካታ ሰዎች ስራቸውን አጥተዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ከመጋቢት ወር አንስቶ ከ 36 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ስራ አጥ ሆነዋል። እንደ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም UNDP ከሆነ አፍሪቃ ውስጥ በኮሮና ወረርሽኝ የተነሳ ግማሽ በመቶ ያህሉ ስራቸውን ሊያጡ ይችላሉ። ከዚህ ቀውስ እስኪያገግሙም አመታት ሊፈጅ ይችላል። ድሮም ቢሆን ስራ ማግኘት ፈተና ለሆነባቸው የአፍሪቃ ሀገራት ወጣቶች ይህ በሽታ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባቸዋል።  ቀውሱ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ለዶይቸ ቬለ DW  እንደገለፁት « የኮሮና ቫይረስ ስራው ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ ከባድ ነው። ሰራተኛ በሙሉ ተቀንሷል። ስራው ቆሟል ማለት ይቻላል። እኛም ስናውደለድል ነው የምንኖረው። ሰራተኛ ተበትኖ ነው ያለው።» ይላል ዝናቡ የተባለው ወጣት።  ወጣት በረከት ደግሞ ሻይ እና ቡና እየሸጠች ነው የምትኖረው።  « ገበያ የለም።  ኮሮና ከገባ ጀምሮ 100 ብር እንኳን ባንክ አስገብቼ አላውቅም።  ጎዳና ላይ ከመውጣት ብለን ነው እንጂ ምንም አናገኝም። እኔ ራሴም ድጋፍ እየፈለኩ ነው ያለሁት። » 
አሰጋኸኝ የሴቶች ፀጉር ባለሙያ ነው። « ሁለት ሶስት ሰራተኛ ነው የነበረኝ። አሁን ሰራተኛ አስወጥቼ ብቻዬን ነው የምሰራም። እንደዚህም ሆኖ ስሰራ አንድ ሰው እንኳን ፀጉሩን ለመሰራት አይመጣም።»  ይላል። ከመንግስት የሚጠብቀው ነገር በግብር ላይ ቅናሽ እንዲያደርግ ቢቻል ደግሞ ግብሩን በዚህ ዓመት ሙሉ በሙሉ እንዲሰርዝ ነው። 
ዝምባዌ ውስጥም የሀገሪቱ ወጣቶች እንደሚሉት ስራ አጥነት በኮሮና ወረርሽኝ የተነሳ ተባብሷል። « የኮሮና ተህዋሲ እንደልባችን የፈለግንበት እንዳንሄድ አድርጎናል። እኔ ለምሳሌ ፎቶ አንሺ ነኝ እና ስምንት ትዕዛዞችን ለመሰረዝ ተገድጄያለሁ። ምንም አይነት ዝግጅቶች እየተካሄዱ አይደለም እና በጣም የሚገርም ሁኔታ ነው ያለው። በፋይናንስ ረገድ በጣም ጎድቶኛል። »

USA Steigende Arbeitslosigkeit durch Coronavirus (Getty Images/J. Raedle)

የስራ አጥ ቁጥሩ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው

« እኔ ገቢያቸውን ካጡት ሰዎች አንዷ ነኝ። ይህ ለእኔ በጣም ከባድ እና እጅግ ጭንቀት ውስጥ የሚከት አጋጣሚ ነው። በሳምንቱ መጨረሻ እንኳን ከጎደኞች ጋር መገናኘት አለመቻል ይከብዳል። « የእንቅስቃሴ እገዳው በተግባር ላይ ሲውል በማንኛውም ረገድ በህይወቴ ላይ ጫና ፈጥሯል። ምክንያቱም ምንም አይነት ገቢ አላገኝም። የቤት ኪራዬን እንኳን መክፈል አልቻልኩም። »ግን ወጣቶች ይህን አጋጣሚ ለበጎ ሊጠቀሙበት ይችሉ ይሆን? እስቲ የአፍሪቃ የዓለም ባንክ ተጠሪ የኢኮኖሚ ምሁር አልበርት ዘፋክ « በምግብ አቅርቦት ሰንሰለቱ ውስጥ (food supply chain) ወጣቱ አንዱ ጋር ራሱን ለማስገባት መጣር አለበት ያለበለዚህ በትላልቅ ከተሞቻችን የምግብ እጥረት ቀውስ ይገጥመናል። አንድ ማወቅ የሚገባን ነገር ቢኖር ይህ የአለም መጨረሻ አይደለም ግን ጠንከር ያለ ነገር ነው። እና አፍሪቃ ይህንን መጥፎ በሽታ መዋጋት እንድትችል የበኩላችንን ድርሻ እንወጣ። በአንድ ቀውስ ውስጥ ሁል ጊዜ እድልም አለ። ይህ አጋጣሚ ደግሞ አያምልጣችሁ።» ይላሉ።
ወደ ዩጋንዳ ዞር ስንል በዚህ ቀውስ ስራ አጥ የሆነችው ዩጋንዳዊቷ አሚና በፀሀይ ብርሃን የሚሰራ የኃይል ማመንጫ መሳሪያዎች በሚሸጥበት ሱቅ ውስጥ እንግዳ ተቀባይ ሆና ትሰራ ነበር። ከስራ የመሰናበቷን የሚገልፀው ደብዳቤ ሲደርሳት ሀዘን ነበር የተሰማት። «እንደምታዩት እዚህ ሀገር ላይ ምንም አማራጭ የለንም። ስለዚህ ወደቤት ሄዶ አርፎ መቀመጥ ነው። በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ የምንመገበው ነገር ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ። ምክንያቱን ስራ የለንም። ደሞዝም አይከፈልም። » ስለሆነም አሚና ለመኖር ያላት የመጨረሻ አማራጭ የቤት እቃዋን እያወጣች መሸጥ ሆኗል። አሁን ግን አልጋዬ ብቻ ነው የቀረኝ ትላለች። በዚህ ችግር ብቸዋን አይደለችም። የሀገሯ ወጣት የሆነው ቶም እንደ ሬዲዮ፣ ሶላር ፓናል የመሳሰሉ ኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን እየጠገነ እና እየሸጠ ነበር የሚተዳደረው። እሱም ስራ አጥ የሆነው ገና ቀውሱ እንደጀመረ ነው።« ደንበኞቻችን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ናቸው። ስለሆነም መሰረታዊ ፍላጎት የሆነውን ምግብ መግዛት ትተው በፀሀይ ብርሃን የሚሰራ የኃይል ማመንጫ መሳሪያ ሊገዙ አይመጡም። ስለሆነም መብራት ለማግኘት ወደ ቀድሞው አማራጫቸው ተመልሰዋል። በዚህ የተነሳም ስራ የለኝም። ይህ ማለት ደግሞ ቤተሰቤን የምመግብነት ገቢ አላገኝም። እና በጣም የሚያሳዝን ሁኔታ ላይ ነው ያለነው።» ሌላዋ ወጣት ፍራንክሊን የሰራተኞችን ውል እና ክፍያን የሚመከቱ ጉዳዮችን በመፈፀም ነበር የሰው ኃይል አስተዳደር ክፍል ውስጥ የምትሰራው። ዛሬ እሷም ስራ አጥ ሆናለች። ይህ ፍፁም ያልጠበቀችው ነገር ነበር።« የስራ መልቀቂያው ሲመጣ የሞት ብይን ነው የመሰለኝ። በአሁኑ ሰዓት የቆጠብኩት በጣም ትንሽ ገንዘብ ነው ያለኝ።  ምን እንደማደርግ አላውቅም። አለቃዬ ደውሎ ድርጅቱ ትርፍ እያገኘ አይደለም እና ሰራተኛ እንቀንሳለን ሲል። እኔ የመሰለኝ ግማሽ ደሞዝ የሚሰጠን እና ነገሮች ሲስተካከሉ ተመልሰን ወደ ስራ የምንገባ ነው። አሁን ግን ጨርሶ እንደማንመለስ ነው የተነገረን።»

Covid-19 und Arbeitslosigkeit in Inhambane Afrika Mosambik

ስራ አጥነት በሞዛምቢክ


ጄኮብ ሙቴሳ የአንድ የስራ አጥ ኤጀንሲ እራ አስኪያጅ ናቸው።  በኮሮና ወረርሽኝ የተነሳ ሀገራቸው ዩጋንዳ በርካታ እገዳዎች ከጣለች በኋላ ለስራ አጦች ስራ ማግኘት አልቻሉም።
«ምንም አይነት የስራ እድል አማራጮች በአሁኑ ሰዓት የሉም።  እንደምታውቁት ሁሉም ነገር ተቋርጧል። ብቅ ብቅ በማለት ላይ ያሉ ድርጅቶች ያላቸውን ሰራተኛ እየቀነሱ እና አዲስ ቅጥረኛ እየወሰዱ አይደለም። አብረናቸው እንሰራ እና ለብዙ ሰዎች የስራ እድል ይሰጡ የነበሩ በርካታ ድርጅቶች በእገዳው ምክንያት ተዘግተዋል። አንዳንዶቹ እንደውም መልሰው መክፈትም የማይችሉበት ሁኔታ ነው ያለው። በኮሮና ተህዋሲ የተነሳ ከባድ ጊዜ ነው ከፊታችን የተደቀነው። » ይሁንና ሙቴሳ አፍሪቃዊ ወጣቶች ያላቸውን ጠንካራ ኃይል ተጠቅመው ተስፋ እንዳይቆርጡ ይመክራል። መንግሥታት ደግሞ በዚህ ሊደግፏቸው ይገባል።« ለዚህ ጥሩው አማራጭ ስራ አጥ የሆኑ ወጣቶችን ትናንሽ ፕሮጀክቶች እንዲጀምሩ ማበረታታት ነው።  ለምሳሌ ከውጭ የሚመጡ መገልገያዎችን ማምረት ሊሆን ይችላል። የ ኮቪድ 19 ቀውስ  ቢሮ ውስጥ ቁጭ የሚሉ  የበርካታ ሰራተኞችን አይን ከፍቷል። በሚሰሩበት ሙያ ላይ ብቻ ተማምኖ ደሞዝ እስኪገባ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ምናልባትም በግብርና ሙያ ላይ መሰማራት እና ራስን መቻል እንደሚያስፈልግ ተረድተዋል። ምክንያቱም ቀጣሪዎች በኮቪድ 19 ቀውስ የተነሳ ደሞዝ የመቁረጥ፣ የሰራተኞችን ቁጥር የመቀነስ ርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ።» 

ልደት አበበ/ አሌክስ ጊታ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች