«ኮሮናና ጥቃት፣ ተማሪዎቹ የትገቡ? ጣናን እንታደግ» | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 05.06.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

«ኮሮናና ጥቃት፣ ተማሪዎቹ የትገቡ? ጣናን እንታደግ»

ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰሞኑ ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ በሁለት ወራት 101 ሕጻናት መደፈራቸውን የአዲስ አበባ ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አልማዝ አብርሃም በመገናኛ ብዙሃን በተካሄደ ጾታዊ ጥቃትን በተመለከተ ውይይት ላይ ገልጸዋል። ይህን በተመለከተ ብዙዎች ቁጭት ቁጣቸውን ያዘለ አስተያየታቸውን በማኅበራዊ መገናኛው አስነብበዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:17

«የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት»

 

የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ከተከሰተና በአብዛኛው ሃገራት ሰዎች በቤታቸው እንዲወሰኑ ካስገደደ ወዲህ በመላው ዓለም የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቆቶች መበራከታቸውን የተመድም ሆነ የዓለም የጤና ድርጅት ይፋ አድርገዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰሞኑ ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ በሁለት ወራት 101 ሕጻናት መደፈራቸውን የአዲስ አበባ ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አልማዝ አብርሃም በመገናኛ ብዙሃን በተካሄደ ጾታዊ ጥቃትን በተመለከተ ውይይት ላይ ገልጸዋል። ይህን በተመለከተ ብዙዎች ቁጭት ቁጣቸውን ያዘለ አስተያየታቸውን በማኅበራዊ መገናኛው አስነብበዋል። ይህን ጠቅሰው ፍሬሕይወት መለሰ በፌስቡክ በሰጡት አስተያየት፤ ለወሲባዊ ጥቃት ከተጋለጡት ውስጥ የ14 እና የ17 ዓመት ሴቶች በአባታቸው የተደፈሩ እና በመጠለያ የሚገኙ መሆናቸውን፤ ከተደፈሩት ሴት ሕፃናት በተጨማሪም 57ቱ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ «ወንድ ልጆች» እንደሆኑ አስታውሰው፤ «እንግዲህ ለሴት ልጅ ከቤትዋ ሌላ መሸሸጊያ ከአባትዋ ሌላ መከታ ከየት ልታገኝ ነው???» የሚል ጥያቄ አቅርበዋል። ትዕግሥት ዋሪዮ በበኩላቸው « ኧረ የምንሰማዉ ሁሉ የሚያም ሆነ። እናት ልጇን ለአባት ጥላ መሄድ ካሰጋት ምንድነዉ ሊሆን የሚችለው? መከታዉ አባት በዓይነቁራኛ የሚታይ ጠላት ከሆነ እናቶች ሆይ መላዉ ምንድነው? ወደ ሕግም ወደ ፈጣሪም ኧረ እንጩህ!» ነው ያሉት። «አባቴ ጠባቂዬ ነው። ገዳዬ መሆን የለበትም።» የሚሉት ሮዝ መስቲካ ደግሞ ፍትህ ይጠይቃሉ፤ «የሕጻናቱ መደፈር ከሪፖርትነት መዝለል አለበት። በሁለት ወራት ውስጥ የተመዘገቡ 101 ሕጻናት ናቸው። ስለዚህ 101ዱ ደፋሪዎች ወደ እስር ቤት ወርደዋል የሚል ዜና መስማት ያስፈልገናል። ሌላው ደግሞ ይቀጥላል።»

ግሩም ተክለሃይማኖትም እንዲሁ ሕጉ ላይ ያተኩራሉ፤ «በሕጻናት እስከመቼ እንዲህ አይነት ግፍ...? አባት የወለዳትን ሕፃን ደፍሮ...ይሰቀጥጣል.... አንዳንዴ ሳስበው ችግሩ ሕጉ ላይ ይመስለኛል። ሰይጣን አሳሳተው ገለመሌ ከሚባለው ውጭ ማለቴ ነው...እንደነዚህ አይነት ሰዎች ሞት ያንሳቸዋል። በእኛ ሀገር ለእንደነዚህ አይነት ዋልጌዎች ሕግ የለም።...ልጆችን የሚደፍሩ ሰዎች የሚቀጡበት ሕግ ሊሻሻል እንደገና ሊታይ ይገባል።»

ኪዳኔ መካሻ ግን ሕጉ አለ ባይ ናቸው፤ « በሕግ ተደንግጓል በወንጀል ሕጋችን መሰረት ከ18 አመት በታች ያሉ ሕፃናት ወንድም ሴትም ለግብረ ስጋ ግንኙነት ፍቃዳቸውን መስጠት አይችሉም። ስለዚህ ከ18 አመት በታች ካሉ ሕፃናት ጋር ፍቃደኛም ሆኑ ተገደው ወሲብ መፈፀም ወይም መሰል የግብረ ስጋ በደል መፈፀም በወንጀል ያስቀጣል።» በጉዳዩ ላይ ትዊተር አስተያየታቸውን ያጋሩት ዶክተር ምህረት ደበበ ደግሞ ፤ «ሕፃን ልጅን መድፈር ፈጣሪን መድፈር ነው! ሕፃንን በስድብና በዱላ ማጥቃት ፈጣሪን መስደብና መደብደብ ነው! ይህንን በሚያደርገው ሰውና ሲደረግ በዝምታ አይቶ እንዳላየ በሚያልፍ አማኝ ነኝ ባይ ማኅበረሰብ መካከል ምንም ልዩነት የለም።» ነው የሚሉት።  እሱባለው ሰሎሞን ደግሞ፤ «ሞራል አልባ ህዝበ እኮ ነን!! ባዘቦት ማንደፍር ይመሰል ኮረና መጠበቁ። ይሄኔኮ ልጁን የደፈረው አባት ጋቢውን አመሳቅሎ/ ጀለብያውን ነስንሶ ቤተ ክርስቲያን ወይም መስጊድ ይሄዳል። ዶር በድሉ ዋቅጅራ እንዳለው የሞራል ልዕልናችን ስላልተገለጠ ነው እንጂ መቀመቅ ገብቷል። የሁሉም ነገራችን ምንጭ እሱ ነው። ልጁን ደፋሪ አባት ያለበት ማኅበረሰብ በብሔር/በሃይማኖት ተቧድኖ ቢሞሻለቅ በፖለቲካ ቢቋሰል አይገርምም። ስናሳፍር!!!» በማለት ትዝብታቸውን በፌስቡክ አጋርተዋል። 

ሌላው የማኅበራዊ መገናኛው መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው የዛሬ ስድስት ወር ገደማ ከደምቢሎዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደቤተሰቦቻቸው ለመሄድ መንገድ ጀምረው መታገታቸው ውሎ አድሮ የተሰማው ተማሪዎች ጉዳይ ነው። አልረሳናቸውም ፤ ይብላኝ በሰቀቀን ለሚገኙ ወላጆቻቸው የሚሉት እነዚህ ወገኖች ግንቦት 24 ቀን ተማሪዎቹ ከታገቱ ስድስተኛ ወራቸውን እንደያዙ በማመልከት የማኅበራዊ መገናኛ ዘመቻ አድርገዋል። በዚህ ተማሪዎቹ የትገቡ? በሚለው የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ዘመቻም በትዊተርና በፌስቡክ ብዙዎች ተሳትፈውበታል።

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል፤  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ The Yellow Movement: የተሰኘው ስብስብ በፌስቡክና ትዊተር ገጹ  የተማሪዎቹን ስም በመዘርዘር ፤ « ስድስት ወራት አለፉ! ልጆቻችን የት ገቡ?  የሎው ሙቭመንት አሁንም ስለ ተማሪዎቹ ግልፅ ምላሽን ትጠይቃለች።» በማለት በዝምታም 140 ቀናት ማለፋቸውን አጽንኦት ሰጥቶ አስታውሷል። «ምንድነው የተፈጠረዉ? ማነዉ ያገታቸዉ? ተማሪዎቹ የታሉ? ምን እያደረጋችሁ ነው?» በማለት በፌስቡክ የጠየቁት ጴጥሮስ አሸናፊ ከበደም «ተማሪዎቹን መልሱልን፤ #ልጆቻችን የትገቡ #Ethiopia» » ሲሉ ጠይቀዋል። ደረጀ ይህዓለም ደግሞ በትዊተር ለተማሪዎቹና ቤተሰቦቻቸው ፍትህ ይላሉ፤ «ፍ-ት-ሕ በማያቁትና በሌሉበት ነገር በአረመኔዎች ታግተው አሰቃቂ መከራ እየደረሰባቸው ላሉ ንፁሃን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፤ ፍ-ት-ሕ ስድስት ወር ሙሉ ማቅ ለብሰው በሰቀቀን ለሚያነቡ ወላጅና ቤተሰቦቻቸው፤ አለንናችሁ እንበላቸው ፤ #BringBackStudents፤ ተማሪዎቹን መልሱልን»
ኖሃ ኤ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ፤ «ተማሪዎቹ የት ገቡ?» ብለው በአጭሩ ሲጠይቁ ጁኒየር ረቡኒ የተባሉት ደግሞ፤ «የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹ መታገታቸው ይፋ ከኾነ ስድስተኛ ወሩን ግንቦት 24 ቀን፣ 2012 ዓም አስቆጥሯል። #ልጆቻችን የት ገቡ? ብዙ ጊዜ ሴት ልጅ ሁሉም ነገር ናት ሲባል እሰማ ነበር ግን ይህ አሁን እውነት አይደለም።» ብለዋል። ዮናስ አበበ በትዊተር፤ «ምስኪን ታጋቾች የደረሱበት ሳይታወቅ ፤ ወላጆች  በሐዘን ብዛት ለበሸታ ታዳርው ፤ ለዜጎች ደህንነት ሐላፊነት ሊወስድ የሚገባው «መንግሥት» (ቡድን) ይህ ነው የሚባል መልስ እንኳ ሳይሰጥ መንፈቅ ሞላ።#ተማሪዎቹ_የት_ገቡ ?? » በማለት ጠይቀዋል።
ምኒሊካዊ ጥቁር ሰው የሚል ስም ያላቸው የትዊተር ተጠቃሚም፤ «እርዳት ያጡ ታጋቾች፣ የምትንሰፈሰፍ በሰቀቀን ያለች እናት፣ ግራ የገባው አቅም ያጣ አባት፤» ካሉ በኋላ ተማሪዎቹ_የት_ገቡ? » የሚለውን ጥያቄ እሳቸውም ደግመዋል።

አንድ ሰሞን ጣና ሐይቅን ከወረረው መጤ የውኃ ላይ አረም ለማጽዳት ይደረግ የነበረው ቅስቀሳ እና የተለያዩ ወገኖች እንቅስቃሴ ያስገኘው ውጤት ምን እንደሆነ ጥያቄ በማቅረብ፤ አሁን ላይ ሐይቁ በተስፋፋበት እንቦጭ ምክንያት ሕልውናው አጠያያቂ መሆኑን የሚያሳስቡ አስተያየቶች እየተሰሙ ነው። ጣናን እንታደግ የሚሉ ወገኖች ወቅታዊውን ይዞታ የሚያሳዩ ፎቶዎችን በመለጠፍ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።  ዓለምጸሐይ ፈንቴ፤ « በጣም ያሳዝናል የተፈጥሮ ሐብት ሲጠፋ ማየት፤  የቱሪስት ስበት የህዝብ መዝናኛ፤ ለገበሬው ለቤተክርስቲያን እረ የስንቱን ውበት ጸጋ የያዘ ነገር እንደቀላል ጸጥ ሲባል።» ሲሉ ቁጭት አዘል አስተያየታቸውን አካፍለዋል።  እንቦጭን በኬሚካል ማጥፋት አይገባም የሚሉት ፍሬህይወት ፌሪ አያይዘው ብዙዎች የሚያነሱትን ጥያቄ ይጠይቃሉ፤ « እንቦጭን ሊያጠፋው የሚችል ኬሚካል ቢኖርም በኬሚካል ማጥፋት አይቻልም ምክንያቱም በዙሪያው ብዙ ህዝብ ለመጠጣት ይጠቀመዋል ሲቀጥል በውስጡ ያሉት አሳዎች ይጠፋሉ ፣ በሰው ጉልበት እንዳይሞከር ኮሮና ምቀኛ ሆኖናል። በዚህ ሁኔታ መፍትሄ ይሆናል ብዬ የማስበው ከዚህ በፊት አረሙን የሚነቅል ሞተር የተገጠመለት ጀልባ ይሁን መኪና ነገር ነበር ከምን ደረሰ?» በማለት፤ የአንተነህ ተስፋዬ አስተያየት ደግሞ ያደረባቸውን ጥርጣሬ ያሳያል፤ « ፣በ24 ሰአታት ውሥጥ አረሙን የሚያጠፋ መድሃኒት አለኝ።" ያለውን ግለሰብ የሚሰማው የጠፋው ለምንድነ ነው ? መንግሥት መድሃኒቱን የቀመምክባቸውን ተክሎች ካልነገርከኝ . . .ብሎ ሚገዳደረው ለምንድን ነው? በአጭሩ መንግሥት እምቦጭ እንዲጠፋ(በአንድም በሌላ ምክኒያት) አይፈልግም።» ፈጠነ ሰይድም ይጠይቃሉ፤ « ሰው ሰራሽ ሐይቅ ለመገንባት ቢሊዮን ብር እየተመደበ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማህፀን የሆነውን የተፈጥሮ ሐይቃችንን ለመታደግ ምነው እጅ አጠረን ?» ዳግም አሰፋ በፌስቡክ፤ « የአማራ ክልል መንግሥት ጣናን ለመታደግ አቅም እንዲሁም ገንዘብ ከሌለው ህዝቡ ገንዘብ እንዲያዋጣ የባንክ አካውንት ይክፈት ዓይናችን እያየ የጣና ሀይቅ እንዲደርቅብን አንፈልግም!!» ሲሉ፤ ኑር ሁሴን በበኩላቸው፤ « የተዋጣው ብር የት ሄደ?» በማለት ይጠይቃሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ 

Audios and videos on the topic