ክብካቤ የሚያሻት መሬት | ጤና እና አካባቢ | DW | 24.04.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

ክብካቤ የሚያሻት መሬት

በየዓመቱ በጎሮጎሮሳዊዉ ቀን አቆጣጠር ሚያዚያ 22 ቀን ላይ ይታሰባል የመሬት ቀን። ይህ ከእምነት ጋ የማይገናኝ በዓል ሲከበርም 43ኛ ዓመቱን ይዟል። አነሳሱ ሰዎች ለአካባቢ ተፈጥሮ ትኩረት እንዲሰጡና ተፈጥሮን እንዲከባከቡ በሚል ነዉ።

በጎርጎሮሳዊዉ 1970 ዓ,ም ወደሁለት ሺህ የሚገመቱ የዩናይትድ ስቴትስ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች፤ አስር ሺ ገደማ የሚሆኑ ከአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተዉጣጡ ተማሪዎች እንዲሁም በመላ ሀገሪቱ በመቶዎች የተገመቱ የማኅበረሰብ አባላት የመጀመሪያዎቹ የመሬት ቀን በዓል አክባሪዎች መሆናቸዉን መረጃዎች ያመለክታሉ። ዓላማቸዉም ሰዎች ተፈጥሮን መከባከብ ጠቀሜታ የሚያስገኙትን መንገድ እንዲያስተካክሉ፤ ሁሉ ከእሷ ሁሉ ወደእሷ የሆነችዉ መሬት ጥንቃቄ እንደሚያስፈልጋት ማሳሰብ ነዉ።

ስለመሬት ሲታሰብ መሬት የተሸከመችዉ እና ለሰዉ ልጅ ጥቅም የሚዉለዉ የተፈጥሮ ሃብት ሊደረግለት የሚገባዉ ጥንቃቄ ይታሰባል። የደን መራቆት መሬት ለንፋስና ጎርፍ እንዲጋለጥ ማድረጉ የሚታይ ነዉ። በለያዩ አካባቢዎች የሚከናወነዉ የደን ምንጠራ የመሬቱ ለምነት በአንድም በሌላ መንገድ እንዲቀንስ እንደሚያደርግ ባለሙያዎች ያሳስባሉ። የተራቆተ እና ለምነቱ የከዳዉን መሬት ከንክኪ በመከለል እንዲያገግምና እንዲለወጥ የሚደረጉ ጥረቶች አንዳንድ አካባቢ ለዉጥ እንዳመጡ ይነገራል። በአርሲ ነገሌ የአርሲ የአካባቢ ልማት ድርጅት በሚንቀሳቀስበት የስምጥ ሸለቆ አካባቢ ተፈጥሮን የመከባከብ ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ ለመረዳት ችለናል።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደቀቦ ዳሌ ቱፌ ከአካባቢዉ መንግስት ጋ በመሆን ማኅበረሰቡን በማስተባበር የተከናወኑት ተግባራት ዉጤት ማሳየታቸዉን ይናገራሉ። ከዚህም ሌላ ይላሉ አቶ ደቀቦ ህዝቡ ከመሬቱ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሥራም እየተሠራ ነዉ። እሳቸዉ እንደሚሉትም በአሁኑ ወቅት የአካባቢ ተፈጥሮን ለመከባከብ ህዝብ ያሳተፈ ህዝባዊ ንቅናቄ ተፈጥሯል። የእሳቸዉ ድርጅት ማኅበረቡን አስተባብሮ የአፈር እቀባ፤ የደን ተከላ፤ አካባቢን ከሰዉና እንስሳ ንክኪ በመከላከል እንዲያገግም ጥረት እያደረገ ነዉ። በዚህ ሂደትም ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድም ለማመቻቸት እየተሞከረ ነዉ። የመሬትን መራቆት ከሚከላከሉ ስልቶች አንዱ መሬቱን በተክል መሸፈን እንደመሆኑ በየተለያዩ ጊዜያት በዘመቻም ሳይቀር ዛፎች እንደሚተከሉ ይሰማል ይታያል።

Nomadin hütet Ziegen in Äthiopiens Krisenregion Ogaden

እነዚህ ዛፎች እንኳን ስለማደጋቸዉ ስለመጽደቃቸዉም ቢሆን ተከታትሎ ዉጤታቸዉን የሚገልፅ ብዙ የለም። የአርሲ የአካባቢ ልማት ድርጅት በሚንቀሳቀስበት አካባቢ በየዓመቱ የሚተከሉ ችግኞች ባለቤት እንዲኖራቸዉ የማድረግ ስልትን በመከተሉ ከሚተከሉት ችግኞች ሰማንያ በመቶዉ መጽደቁን ነዉ አቶ ደቀቦ የገለፁልን።

የችግኝ ተከላዉ በአንድ አካባቢ ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ ይታወቃል። ዋና ከተማ አዲስ አበባ ለረዥም ጊዜያት የዘመቻ ችግኝ ከሚተከልባቸዉ አካባቢዎች አንዷ ናት። እንደሚተከሉት ችግኞች ብዛትና እንደአየር ንብረቱ ተስማሚነት ከተማዋ አረንጓዴ ትሆን እንደነበር የሚገምቱ በርካቶች ናቸዉ። ግን ያ አይታይም። ዛሬ እንደዉም የጠዋት ፀሐይ ሳይቀር መግቢያ የሚያሳጣባት መሆኗ ነዉ የሚነገረዉ። ለአካባቢ ተፈጥሮ ከሚሟገቱ ወገኖች አንዱና በአካባቢ ተቆርቋሪዎች መድረክ በሥራ አስካሄያጅነት የሚያገለግሉት አቶ ዮናስ ገብሩ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚተከሉት ችግኞች ክትትል እንዳሚያሻቸዉ ነዉ የሚጠቁሙት።

ዋና ከተማ አዲስ አበባ ከሚታየዉ የሕንፃ ግንባታና የመንገድ ሥራዎች አንጻር ለአረንጓዴ ቦታዎቿ ትኩረት የተሰጠ አይመስልም የሚሉ ወገኖች አሉ። ህንፃና መንገዱ ለከተማዋ እድገት አስፈላጊ መሆናቸዉ ባይካድም በዚያ ላይ ዛፎች ቢኖሯት ለዉበቷ ብቻ ሳይሆን ለአየር ንብረቷም ጉልህ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉም ይታመናል።

ለመሬት ቀንን ለይቶ ጥቅም አገልግሎቷን ብሎም የሰዉ ልጅ ለኑሮዉ የሚሻዉን እንደልቡ እንዲያገኝ ተገቢዉን ክብካቤ እንዲያደርግላት ማሳሰብ በአሜሪካን ግዛቶች ተጀምሮ ዛሬ የዓለማችን 192 ሀገሮች እንዲዘክሩት ሆኗል። መሬት በእናት ትመሰላለች፤ እናት የህይወት ምንጭ ብቻ ሳትሆን፤ ተሸካሚና ሁሉን ቻይነቷም ከመሬት ያመሳስላታል። መሬትን መከባከብ በደህነቷ የራስን ህልዉና ማረጋገጥ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚደረገዉ ክብካቤ ምን ይመስላል። ያድምጡ።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic