ኮል እና ፖለቲካዊ ህይወታቸው  | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 20.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

 ኮል እና ፖለቲካዊ ህይወታቸው 

ኮል ሁለቱን ጀርመኖች ለውህደት በማብቃት ብቻ ሳይሆን የተዋሀደችው ጀርመን በቀድሞ ታሪኳ ምክንያት በጎረቤቶቿ በፍራቻ ከመታየት ይልቅ እምነት የሚጣልባት ወዳጅ እንድትሆን ለማድረግ እና ተጠራጣሪዎችንም ለማሳመን የበቁ ታላቅ አውሮጳዊም ናቸው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:50

ኮል እና ፖለቲካዊ ህይወታቸው


«የጀርመን ውህደት አባት» በመባል ይጠራሉ፤ታላቁ የጀርመን ፖለቲከኛ እና የአውሮጳ የክብር ዜጋ ሔልሙት ኮል። ከፍራንክፈርት በስተደቡብ በምትገኘው እና በተወለዱባት ሉድቪክስሀፈን በተባለችው ከተማ ባለፈው ሳምንት አርብ በ87 ዓመታቸው ያረፉት ሔልሙት ጆሴፍ ሚሻኤል ኮል የሚታወሱት በጀርመን ውህደት ብቻ አይደለም። ለአውሮጳ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ ህብረት ባበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦም ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል። ጀርመን የተማሩት እና የሚኖሩት የታሪክ ምሁር ደራሲ እና የአፍሪቃ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች አማካሪ ዶክተር ልጅ አስፋወሰን አሥራተ ካሳ ታላቁን ፖለቲከኛ ኮልን ታሪክ በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ያስታውሳቸዋል ይላሉ። ኮል ሁለቱን ጀርመኖች ለውህደት በማብቃት ብቻ ሳይሆን የተዋሀደችው ጀርመን በቀድሞ ታሪኳ ምክንያት በጎረቤቶቿ በፍራቻ ከመታየት ይልቅ እምነት የሚጣልባት ወዳጅ እንድትሆን ለማድረግ እና ተጠራጣሪዎችንም ለማሳመን የበቁ ታላቅ አውሮጳዊም ናቸው። ኮል በአንድ ወቅት እንዳሉት በርሳቸው እምነት የአውሮጳ አንድነት ለጀርመን ጠቃሚ ምርጫ ነው ።

«ለኛ ለጀርመኖች የአውሮጳ አንድነት መርህን ይዞ መቀጠል የወደፊት እጣ ፈንታችንን እኛነታችንን ወደ መጥፎ አቅጣጫ ያመራዋል ተብሎ የሚያከራክር ግልፅ ምክንያት አይኖርም ። የአውሮጳ አንድነት መርህ ከመከተል ውጭ ሌላ አሳማኝ አማራጭ አይኖረንም ። »
ከአራት አሥርት ዓመታት በላይ ጀርመን የኖረው የዶቼቬለ የበርሊን ዘጋቢ ይልማ ኃይለ ሚካኤል ኮልን ታላቅ መሪ ነው የሚላቸው። ለዚህም በአብነት የሚያነሳው ለአውሮጳ ህብረት እና ጀርመን በህብረቱ ተሰሚነት እንድታገኝ ያበረከቷቸውን አስተዋጽኦዎች ነው። ይልማ እንደሚለው ሁለቱ ጀርመኖች ከተዋሀዱ ኃይላቸው ይጠናከራል ብሄረተኛም ይሆናሉ የሚለውን ስጋት ኮል ማለዘብ ችለዋል። ለመሆኑ የኮል አውሮጳዊነት እንዴት እና ከየት መጣ? ዶክተር አስፋወሰን ያስረዳሉ።
 ለ25 ዓመታት የመሩት፣ የጀርመን ወግ አጥባቂ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት ፓርቲ አባል የሆኑት ገና የ17 ዓመት ወጣት ሳሉ ነበር። ለመጀመሪያ ዲግሪያቸው እና በኋላም ለዶክትሩት ዲግሪያቸው ታሪክ ህግ እና የመንግሥት አስተዳደር እንዲሁም የህዝብ መርህ በሚያጠኑበት ወቅት በፖለቲካው ንቁ ተሳታፊ ነበሩ። በ29 ዓመታቸው በምዕራብ ጀርመንዋ የራይንላንድ ፋልስ ፌደራዊ ክፍለ ሀገር ፓርላማ አባል ከ4 ዓመት በኋላ በፓርላማው የፓርቲያቸው ሊቀመንበር ለመሆን በቁ። ለኋለኛው ሃላፊነት በመብቃት እና ከሦስት ዓመት በኋላም የፌደራል ክፍለ ሀገሩ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን በእድሜ ትንሹ ፖለቲከኛ ነበሩ። የኮል የፖለቲካ ህይወት

ስኬት በዚህ ሳያበቃ በጎርጎሮሳዊው 1973 የክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት ፓርቲን ሊቀመንበርነት ሥልጣን ያዙ። ከዚያን ጊዜ አንስቶም ምኞታቸው መራሄ መንግሥት መሆን እንደነበር ያሳውቁ ነበር። በ1976 ተወዳድረው ባይሳካላቸውም ከ6 ዓመት በኋላ በጎርጎሮሳዊው ጥቅምት 1982 ምኞታቸው እውን ሆነ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ለ16 ዓመታት በመራሄ መንግሥትነት አገልግለዋል። በፌደራል ጀርመን ታሪክ ይህን ያህል ጊዜ ሥልጣን ላይ በመቆየት 6 ተኛው የጀርመን መራሄ መንግሥት ሄልሙት ኮል የመጀመሪያው መሪ ናቸው። ዶክተር አስፋወሰን ያስረዳሉ። በኮል የመጀመሪያዎቹ የሥልጣን ዘመናት የጀርመን ዓመታዊ እዳ ቢሽቆለቁልም የሥራ አጡ ቁጥር መጨመር አብይ ችግር ነበር ። ይህ ቅሬታ አስነስቶ በ1987 ጥሩ የሚባል ውጤት አላስገኘላቸውም ሆኖም የጀርመን ውህደት የ1990ውን ምርጫ ለማሸነፍ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖላቸዋል። ያያኔው የሶቭየት መሪ ሚኻኤል ጎርባቾቭ በጎርጎሮሳዊው 1980 ዎቹ መጨረሻ ለውጥ እና ግልጽነት ብለው የጀመሩት የፖለቲካ መርህ ለኮል ጠቅሟል። በ1989 ጎርባቾቭ ቦን ከመጡ በኋላ ሁኔታዎች በፍጥነት ይለዋወጡ ያዙ። ብዙም ሳይቆይ የበርሊን ግንብ ፈረሰ

ኮልም ጊዜ ሳያጠፉ ሁለቱ ጀርመኖች የሚዋሀዱበትን ባለ 10 ነጥብ እቅድ አቅርበው ምስራቅና ምዕራብ ጀርመን የዛሬ 27 ዓመት ተዋሀዱ። ይሁን እና ከውህደቱ በኋላ ያበበው የሥራ እድል ብዙም አለመዝለቁ እን የሥራ አጡ ቁጥር መጨመሩ በ1994 ቱ ምርጫ ሊሸነፉ ይችላሉ የሚል ስጋት ቢያሳድርም ማሸነፍ ቻሉ። በቀጣዩ በ1998 ቱ ምርጫ ተሸንፈው ከ16 ዓመታት ሥልጣን በኋላ ከመሪነት ወርደው በጀርመን ፓርላማ የተቃዋሚዎችን ቦታ ያዙ። በዓመቱ ግን በሥልጣን ዘመናቸው ከህግ ውጭ በሚስጥር የባንክ ሂሳብ ለፓርቲያቸው የገንዘብ እርዳታ ተቀብለዋል የሚል በኮል ታሪክ ጥቁር ነጥብ ጥሎ ያለፈ ዜና ተሰማ። መጀመሪያ ላይ ድርጊቱን ያስተባበሉት ኮል በኋላ ድርጊቱን አምነዋል። ይሁን እና የገንዘብ ለጋሾቹን ማንነት ይፋ ለማድረግ ሳይፈቅዱ ከሃላፊነታቸው ተነስተዋል። ሔልሙት ኮል በሚስጥር የተቀበሉት የገንዘብ እርዳታም በፓርቲያቸው ላይ ልዩ ልዩ መዘዞችን ማስከተሉን ይልማ ያስታውሳል። ኮል ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከጀርመን ፖለቲካ ተገለው ቆዩ። ታላቁ ጀርመናዊ እና አውሮጳዊ ኮል ባለፈው አርብ በ87 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት ፓርቲ መሪ የጀርመን መራሂ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ኮልን እንደ ታላቅ

አውሮጳዊ እና እንደ የውህደት መራሄ መንግሥት ስናስታውሳቸው እንኖራለን ብለዋል። ሜርክል ኮል የርሳቸውን ጨምሮ የሚሊዮን ጀርመናውያንን ህይወት መለወጣቸውን አስታውሰዋል።
«ሔልሙት ኮል ለኛ ለጀርመኖች ከእግዚአብሔር የተላኩልን ሰው ነበሩ። ሔልሙት ኮል የኔንም ህይወት ቀይረዋል። እንደ ሌሎች ሚሊዮኖች የ«GDR»ን አምባገነን ህይወት አምልጬ የነፃነት ህይወት ማግኘት ችያለሁ። ካለ ፍርሀት እና ካለ ቋሚ ክትትል መኖር መጀመር ችያለሁ። ከዚያም በኋላ በተከተሉት 27 ዓመታት የሆነው ሁሉ ካለ ሔልሙት ኮል የሚታሰብ አልነበረም።» 
የጀርመናውያን ብሎም የአውሮጳውያን ባለውለታ ከሆኑት ከኮል የፖለቲካ ህይወት ኢትዮጵያውያን የምንማረው አለ ይላሉ ዶክተር አስፋወሰን አሥራተ ካሳ ። 


ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic