ክትባትና የዕድሜ ገደብ | ጤና እና አካባቢ | DW | 09.05.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ክትባትና የዕድሜ ገደብ

የተለያዩ በሽታዎችን በክትባት መከላከል ሲቻል የበርካቶች ሕይወት እንደሚቀጠፍ የዓለም የጤና ድርጅት በየጊዜዉ በሚያወጣቸዉ መረጃዎች ያሳስባል። ይህን መሠረት በማድረግም በየዓመቱ በአዉሮጳ «የአዉሮጳ የክትባት» ሳምንት ይታሰባል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:05

ከተቻለ በየጊዜዉ መከተብ ይመከራል፤

በጎርጎሪዮሳዊዉ የቀን መቁጠሪያ መሠረት ከሚያዝያ 24 እስከ 30 ወይም በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከሚያዝያ 16 እስከ 22 ድረስ በአዉሮጳ የክትባት ሳምንት በመባል ይታወቃል። በዚህ ሳምንትም በየዕድሜ ደረጃዉ ሰዎች ሊወስዱት ስለሚገባቸዉ የክትባት አስፈላጊነት ግንዛቤ እንዲኖራቸዉ በየመገናኛ ብዙሃኑ ሲቀሰቀስ መረጃዎችም ይሰራጫሉ። አፍሪቃም ተመሳሳይ የክትባት ግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት እንዳላት በኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶች እና ሕጻናት ዘርፍ ረዳት ዳይሬክተር እና የክትባት ጉዳዮች ቡድን አስተባባሪ ወ/ሮ ሊያ ወንደሰን ገልጸዉልናል።

በኢትዮጵያ ይህ የሚከናወነዉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲሆን የዘንድሮዉን የክትባት ሳምንት በኦሮሚያ ክልል በፍቼ ከተማ የተከበረ ሲሆን በርካታ ሕጻናት በዚህ ወቅት መከተባቸዉንም ገልጸዉልናል ወ/ሮ ሊያ። በተጠቀሰዉ ሳምንት የሚከናወነዉም ለመደበኛ ክትባቱ መርሃግብር  እንደተጨማሪ ድጋፍ የሚወሰድ መሆኑም አብራርተዋል።

Schweinegrippe - Impfung

የተመ የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለዉ በመላዉ ዓለም 86 በመቶ የሚሆኑ ሕጻናት እስከ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2015 ድረስ መንጋጋ ቆልፍን፣ ትክትና አናዳን ለመከላከል ተከትበዋል። እንዲያም ሆኖ 19,4 በመቶ የሚሆኑት አሁንም ክትባት ማግኘት አልቻሉም። ኩፍኝን መከላከል የሚያስችለዉን ክትባት ባለማግኘታቸዉም በየዓመቱ 134 ሺህ ልጆች እንደሚያልቁ የዓለም የጤና ድርጅት ያመለክታል። ኢትዮጵያ ዉስጥ ክትባት የማዳረሱ ጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል ይላሉ ወ/ሮ ሊያ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 1980ዓ,ም ነዉኢትዮጵያ ዉስጥ ክትባት መስጠት የተጀመረዉ። ያኔ በትንሹ የተጀመረዉ የክትባት መርሃግብር አሁን ቁጥሩ ከፍ ብሏል።

በክትባት መከላከል ከሚቻሉ በሽታዎች መካከል ለምሳሌ ኩፍኝ በቀላሉ ማስነጠስ፣ በሳል እንዲሁም በትንፋሽ ሊተላለፍ የሚችል በሽታ ነዉ።

UNICEF, Impfen in Indonesien

ተሐዋሲዉ ከታመመዉ ሰዉ ወደጤነኛ ሰዉ ገብቶ ጥቃት ሲያደርስ ከፍተኛ ትኩሳት እና ቆዳ ላይ የሚወጣ ሽፍታ ያስከትላል። የበሽታዉ መከላከያ ክትባትም ሕይወት ያለዉ ተሐዋሲ ነዉ። የኩፍኝ ክትባትን ከ11 እስከ 14 ወራት የሆናቸዉ ሕፃናት ለመጀመሪያ ጊዜ መከተብ ይኖርባቸዋል፤ ከ15 እስከ 23 ወራት ሲሆናቸዉ ደግሞ በድጋሚ እንዲከተቡ ማድረግ ይገባል። ሀኪሞች ከታማሚዉ ሰዉ ጋር በሚኖር ቀጥታ መነካካት ወይም ከታማሚዉ የወጡ ፈሳሾችን በመንካት እንደሚጋባ የሚናገሩለት ጆሮ ደግፍም መከላከያ ክትባትም በተመሳሳይ የዕድሜ ደረጃ በተደጋጋሚ ጨቅላ ሕፃናት ማግኘት አለባቸዉ። መንጋጋ ቆልፍ በአፈርና የእንስሳት ፍግ ምክንያት ባክቴሪያ የሚያመጣዉ የጤና ችግር ነዉ። በሽታዉ ሲከሰት የሰዉነት መረበሽ፣ የራስ ምታት እና ላብ ያስከትላል። ሲባባስ ደግሞ የመተንፈሻ አካላትን ጡንቻዎች ሽባ ያደርጋል። ልጆች ለዚህ በሽታ እንዳይጋለጡ በለጋ ዕድሜ የመጀመሪያዉን ክትባት መዉሰድ ይኖርባቸዋል። ከፍ ሲሉ ደግሞ እስከ 17ዓመት ድረስ እንዲከተቡ ይመከራል። ተገቢዉን ክትባት ሳያገኙ ቀርቶ ለበሽታዉ የሚጋለጡ ታማሚዎች መካከል ከ20 እስከ 50 በመቶ የሚሆኑትን እንደሚገድል የዓለም የጤና ድርጅት ያሳስባል። 

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic