ኮሮና ተሐዋሲ፤ የውጭ ዜጎች ላይ ጥቃት፤ ካትሪን ሀምሊን | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 20.03.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ኮሮና ተሐዋሲ፤ የውጭ ዜጎች ላይ ጥቃት፤ ካትሪን ሀምሊን

የመገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎች ትኩረት ኮሮና ተሐዋሲ የሆነ መስሏል። በየዕለቱ በተለያዩ ሃገራት በተሐዋሲው የተለከፉና የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ብዙዎች ይጽፋሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች ራሳቸውን ከተሐዋሲው ለመከላከል ሊያደርጉት የሚገባውን ከመምከር ጀምሮ የውጭ ዜጎች ላይ በተሐዋሲው ሰበብ ተፈጸሙ የተባሉመገለል እና ጥቃቶችን ያወገዙም አሉ።  

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:57

«የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት»

ኢትዮጵያ ውስጥ ተሐዋሲ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ ትናንት ይፋ ሆኗል። እጅን መታጠብ፣ አለመጨባበጥ እንዲሁም በማኅበራዊ መስተጋብርም ርቀትን ጠብቆ መንቀሳቀስን የሚያሳስብ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ዘመቻ ተጀምሯል። በየመንገዱ ሰዎች እጃቸውን እንዲያጸዱ ውኃና ሳሙና ይዘው የሚያስታጥቡ ወገኖችን የሚያሳዩ ፎቶዎችንም ሰዎች ይቀባበሏቸዋል። ተጠጋግተው ይህን የሚያከናውኑትን በተመለከተ ኃይለ ማርያም ማሞ በፌስቡክ፤ «ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በየአደባባዩና መሥሪያ ቤቶች መግባቢያ ላይ እጅን ማስታጠቡ መልካም ነው። ነገር ግን ሰውን አጠጋግቶ አሰልፎ እጅን ማስታጠብም ሆነ ሌላ አገልግሎት መስጠት ትክክል አይደለም። ቫይረሱ በአመዛኙ ይተላለፋል የሚባለው ከአፍና ከአፍንጫ ከሚወጣ ፈሳሽ ጋር በተያያዘ ነው። ማስክ ማድረጉ ላይ ቢተኮር መልካም ነው። ማስክ እንኳ ቢጠፋ በፎጣም ሆነ በተገኘው አፍንና አፍንጫን ሸፍኖ መንቀሳቀሱ ይበጃል።» ሲሊ መክረዋል። እጃቸውን ለመታጠብ ተጠጋግተው የተሰለፉ ሰዎችን የሚያሳይ ፎቶን አስመልከተው አክሊሉ ፈቃደ ደግሞ፤ «ይህ አሰላለፍ እንደውም ምናልባት ተሐዋሲውን ከመከላከል ይልቅ ሊያስፋፋው ይችላል።» የሚል አስተያየታቸውን በፌስቡክ አጋርተዋል። ግርማው ዋቅጅራ በዚሁ በፌስቡክ ፤ «ሕዝቡ ስለበሽታው ጠለቅ ያለ ግንዛቤ የለውም እየተነገረውም በበሽታው ይቀልዳል። ሚዲያዎች በዚህ ላይ ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።» ነው ያሉት።

በተሐዋሲው ላለመያዝ ከተመከሩት ዋነኛው እጅን አዘውትሮ መታጠብ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተሩ ካሳሰቡ እና መሪዎች ለየዜጎቻቸው አርአያነትን እንዲያሳዩ ከጠየቁ በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አንስቶ ባለሥላጣናት እና ታዋቂ ሰዎች እጅ ሲታጠቡ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በማኅበራዊ መገናኛው ተሰራጭተዋል። ይህን አስመልክተው ፋንታዬ በላይ በፌስቡክ፤ «የመንግሥት እጅ መታጠቢያ ልዩ ነው። ደስ ይላል እናመሰግናለን! ውኃ የለም እንጂ እጅ የመታጠብ ትምህርቱን ወስደናል።» ሲሉ ፍሬው አበበም እንዲሁ፤ «ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሩቅ ሳንሄድ አራት ኪሎ እየኖርን ውኃ በፈረቃ እያገኘን ነው። መጀመሪያ ይህ ይስተካከል!»ሲሉ ጠይቀዋል። መስ ደሞዜ ደግሞ፤ «ውኃ የለም እንጂ ውኃማ ቢኖር እንኳን እጅ ቀርቶ ይታጠባል እግር።» ብለዋል። ናፍቆት አስጨናቂ በትዊተር፤ ፤«ለሚመለከተው ሁሉ» በማለት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የርዳታ ጥሪ አስተላልፈዋል፤ ረዘም ባለው መልእክታቸውም ሰዎች ስለበሽታው የመተላለፊያ መንገድ ግንዛቤ እንዲያገኙ ከማስተማር ጀምሮ ተሐዋሲውን ለመከላከል ይረዳሉ የተባሉትን እያስተባበሩ ማቅረብ፣ ሌሎች ርዳታዎችንም ለማስተባበር በቡድን መነሳታቸውን ገልፀው ሌሎችንም ጋብዘዋል።የዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር በተለይ ለአፍሪቃውያን ያስተላለፉት መልእክት «ተሐዋሲው የማያዳርሰው ሀገር እና የማያሰጋው ሰው የለም ። እናም ከወዲሁ  ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጉ፤» የሚል ነው። «እጅ አንስጥ፤ እጅ እንንሳ» ኮሮና ተሐዋሲን ከእኛ የምናርቅበት አንዱ መንገድ የሚለው የማኅበራዊ መገናኛው የምክር ዘመቻ መሪ ቃል ነው።

ከኮሮና ተሐዋሲ ጋር በተገናኘ የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያ ውስጥ መገለል እና ጥቃቶች እየደረገባቸው መሆኑን የሚገልፁ መረጃዎችን በማኅበራዊ መገናኛው እያካፈሉ ነው። ሌዋና ሉንጉ በትዊተር፤ «ኢትዮጵያዬ ምን እየሆነ ነው? የካፌ ሠራተኞች ለፈረንጆች መታዘዝ አሻፈረኝ ብለዋል፤ ፕሮፌሰሮች ሊሴ ላይ በድንጋይ ጥቃት ደርሶባቸዋል። የሥራ ባልደረባዬ ቦሌ ውስጥ ሁለት ጊዜ ጥቃት ደረሰበት። የጓደኛዬ ፎቶ በፌስቡክ ኮቪድ 19 ይዞታል በሚል በሀሰት ተሰራጭቷል። አሁን በመንገድ ላይ ኮሮና ብለው ይጠሩናል።» በማለት ገጠመኛቸውን አጋርተዋል። የእሳቸውን መልእክት በ,ማጋራት ጴጥሮስ አሸናፊ በፌስቡክ፤ ይህን መስማት ያሳዝናል። እባካችሁ በጋራ ሆነን ይህን ወረርሽኝ እንታገል።» ሲሉ ዮሐንስ ጌታቸው በበኩላቸው፤ «ይህ ተቀባይነት የሌለውና ኢትዮጵያዊ የእንግዳ ተቀባይነታችንን የሚጻረር ነው። ስለበሽታውና ስለሚተላለፍበት መንገድ ሕዝቡን ማስተማሩ በሁሉም ደረጃ መጠናከር አለበት።» በማለት ሃሳባቸውን በፌስቡርክ አጋርተዋል።

ኤድዋርዶ ስቴራሶ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚም አዲስ አበባ ላይ የገጠማቸውን እንዲህ ጽፈዋል፤ «አዲስ አበባ ውስጥ ወደባንክ ሄድኩ፤ ሁለት ሴቶች በፍርሃትና እየሳቁ ከእኔ ሸሹ። ሙስሊሞች ነበሩና በአረብኛ ሊገላችሁ የሚችለው አለማወቃችሁ እንጂ የውጭ ዜጎች አይደሉም አልኳቸው። መኖሪያ ሀገሬ እየሆነ ያለችው በጣም አሳዛኝ ነው።» «እንደሚታወቀው የአስጎብኚ ድርጅት ሾፌር ነኝ።» ያሉት ሶል ዲሞ የሚል የፌስቡክ ስም ያላቸው የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚ ፤ ካለፈው እሁድ አንስተው ለአንድ ሳምንት ጉብኝት ሁለት የስዊድን ዜጎችን ይዘው ወደ ደቡብ ናሞ ለመጓዝ ኮንሶ ሲደርሱ ቱሪስቶቹ የሀገራቸው መንግሥት ዜጎች ከያሉበት ባስቸኳይ እንዲመለሱ በመወሰኑ በመልስ ጉዟቸው ያጋጠማቸውን አጋርተዋል። «አሳዛኙ ገጠመኜ በኮንሶ፣ ሀዋሳና ሻሸመኔ ሆቴል ለመገልገልና ነዳጅ ለመቅዳት በቆምኩበት ሰዓት እንግዶቹ ላይ ሲደርስ የነበረው ስድብና ዘለፋ ጥፍር ውስጥ የሚያስደብቅ ነው። ለነገሩ አውራጃ እና ቀበሌ መርጦ ዘረኝነትን ከሚያቀነቅን ከዚህ በላይ አይጠበቅም።» ሲሉ ተችተዋል። ዶክተር ምህርት ደበበም በትዊተር፤ «እንግዳ ማንጓጠጥና ማጥቃት በባህላችንም በእምነታችንም በሰብአዊነትም ፈጽሞ የወረደ ተግባር ነው። ፍቅር መስጠት ባንችል ጥላቻ ምን አመጣው? በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በውጭ ሀገር እንደሚኖሩ መርሳት አይገባም። ደግነት ለራስ ነው።» ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸውም፤ «የኮሮና ቫይረስ ኮቪድ 19 በሽታ ዘር ቀለም እና ሃይማኖት ሳይለይ የየትኛውንም ሀገር ዜጋ የሚያጠቃ ነው። ይህንን ተገንዝበን ሁላችንም በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ማንንም ሳናገል በመተባበርና በመረዳዳት ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ ልንወጣ ይገባል።» በማለት ማሳሰቢያቸውን በትዊተር አጋርተዋል።

የካትሪን ሀምሊን ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ በወሊድ ጊዜ ባጋጠማቸው የጤና እክል ህይወታቸው ጨልሞ የነበር በርካታ ሴቶችን ኑሮ የለወጡት የፊስቱላ ሆስፒታል መሥራችና የህክምና ባለሙያ ዶክተር ካትሪን ሀምሊንን ህልፈት ይፋ ካደረገ በኋላ በርካቶች የተሰማቸውን ሀዘን፣ እንዲሁም ለ96 ዓመቷ የሰብዓዊነት መገለጫ ያላቸውን አድናቆት ሲገልፁ ተስተውሏል። ከእነዚህ መካከልም ታምራት ኃይሉ፤ «ሩጫቸውን ጨርሰዋል! ሩጫዬን ጨርሻለሁ የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በትክክል ከሚገባቸው ሰዎች መካከል አንዷ ዶክተር ካትሪን ሀምሊን በ96 ዓመታቸው አርፈዋል።» ሲሉ በፌስቡክ ተድላ ኤም ገብረጻድቅም በበኩላቸው፤ «ደግ፣ ርህሩህ፣ የፍቅር እናት ውለታዎን ምንጊዜም አንረሳም። እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን።» ብለዋል። ኤልሳቤጥ ባስሊዮስም እንዲሁ በፌስቡክ ፤« ዶክተር ካትሪን ሃምሊን በኢትዮጵያውያን እናቶች ዘንድ ለዘለዓለም ይታወሳሉ። እግዚአብሔር ይስጥልን እጅግ በጣም እናመሰግንዎታለን። እግዚአብሔር ነፍስዎን ከደጋጎቹ ከአብርሃም እና ይስሀቅ ጎን ያስቀምጥ!» ሲሉ ወንዱ በቀለም በፋንታቸው፤ « ዶክተር ኤሊኖር ካትሪን ሀምሊን በትውልድ አውስትራሊያዊት በምርጫ ደግሞ ኢትዮጵያዊት ሆነው ለየት ባለው ሰብዓዊነታቸው የበርካታ ሺህ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ሕይወት ያሻሻሉ ነበሩ። ሰዎች ለዘለዓለም በምድር ልንኖር አልተፈጠርንም። ሕይወት አንዳንዴ ረዥም ብትመስልም አጭርና ሊያባክኗት የማይገባ ውድ ናት። እኛ ኢትዮጵያውያን ዶክተር ሀምሊን ለተዘነጉት ኢትዮጵያውያን ሴቶች ያደረጉትን ምትክ የለሽ ተግባር እንደማንዘነጋው ተስፋ አደርጋለሁ።» በማለት ዘርዘር ያለ አስተያየታቸውን አካፍለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድም በተመሳሳይ በፌስቡክ፤« በዶክተር ካትሪን ሀምሊን ሕልፈተ ሕይወት ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶኛል። ካትሪን ሀምሊንከ60 ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ክብራቸው የተነጠቀባቸውን በሺህዎች የሚቆጠሩ የሀገሬን ሴቶች ዳግም ቀና ብለው እንዲራመዱ ለፍተዋል።እኒህን ብርቅዬ ጌጥ ኢትዮጵያ አጥታለች። ለሚወዷቸው ቤተሰቦቻቸው፤ ወዳጆቻቸውና የሥራ ባልደረቦቻቸው መፅናናትን እመኛለሁ። ነፍሳቸው በሰላም ትረፍ።» የሚል የሀዘን መግለጫቸውን አስተላልፈዋል።  

 ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች