ኮህለርና ለአፍሪቃ አጋርነት ፕሮዤ፤ | አፍሪቃ | DW | 05.11.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ኮህለርና ለአፍሪቃ አጋርነት ፕሮዤ፤

በጀርመኑ ፕሬዝደንት ኾርስት ኮኽለር አነሳሽነት የተጀመረዉ አጋርነት ከአፍሪቃ ጋር የተሰኘዉ ፕሮዤ ሶስተኛ ጉባኤዉን በሳምንቱ ማለቂያ አካሄደ።

ኮኽለርና ተሳታፊዎች

ኮኽለርና ተሳታፊዎች

በአገራቸዉ የፖለቲካ ተግባር ዕለት ተዕለት ያልተጠመዱት ፕሬዝደንት ኮኽለር ድህነትን ከአፍሪቃ ለማጥፋት ለሚደረገዉ ጥረት ሰፊ ጊዜያቸዉን መስጠታቸዉ ይነገራል። የአፅናፋዊ የንግድ ትስስር ማለትም Globalization እዉን ሆኖ ሁሉን እንዲጠቅም በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አጋርነት በየደረጃዉ ይኑር በሚለዉ አቋማቸዉ ፕሬዝደንቱ ይታወቃሉ።
«እኔ እንደማምነዉ ለታለመዉ ነገር ሁሉ በአፅናፋዊ የንግድ ትስስር ልንጎዳኝ የምንችለዉ በእኩልነት ላይ በተመሰረተ አጋርነት መኖርና መስራት ስንችል ነዉ።»
አጋርነት ከአፍሪቃ ጋ የተሰኘዉ ፕሮዤ አላሚና አንቀሳቃሽ የጀርመን ፕሬዝደንት ሆርስት ኮኽለር ጉባኤዉን በከፈቱበት ወቅት የተናገሩት ነዉ። ምንም እንኳን አሉ ኮኽለር ምንም እንኳን ዓለም ዓቀፉ ግንኙነት እየጠበቀና እየተጠናከረ የሄደ ቢመስልም አንዳችን ስላንዳችን የምናዉቀዉ እጅግ ዉሱን ነዉ። ስለዚህ ጀርመንም ሆነች ሌሎች ሀገራት ከአፍሪቃ አቻዎቻቸዉ ጋ ተቀራርበዉ አንዳቸዉ ስለሌላዉ መረዳት እንደሚያስፈልግ ፕሬዝደንቱ ጠቁመዋል።
ፕሮዤዉ እንቅስቃሴዉን ከጀመረ ሁለተኛ ዓመቱን መያዙ ነዉ። ልክ የዛሬ ሁለት ዓመት እዚህ ቦን የተካሄደዉና የአፍሪቃ ሀገራት ፕሬዝደንቶች፤ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፤ የቀድሞ መሪዎች፤ እንዲሁም ከአዉሮፓና ከአጎራባች አህጉራት ጋዜጠኞች የተጋበዙበት የልምድ ልዉዉጥ መድረክ የመጀመሪያዉ ጉባኤ ነበር። በጉባኤዉም በአፍሪቃና በኢንዱስትሪ የበለፀጉት ሀገራት ግንኙነት የሚፈጥሩበትን መንገድ በተመለከተ ግልፅ ዉይይት ተካሂዷል። በወቅቱም ከተነሱት መካከል አፍሪቃ ችግሮቿን በራሷ መንገድ ለማስወገድ ምን መስራት እንዳለባትና የበለፀጉት ሀገራትስ ያንን ለማገዝ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል በሚል ያነጋገረዉ ይጠቀሳል። ቀድሞ ዓለም የገንዘብ ተቋም IMF የበላይ የነበሩት ኮኽለር ገና የመንግስት ስልጣን ይዘዉ ፕሬዝደንት ሲሆኑ በልባቸዉ የነበረዉን ለአፍሪቃ ልዩ ትኩረት የመስጠት ፍላጎት በግልፅ አሳይተዋል። ለእኔ አሉ በጀርመን ቡንደስታኽ ማለትም ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ላይ «ለእኔ የዓለም ህዝብ ሰብዓዊነት የሚለካዉ የአፍሪቃ መፃኤ እድል ሲሻሻል ነዉ።» ማለታቸዉ ይጠቀሳል። በዚህ መሰረትም ኮኽለር አዉሮፓና አፍሪቃ የሚነጋገሩበትን መድረክ ለማመቻቸት ግፊት ያደርግ ዘንድ ከአፍሪቃ ጋ አጋርነት የተሰኘዉን አዲስ ፕሮዤ ጀመሩ።
«ግቡ ለእኔ፤ አፍሪቃዉያንን የራሳቸዉን ጉዳይ ሲነግሩን የራሳችን የሆነ የተሳሳተ ግንዛቤ ሳንይዝ እንድናዳምጣቸዉና ያንንም እነሱ እንዲለምዱት የሚል ነዉ። እዉነታዉ ራሳችንን ከላይ አድርገን ወደታች ልናያቸዉ፤ ወይም እነሱ ከታች ወደላይ ሊያዩን አይገባም። ይልቁንም በዚች ፕላኔት የጋራ እጣ ፈንታ እንዳለን ሁላችንም በመግባባት አንዳችን ሌላችንን መረዳት ይኖርብናል።»
ከመጀመሪያዉ ጉባኤ በኋላም የተነሱለት ዓላማ ግልፅ እዉነታ በመሆኑ ተሳታፊዎቹ ወደዉት የተጨበጠ ርምጃ ላይ ለመድረስ በቀጣይ ምንመስራት አለብን የሚል ሃሳብ ላይ ደረሱ። በወቅቱ ኮኽለር ይህን አላሰቡም ነበር። ከ14 ወራት በኋላም ዳግም በጋናዋ መዲና አክራ ላይ ተሰባሰቡ። ተሳታፊ የነበሩት የየአፍሪቃ ሃገራቱ መሪዎች በስሜት ለአህጉሪቱና ለህዝቦቿ የተሻለ ቀን ለማምጣት ዴሞክራሲያዊ የሚለዉ ሃሳብ ላይ ትኩረት አደርገዉ ተነጋገሩ። ኮኽለር አሁንም አንድ ሃሳብ አመጡ፤ ከአፍሪቃ ሀገራትና ከጀርመን በጥቅሉ 50 ወጣቶች በጉባዉ እንዲሳተፉ ማድረግ። ይኽም የየአገራቱ መሪዎች የነገዉ ሃላፊነት ተረካቢ ከሆኑት ወጣቶች ጋ በግንባር ስለጋራ ጉዳያቸዉ እንዲነጋገሩ መንገድ ፈጠረ። ስለመልካም አስተዳደር፤ የየአገራቱ መንግስታት ተገቢዉን ሃላፊነታቸዉን እየተወጡ እንደሆነና የተያያዙ ነጥቦች በጋና በተደረገዉ ዉይይትም ወጣቶቹ ጥሩ ጥሩ ነጥቦች እያነሱ ከመነጋገር ባሻገር መሪዎቻቸዉን በጥያቄ ሲያፋጥጡ መታየቱ ታዛቢዎችን ያስደነቀ ነበር። በዘንድሮዉ ጉባኤ ደግሞ 44 ከፍተኛ ባለስልጣናትና ምሁራን የተሳተፉ ሲሆን አፅናፋዊ የንግድ ትስስርን በተመለከተ ለተጋረጠዉ ችግር አፍሪቃና ጀርመን ምላሽ የፈለጉበት ደማቅ ዉይይት ተካሂዷል። የናይጀሪያዉ ፕሬዝደንት ዑማሩ ኤም ያራዱዋ ይኸዉ ጉዳይ አፍሪቃ ላይ ስለሚኖረዉ ተፅዕኖ ማብራሪያ አቅርበዋል። እዚህ ጀርመን ለፍራንክፈር ከተማ በምትቀርበዉ ጥንታዊቷ ኤልትፊለ ከተማ ቅዳሜ ዕለት በተከፈተዉ ጉባኤ የተሳተፉት የናይጀሪያ፤ ሞዛምቢክ፤ ቦትስዋናና ቤኒን ፕሬዝደንቶች ናቸዉ።