ኮምፒውተርን በቋንቋው የሚያናግሩ ልጃገረዶች | ባህል | DW | 16.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

ኮምፒውተርን በቋንቋው የሚያናግሩ ልጃገረዶች

የአሜሪካን ምክትል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባለቤት ጂል ባይደን ለሁለት ነገር ስሱ ናቸው- ለሴቶች ጉዳይ እና ለትምህርት፡፡ በትምህርት የዶክትሬት ማዕረግ ያላቸው ባይደን ዋይት ሃውስ ገብተው እንኳ የእንግሊዘኛ መምህርነታቸውን አልተውም፡፡ ባለፈው ሐምሌ ወር ወደ ምስራቅ አፍሪካ ለመጓዝ ሲሰናዱም የሴቶችን የትምህርት ዕድል ጉዳይ አንግበው ነበር፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:35
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:35 ደቂቃ

200 ወጣት ሴቶች በ4 ከተሞች ስልጠና ጀምረዋል

ጂል ባይደን ከተጎብኚ ሀገራት አንዷ በነበረችው ኢትዮጵያ ያሉ ወጣት ሴት የኮምፒውተር አሿሪዎች ትኩረታቸውን ስበዉት ነበር፡፡ ወጣቶቹ በዕድሜያቸዉ ሃያ እንኳ ያልደፈኑ ገና ለጋ ቢሆኑም ለብዙዎች ውስብስብ የሚመስለውን የኮምፒውተር ፕሮግራምን መጻፍ የደፈሩ ናቸው - ሊያውም ገና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሳይጠናቅቁ፡፡ ቁጥራቸው አርባ ሲሆን በአዲስ አበባ ከሚገኙ 10 ሁለተኛ ደረጃ እና የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ናቸው፡፡ ፕሮግራሞቹ እንዴት እንደሚጻፉ የሚያሰልጠኗቸውም ቢሆን በዕድሜ ከእነርሱ ብዙም ያልራቁ ወጣት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ናቸው፡፡ ሁሉም ሴቶች ናቸው፡፡

እነዚህን አዳጊ ወጣቶች በአንድ ጥላ ስር ያሰባሰበው ደግሞ በአሜሪካ ኤምባሲ የሚደገፈው “ገርልስ ካን ኮድ” የተሰኘው ፕሮጀክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ዕውን የሆነው ባለፈው ዓመት ጥቅምት ላይ ሲሆን ለዘጠኝ ወር የዘለቀ ወጣቶቹ ተማሪዎች የኮምፒውተር እና ተጓዳኝ ስልጠናዎች እንዲወስዱ፤ እንደዚሁም ሌሎች የህይወት ክህሎቶችን እንዲቀስሙ ያደረገ ነው፡፡ የአሜሪካ ኤምባሲ ሠራተኛ እና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ እምነት መቆያ ስለ ዓላማው እንዲህ ታስረዳለች፡፡ 

“ገርልስ ካን ኮድ ትልቁ ዓላማው ሴት ተማሪዎች  በተለይ ደግሞ ከመንግሥት ትምህርት ቤት ስለሆኑ ብዙውን ወደ ቴክኖሎጂው መግፋት አንዲችሉ ዕድሉን ላላገኙ ተማሪዎች ዩኒቨርስቲ ሲገቡ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ እና ሂሳብ ፍላጎት ኖሯቸው የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን በእነዚህ ላይ መቀጠል እንዲችሉ ማነሳሳት ነው፡፡ [ወደ ትምህርቱ] ከገቡ በኋላ ስኬታማ ሆነው መቀጠል እንዲችሉ፣ ከዩኒቨርስቲ ከወጡ በኋላ ደግሞ በሥራ ሂደትም ቢሆንም ይሁን ሌሎች ሴት ተማሪዎችን በማበረታት ሂደት ቴክኖሎጂውን በቀላሉ ተግባብተው የወደፊት ህይወታቸውን  መቅረጽ እንዲችሉ ነው ዋናው አላማችን” ትላለች የፕሮጀክቱ አስተባባሪ፡፡

ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በተገኘ ጥቂት ገንዘብ ዕውን የሆነው ፕሮጀክት ዳዴ ያለው ከግል ትምህርት ቤት የኮምፒውተር ክፍል ተከራይቶ ነበር፡፡ ዘወትር ቅዳሜ ለግማሽ ቀን ይሰጥ የነበረው ስልጠና ሲጀመር መሠረታዊ የኮምፒውተር አጠቃቀም ግንዛቤን በማስጨበጥ ነበር፡፡ ከቀላሉ የተነሱት ወጣቶች አንድ ኮምፒውተር እንዲሰራ የሚፈልጉትን በቋንቋው እስከማዘዝ ደርሰዋል፡፡ አስገራሚው ነገር ታዲያ ከአርባዎቹ ተማሪዎች ውስጥ ሁለት ወይ ሶስቱ ብቻ ነበሩ በቤታቸው ኮምፒውተር የነበራቸው፡፡ 

በሳምንት አንዴ የሚሰጠው ስልጠና ታዲያ ትምህርትን ብቻ የሙጥኝ ያለ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ለተማሪዎቹ የወደፊት ህይወት ጠቃሚ የሆኑ እንደ አጠናን ዘዴዎች፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ ሰው ፊት ቆሞ የመናገር፣ የቋንቋ ችሎታ ማዳበር እና የአመራር ክህሎቶች የሚቀርቡበት ነበር፡፡ ከውጭም ከሀገር ውስጥም የሚመጡ በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦች የህይወት ልምዶቻቸውን እንዲያካፍሏቸውም ተደርጓል፡፡ 

በአዲስ ከተማ የመሰናዶ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ዊሊ ጠና በፕሮጀክቱ አማካኝነት በስልጠናው ከተሳተፉት አንዷ ናት፡፡ ባለፈው ሐምሌ ወር በተካሄደው የምረቃ ስነ-ስርዓት ከ ጆ ባይደን ባለቤት እጅ የምስክር ወረቀት ተቀብላለች፡፡ ስልጠናው በህይወቷ ውስጥ ለውጥ እንዳመጣም ትገልጻለች፡፡ 

“በዚህ ፕሮጀከት በመሳተፌ በዋናነት የኮምፒውተር ዕውቀቱን አግኝቼያለሁ፡፡ በፊት ስለኮምፒውተር ብዙም አላውቅም፡፡ የመንግሥት ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት፤ [ኮምፒውተርን] እንደ አንድ ክፍለ ጊዜ ነው የተማርነው፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ ከተሳተፍኩኝ በኋላ ግን እስከ ዋናው ፕሮግራም ኮድ እስከማድረግ ድረስ ችያለሁ፡ ይህ ደግሞ ለእኔ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ አንድ ድርጅት ቀጥሮ እንኳ ሊያሰራኝ የሚችልበት ሁኔታ ከተመቻቸ ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት አለኝ፡፡ ሌላው በትምህርቴ ፕሮግራም ለማውጣት፣ ሁሉን ነገር ህይወታችን በዕቅድ እንዲሆን፣ በራስ የመተማመን ክህሎታችን እንዲጨምር ብዙ ነገር አድርገውልናል፡፡ በግሌ ወጥቶ በሰው ፊት መናገር፣ ለህዝብ ንግግር ማድረግ የተለያዩ ስልጠናዎች አግኝቼያለሁ፡፡ እና አሁን እኔ አንድ መድረክ ላይ በሚሰጠኝ ዕድል በሙሉ በራስ መተማመን አንድን ነገር መናገር እችላለሁ፡፡ ይህ በጣም ትልቅ ተጠቃሚነት ነው” ስትል ያገኘችውን ትሩፋት ታብራራለች፡፡ 

ወደ ከፍተኛ ትምህርት የሚያስገባትን ፈተና ለመወሰድ በዝግጅት ላይ የምትገኘው የ18 ዓመቷ ዊሊ ስልጠናውን ጨርሳ አርፋ አልተቀመጠችም፡፡ ከጓደኞቿ ጋር ሆና የወጣት ሴቶች ክበብ አቋቁማ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ግንዛቤን ለማስረጽ እየሞከረች ነው፡፡ ከዚሀ በተጨማሪም ማህብረሰቡን እና ሴቶችን የሚጠቅም ነገር ለመስራት እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡ 

ዩኒቨርስቲ የሚያስገባ ነጥብ ካገኘች ኢኮኖሚክስ ማጥናት እንደምትፈልግ የምትናገረው ዊሊ ከፕሮጀክቱ ያገኘችውን ዕውቀት ከወደፊት ትምህርቷ ጋር አዛምዳ መጠቀም ታስባለች፡፡ ከወደፊት ሙያዋ ጎንም የተለያዩ የኮምፒውተር ፕሮግራሞችና አፕልኬሽኖች የመስራት ዕቅድ አላት፡፡ እርሷ ወደፊት ማጥናት የምትፈልገውን አስቀድማ ብትወሰንም አብረዋት የነበሩ ወጣቶች በስልጠናው ተማርከው ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ፣ ኮምፒውተር ሳይንስ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና ተጓዳኝ ዘርፎች የማጥናት ጉጉት አድሮባቸዋል፡፡ ከእርሷ እና ከአንዲት ሌላ ሰልጣኝ በስተቀር ሁሉም የተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ ተማሪ መሆናቸውም አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ 

እንደ ብዙዎቹ አፍሪካ ሃገራት ሁሉ በኢትዮጵያም የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍን የመረጡ ሴቶች ቁጥር አናሳ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (UNESCO) የሴቶችን የሳይንስ ተሳትፎ አስመልክቶ ከሁለት ዓመት በፊት ባወጣው ዝርዝር ጥናት እንዳመለከተው በበርካታ ሃገራት ሴቶች የማኅበራዊ ሳይንስ ላይ ትኩት አንደሚያደርጉና በኢንጂነሪንግ እና ቴክኖሎጂ ያላቸው ተሳትፎ ከሚጠበቀው በታች እንደሆነ ይጠቁማል፡፡

በዚሁ ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሳይንስ ምርምር ከተሰማሩት ውስጥ የሴቶቹ ድርሻ 12 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህ ቁጥር ወደ ኢንጂነሪንግ እና ቴክኖሎጂ ሲመጣ ወደ ሰባት በመቶ ይወርዳል፡፡ በተማረው ማኅብረሰብ ዘንድ ያለውን የጾታ እኩልነት የፈተሸው የዶክተር ህሊና በየነ ጥናትም ተመሳሳይ ምልከታ አለው፡፡ 

እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በ2013 ሳይንስና ቴክኖሎጂን ለማጥናት  ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከገቡ ኢትዮጵያውያን መካከል ሴቶች 27 በመቶውን ብቻ እንደሚሸፍኑ ጥናቱ ያሳያል፡፡ በተመሳሳይ ወቅት በ13 ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ባሉ የሳይንስና ኢንጂነሪንግ የትምህርት ክፍሎች ውስጥ ያለው የሴት መምህራን ብዛት 20 በመቶ ብቻ እንደሆነ ይፋ አድርጓል፡፡ ለእነዚህ ዘርፎች በሁለተኛ ደረጃ ባሉ ተማሪዎች ዘንድ ያለው አመለካከትም ተመሳሳይ እንደሆነ በመማሪያ ክፍሏ የታዘበችውን ተመርኩዛ ዊሊ ታስረዳለች፡፡ 

“ሴት ተማሪዎች በጣም ይፈራሉ፡፡ ፊዚክስ፣ ሂሳብ ይፈራሉ፡፡ ጭራሹኑ ለመረዳት ሙከራ አያደርጉም፡፡ በእነዚህ ትምህርቶች ጥሩ ውጤት የሚያገኙት አብዛኞቹ ወንዶች ናቸው፡፡ አሁን በክፍሌ ደረጃ ጥቂት ሴት ተማሪዎች ናቸው በእነዚህ ትምህርቶች ጥሩ ውጤት በማግኘት ያለፉት፡፡ በጫና እና ባለማጥናት የተነሳ ነው እንጂ ከወንዶች ያነሰ አቅም የላቸውም” ትላለች፡፡ 

ለዚህ አባባሏ ምስክርነት ለማምጣት ደግሞ ርቆ መሄድ አያስፈልጋትም፡፡ ሳምንታዊ ስልጠና ይሰጧቸው የነበሩ ሰባት ወጣት ሴት አሰልጣኞች አሉላት፡፡ ሁሉም አሰልጣኞቿ በሳይንስ፣ ኢንጂነሪንግ፣ ኮምፒውተር ፕሮግራም መጻፍ እና ኮምፒውተር ሳይንስ ዘርፍ በዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ አሊያም የተመረቁ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዷ ህይወት ቢሻው ትባላለች፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአምስተኛ ዓመት ትምህርቷን እየተከታተለች የምትገኘው ህይወት እርሷም ብትሆን መጀመሪያ ላይ ትፈራ እንደነበር ትናገራለች፡፡  

“መጀመሪያ እንደገባሁ በጣም ነበር የሚያስፈራኝ፡፡ ምክንያቱም በጣም ለቴክኖሎጂ ብዙም [ቅርብ] አልነበርኩም፡፡ ሌሎች ሰዎች ስለተለያዩ ኮምፒውተሮች ይሄ እኮ አንደዚህ ዓይነት ስፔስፊኬሽን፣ ይሄን ያህል ሜሞሪ አለው ሲሉ የኮምፒውተሮቹን ልዩነት እኔ አላውቅም ነበር፡፡ ስገባ በጣም ፈርቼ ነበር ግን እያወቅሁት ስመጣ [ወደድኩት]፡፡ በጣም ደስ የሚለው ጭንቅላትህን እንድታሰራ ያደርግሃል፡፡ ዝም ብለህ አንብበህ የምትተው ነገር አይደለም፡፡ አብዛኛው የምንማረው ነገር ፕሮጀክት ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ስለዚህ  ራሳችን እንድንፈጥር፣ ራሳችንን እና ብዙ ነገሮችን እንድናይ ስለሚረዳን በጣም ነው የወደድኩት” ትላለች ህይወት፡፡

ጅማሬው ቢያስፈራትም አሁን ምረቃ አፋፍ ደርሳ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ወጣት ሴቶች ምሳሌ እና መንገድ አመላካች ሆናለች፡፡ ከትምህርቷ በተጓዳኝ ደግሞ ከጓደኞቿ ጋር ሆና የተለያዩ የኮምፒውተር ፕሮግራሞች ትሠራለች፡፡ ዕውቀታቸውን ወደ ገንዘብ  ለመመንዘር ደግሞ ድርጅት ቢጤ ነገር አቋቁመዋል፡፡ እስካሁን የተለያዩ ድረ-ገጾችን፣ አንድ የትምህርት ቤት አስተዳዳር ተማሪዎቹን እና አስተማሪዎቹን የሚመራበት የኮምፒውተር ስርዓት እና የሙዚቃ መሸጫ አፕልኬሽን እንደሰሩ ትናገራለች፡፡ 

ህይወት በዩኒቨርስቲ ቆይታዋ ትሳትፍባቸው በነበሩ ክበቦች ያገኘችው ልምድ በ“ገርልስ ካን ኮድ” አሰልጣኝነቷ ወቅት እንደጠቀማት ታስረዳለች፡፡ የሰልጣኝ ተማሪዎቹ ጉጉት፣ ነገሮችን ተቀብለው የሚተገብሩበት ፍጥነት እና የማያባሩ ጥያቄዎቻቸው ያስገርማታል፡፡ ይህ ደግሞ ከትምህርቷ ጎን ለስልጠናው ጊዜ መድባ እና በአግባቡ ተዘጋጅታ እንድትመጣ እንዳደረጋት ትገልጻለች፡፡ በፕሮጀክቱ መሳተፏ በእርሷም ህይወት ላይ ለውጥ ማምጣቱንም ታብራራለች፡፡  

“እኔ ስገባ መጀመሪያ ላይ ለምሳሌ ስለሴቶች ይባላል፣ ስለ ሴቶች ይወራል ግን በደንብ አልረዳውም ነበር፡፡ ለምንድነው ይህን ያህል ትኩረት መሰጠት ያስፈለገው? አሁን ከትንንሽ ነገር ጀምር፡፡ እኔ ሶፍትዌር ኢንጂነር ነኝ ብዬ ሳወራ የምቀልድ የምመስለው በጣም ብዙ ሰው አለ፡፡ ሴቶች አይችሉም የሚል አስተሳብ አለ፡፡ እኔም ላይ ብቻ ሳይሆን እነዚያም ልጆች ላይ አየው ነበር፡፡ ይሄ በጣም ትልቅ ችግር እንደሆነ ነው የገባኝ፡፡ እነርሱን ልጆች ለውጧል፡፡ ‘ሴቶች ኮድ ማድረግ ይችላሉ’ ፕሮጀክቱ ስሙ ራሱ እና ልጆቹ ችለው፣ ፕሮጀክት ሠርተው አሳይተዋል፡፡ [ውጤቱ] በእንዲህ አይነት ነገር ላይ ይበልጥ እንድሳተፍ አነሳስቶኛል፡፡ ችሎታዬን ከመጨመር ባሻገር አስተሳሰቤን እንድቀይር አድርጎኛል” ስትል ለውጦቹን ትዘረዝራለች፡፡ 

በእርግጥም ለኮምፒውተር አሠራሮች እንግዳ የነበሩ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ስልጠናቸውን ሲጨርሱ ለህዝብ አገልግሎት የሚውሉ አራት ማሳያዎችን እንካችሁ ብለዋል፡፡ ዊሊ እና የተወሰኑት ሰልጣኞች የነበሩበት “ፋኖ” የተባለው ቡድን ለተማሪዎች የሚጠቅም ያለምንም ክፍያ አገልግሎት የሚሰጥ ድረ-ገጽ ነበር የሠራው፡፡ ድረ-ገጹ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በሚገቡ ጊዜ የሚያጠኗቸውን የትምህርት ዘርፎች በመለየት ረገድ የሚያጋጥማቸውን ችግር የሚቀርፍ ነው፡፡ 

በ40 ተማሪዎች አዲስ አበባ ላይ የጀመረው ፕሮጀክት ከዚህ ወር ጀምሮ የሚያቅፋቸው ተማሪዎች ብዛትን ወደ 200 አሳድጎ በተጨማሪ አራት ከተሞች ቅርንጫፎችን ከፍቷል፡፡ ድሬዳዋ፣ ባህርዳር፣ መቀሌ እና ጅማ ያሉ ወጣት ሴቶች ኮምፒውተርን በቋንቋው ለማናገር ስልጠናቸውን ጀምረዋል፡፡

ጂል ባይደን እንዲህ ዓይነት ፈር ቀዳጅ ትምህርቶችን የሚያገኙ ሴቶች ምን ሊያመጡ እንደሚችሉ ለምረቃ በተጠሩ ጊዜ ባደረጉት ንግግር ጠቆም አድርገው ነበር፡፡ የቤኒን ተወላጇን የግራሚ ሽልማት አሸናፊ ዘፋኝ አንጀሊክ ኪጆን ቃላት ተውሰው እንዲህ ብለው ነበር፡፡ “ከተማሩ ህብረተሰባቸውን ያስተምራሉ፡፡ ጤናማ ከሆኑ ሌሎች ጤናማ ሆነው እንዲያድጉ ያደርጋሉ፡፡ ብቃት እንዲኖራቸዉ ከተደረገ ዓለምን ይቀይራሉ”፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ    
 

Audios and videos on the topic