ክሰል እና ደን ምንጠራ በዛምቢያ | አፍሪቃ | DW | 10.09.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ክሰል እና ደን ምንጠራ በዛምቢያ

በደቡብ አፍሪቃዋ ደርባን ከተማ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 14ኛው የዓለም ደን ተመልካች ጉባኤ ሰኞ ጳጉሜ 2 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. ተከናውኗል። ጉባኤው ያተኮረው የዓለም የደን ይዞታዎች ምንጠራ በከባቢ አየር እና በሰው ልጆች ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ መቃኘቱ ላይ ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:58
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:58 ደቂቃ

ክሰል በዛምቢያ

ለከብት ርባታ አለያም ተመሳሳይ አዝርእት ወይንም ሰብሎችን ለማምረት ሲባል እጅግ ሰፋፊ የደን ይዞታዎች የሚመነጠሩት በብራዚል እና በኢንዶኔዢያ ብቻ አይደለም። የደን ጭፍጨፋ ከፍተኛ ደረጃ ከደረሰባቸው የአፍሪቃ ሃገራት መካከል ዛምቢያም ትገኛለች።

አካባቢው ጭስ ጭስ ይላል። በቅርብ ርቀት እሳት እየተቀጣጠለ እንደሆነም ያመላክታል። ከጉድጓዶች እና ከጡብ ከተሰሩ ምድጃዎች ነው ክሰሉ የሚንጣጣው። ሩክ ሙናቺክዌቲ ክሰሉ የሚወጣው ከወዲያ ማዶ እንደሆነ ይገልጣሉ። ሩክ ሙናቺክዌቲ የአካባቢው ነዋሪ «ጥቁሩ ወርቅ» እያለ የሚጠራውን ክሰል የተወሰኑ መቶ ሜትሮች ርቀት በማጓጓዝ ይቸረችራሉ።

እንጨቱ ሲከስል፣ አካባቢው በጢስ ተውጦ

እንጨቱ ሲከስል፣ አካባቢው በጢስ ተውጦ«የክሰል ንግዱ ባሕላዊ እና ለሴቶች የተተወ ተግባር ነው። ወንዶች ወደ ደኑ በማቅናት ዛፎችን ገንድሰው ፍልጦቹን ማክሰል ነው ሥራቸው። እኛ ገበያ ወስደን እንቸረችራለን። ለእኛ ገንዘብ ለማግኘት ብቸኛ መንገዳችን ይኽ ነው። ቤተሰቤን ለመመገብ ይበቃኛል።»

የ57 ዓመቷ ክሰል ቸርቻሪ ወይዘሮ እጅግ የድኅነት አረንቋ ውስጥ የሚገኙ ዛምቢያዊ ድሆች በሚገኙበት አካባቢ ነው ኑሮዋቸው። የመኖሪያ ቀዬያቸው በመዲናይቱ ሉሳካ እና በስተ-ደቡብ ሲል በሚገኘው ሊቪንግስቶን መካከል ባለው መንገድ ላይ ይገኛል።

ክሰል በብስክሌት ተጭኖ

ክሰል በብስክሌት ተጭኖ

ወንዶቹ በክሰል የተሞሉ ጆንያዎችን በብስክሌት እና በበሬዎች በሚገፉ ጋሪዎች ጭነው በአቅራቢያው ወደሚገኘው መንደር ያጓጉዛሉ። በርከት ያሉ በክሰል የተሞሉ ጆንያዎችን ጭነው ወደ ከተማ ለማድረስ አንዳንድ ጊዜ የጭነት መኪናዎችም በአካባቢው ይቆማሉ።

በአጭሩ ክሰል ከመንደሩ ነዋሪዎች የእለት ከእለት ኑሮ ጋር የተቆራኘ ነው ማለት ይቻላል። የአፍሪቃ ከባቢ አየር በእንግሊዘኛ (Environment Africa) የተባለው የከባቢ አየር ጥበቃ ድርጅት ባልደረባ ናሞ ቹማም ይኽንኑ ነው አስረግጠው የሚናገሩት።

« አብዛኞች ምግብ ለማብሰል ከክሰል በሚገኝ የኃይል ምንጭ ጥገኛ ናቸው፤ ከዝያ በተጨማሪ ከሰል ርካሹ የኃይል ምንጭ ነዉ። ከ65 እስከ 70 በመቶ የሚጠጋው የዛምቢያ ነዋሪ፤ ከድህነት ጣርያ በታች ይገኛል። አብዛኛው ቤት እንዲሁ የኤሌክትሪክ አቅርቦት የለውም። ያም በመሆኑ ሌሎች አማራጭ የኃይል ምንጮችን ነው የሚጠቀመው፤ በተለይ ክሰልን። በዛምቢያ ፀሓይ በደንብ ነው የምትወጣው። ስለዚህ ከፀሓይ የሚገኝ ኃይልን እንዴት መጠቀም እንደምንችል ማጤን እንሻለን። ከፀሓይ የሚገኝ ኃይል የትም ሊገኝ የሚችል ነው፤ በዚያ ላይ ወዲያው የሚሟጠጥ አይደለም።»

ይሁንና እንደ ዛምቢያ መንግስት ግምት ክሰል ለማውጣት በየዓመቱ 300.000 ሔክታር ደን ይጨፈጨፋል። ይኽም ዛምቢያ በዓለማችን ደንን በስፋት ከሚመነጥሩ ሃገራት ቀዳሚ ተርታ ላይ እንድትሰለፍ አድርጓታል። በአነስተኛ ምርት የሚተዳደሩ ገበሬዎች ድርቁ እና የጎርፍ መጥለቅለቁ እየተባባሰ መምጣቱ እንዳማረራቸው ይናገራሉ። ከሰል ቸርቻሪዋ ወይዘሮ ሩክ ሙናቺክዌቲ ኹኔታው አሳስቧቸዋል።

በክሰል የተሞላ ከረጢት

በክሰል የተሞላ ከረጢት

«እዚህ በአቅራቢያችን ዛፍ የሚባል ነገር ካየን በጣም ቆይተናል። ወንዶቹ በየጊዜው ሩቅ ቦታ ለመሄድ ይገደዳሉ። ያም በመሆኑ የክሰል ችርቻሮ ንግዱ ባለፉት ዓመታት አስቸጋሪ ኾኗል። እኔ በበኩሌ ለወደፊቱ ብሎ ችግኝ የሚተክል አንድም ሰው አላውቅም።»

ነገሩ ዛፍ ላይ ተንጠላጥሎ ቅርንጫፍ መዘንጠፍ አብሮ ለመገንደስ ነዉ እንደሚባለዉ ሁሉ፤ ይኽን የሀገሪቱ መንግሥትም ቢሆን አሁን ዐዉቆታል። የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣኑ ፍሬዘር ቾሌ ክሰል በማክሰል ከመተዳደሩ ውጪ ነዋሪው አማራጭ ሊኖረው ይገባል ይላሉ።

«ከአኹን በኋላ ክሰል አትጠቀሙ ከሰል አታምርቱ ማለት አንችልም። ሌሎች የገቢ ምንጮችን ልናቀርብላቸዉ ያስፈልጋል። ለአብነት ያኽል የንብ ርባታ እንዴት እንደሆነ እናሳያቸዋለን። ከማር ሽያጭ የሚያገኙት ገቢ ከክሰሉ ይልቃል።»

ይኽን መሰሉ መርሐ-ግብር አንዳች ጠብ የሚል መፍትኄ አልያም የተሻለ መሆኑ ገና አጠያያቂ ነዉ። ድኅነትን ለመዋጋት ፋይዳ ያለው ነገር ካልሰተሠራ እና የኃይል አቅርቦት ካልተዘረጋ በስተቀር በዛምቢያ እለት በእለት የሚገነደሱ ዛፎችን እና የደን ምንጣሮውን ማቆም አይቻልም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic