ክሮኤሺያና የአውሮፓ ሕብረት | ኤኮኖሚ | DW | 03.07.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ክሮኤሺያና የአውሮፓ ሕብረት

የቀድሞይቱ ዩጎዝላቪያ ሬፑብሊክ ክሮኤሺያ ባለፈው ሰኞ 28ኛዋ የአውሮፓ ሕብረት ዓባል አገር ለመሆን በቅታለች። ሕብረቱ ክሮኤሺያን የተቀበለው በጋራ ምንዛሪው በኤውሮና በርከት ባሉ ዓባል መንግሥታት የበጀት ቀውስ ተወጥሮ በሚገኝበት ወቅት ነው።

እናም እንደ ቀድሞው የመስፋፋት ሂደት ሣይሆን በብራስልስና በራሷ በክሮኤሺያ ሳይቀር ደስታው ቆጠብ ያለ ሆኖ ነው የታየው። እንደ ዕውነቱ ከሆነ ከክሮሺያ ሕዝብ ግማሹ ለሕብረቱ ዓባልነት ጀርባውን መስጠቱ ቀደም ሲል የተከሰተ ነገር ነበር። እርግጥ ይህም ሆኖ ግን የሕብረቱ በክሮኤሺያ መስፋፋት ታሪካዊ ግምት የሚሰጠው ሲሆን ለተቀሩት የባልካን ሃገራት በር ከፋች እንደሚሆንም ዕምነት አለ። ለመሆኑ ክሮኤሺያ በምን ዓይነት የማሕበራዊና የኤኮኖሚ ይዞታ ነው ሕብረቱን የተቀላቀለችው? ቀደም ካለው ልምድስ ትምሕርት ተቀስሟል ወይ? መልሱ ቀላል አይሆንም።

አንዱ ሃቅ ግን ክሮኤሺያ የአውሮፓን ሕብረት በዓባልነት የተቀላቀለችው ማሕበረሰቡ ከባድ ሁኔታ ላይ በሚገኝበት ሰዓት መሆኑ ነው። ሕብረቱ በእስካሁን ሕልውናው ከባድ በሆነ ቀውስ ተወጥሮ የሚገኝ ሲሆን በመሠረቱ ተጨማሪ ዓባል አገር የመቀበል ፍላጎቱ ከመቼውም ይልቅ ዝቅተኛ ነው ቢባል ከዕውነት የራቀ አይደለም። ምክንያቱም የመስፋፋቱ ጉዳይ ብዙ ጥያቄዎችን አስነጥቷል። በዚሁ የተነሣም የአውሮፓ ሕብረት የመስፋፋት ጉዳይ ኮሜሣር ስቴፋን ፉለ ባለፈው መጋቢት ወር ዛግሬብን በጎበኙበት ወቅት የሕብረቱ የመስፋፋት ፖሊሲ ዓመኔታ ማጣት እንደሌለበት ነበር ጠበቅ አድርገው ያስገነዘቡት።

«የአውሮፓ ሕብረት በወቅቱ ከሚገኝበት ውስጣዊ ችግር አንጻር የመስፋፋቱ ፖሊሲ መቀጠል ብቻ ሣይሆን አስተማማኝ ሆኖ መራመዱን ማረጋገጡ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ»

ይሄው ዓመኔታ ከስድሥት ዓመታት በፊት ሩሜኒያና ቡልጋሪያ ዓባል በሆኑበት ወቅት ተጓድሎ መገኘቱ የታየ ነገር ነው። ሁለቱ የደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ ሃገራት ዓባል በሆኑበት ሰዓት ሙስናን በመታገሉ ረገድ ከብራስልስ የተጠበቀውን ያህል የተራመዱ አልነበሩም። እናም በጊዜው የታሰበው ዓባልነቱ የተፈለገውን ለውጥ ሊያራምድ ይችላል ተብሎ ነበር። ግን የኋላ ኋላ የተከሰተው የተጠበቀው ሣይሆን ተቃራኒው ነው።

ሁለቱ ሃገራት በዓባልነት ሕብረቱን ከተቀላቀሉ በኋላ የለውጡ ጥረት እንዲያውም ይደበዝዛል። ሩሜኒያና ቡልጋሪያ ዛሬም በሙስና እንደተወጠሩ ሲቀጥሉ በሼንገኑ ከቁጥጥር ነጻ የቀረጥ ክልል እንዳይሳተፉ አሁንም እንደተገለሉ ናቸው። የአውሮፓ ሕብረት ከሁለቱ ሃገራት ባገኘው ልምድ ታዲያ በክሮኤሺያ ላይ ጠንከር ማለቱ አልቀረም። በዛግሬብ መንግሥት የተወሰዱ የለውጥ ዕርምጃዎች ሁሉ ባዶ አዋጅ ሆነው እንዳይቀሩ በሚገባ ገቢር መሆናቸውን ለማረጋገጥ ዓቢይ ትኩረት ተሰጥቷል።

ለዚህም ነበር የሕብረቱ የመስፋፋት ጉዳይ ኮሜሣር ስቴፋን ፉለ ክሮኤሺያ አስተማማኝ ለውጥ ማካሄዷን በደስታ ያረጋገጡት።

«ክሮኤሺያ ዛሬ አስተማማኝ፣ ቀጣይነት ያለውና መልሶ የማይታጠፍ ለውጥ ማካሄዷን ለማስመስከር ትችላለች»

ለአውሮፓ ሕብረት ክሮኤሺያ አሁን በተለይም ሙስናን በመታገል መቀጠሏ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው እንደ ሩሜኒያና እንደ ቡልጋሪያ ተደፋፍኖ መቅረት የለበትም። አይሆንም እየተባለም ነው። የክሮኤሺያው ፕሬዚደንት ኢቮ ዮሲፖቪች እንደገለጹት ዛሬ በሙስና ላይ ያለው የሕብረተሰብ አመለካከት በአገራቸው መለውጥ የያዘ ጉዳይ ሆኗል።

«ክሮኤሺያ ውስጥ የሚደረገው ለውጥ ጨርሶ ወደ ኋላ የማይመለስ ነው። አዎን፤ እንደ ሌሎች ሃገራት ሁሉ እኛም ዘንድ ሙስና ነበረ፤ ዛሬም አለ። ነገር ግን በሌላ በኩል በሙስና ላይ ያለው አመለካከት እየተለወጠ መጥቷል። ከእንግዲህ ይህን ወደ ቀድሞው ሁኔታ የሚመልስ ፕሬዚደንትም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም የፈለገው ሌላ ሊኖር አይችልም»

ክሮኤሺያ የአውሮፓው ሕብረት ዓባል የሆነችው ከባድ የኤኮኖሚ ችግሯን እንደያዘች ነው። ግን ለነገሩ በሕብረቱ ውስጥ በዚህ ረገድ ብቸኛዋ አገር አትሆንም። ሕብረቱ ከግሪክ እስከ ስፓኝ በርከት ባሉ ዓባል ሃገራቱ በፊናንስና በበጀት ቀውስ መጠመዱ ውሎ ያደረ ሃቅ ነው። ከዚህ አንጻር በትስስሩ የክሮኤሺያም ሆነ የብራስልስ ተጠቃሚነት ቢቀር በአጭር ጊዜ ስሌት ያን ያህል ጎልቶ የሚታይ አይመስልም።

እንግዲህ የአውሮፓ ሕብረት ክሮኤሺያን በዓባልነት በመቀበል በወቅቱ ከጥቅሙ ይልቅ ሸክሙን ነው ያከበደው። የቀድሞይቱ ዩጎዝላቭ ሬፑብሊክ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ከባድ የኤኮኖሚ ችግር ተጭኗት ቆይታለች። የስራ አጡ ድርሻ ሃያ ከመቶ ይጠጋል። ከዚህ አንጻር ክሮኤሺያ በሕብረቱ ዓባልነት በፍጥነት ከዛሬ ወደ ነገ ለመበልጸግ መቻሏ የማይጠበቅ ነገር ነው። በሌላ በኩል ግን ዓባልነቱ ለፉክክር እንድትነሣ የሚያነቃቃት ለመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስተሯ የዞራን ሚላኖቪች ጽኑ ዕምነት ነው።

«ክሮኤሺያ የአውሮፓው ሕብረት ዓባልነትም ሆነ ዓለምአቀፉ ትስስር የሚያስከትለውን ፈተና ሁሉ እንደምትቋቋም እርግጠኛ ነኝ። ጎረቤቶቻችንንም ወደፊት ወደ አውሮፓ በሚያደርጉት ጉዞ እንደግፋለን። ይህም የሰርቢያን ሆነ የቦስናን ዓባልነት አንቃወምም ማለት ነው። ጉዳዩ አጀንዳ ላይ ከቀረበ ክሮኤሺያ ልታግደው አትሞክርም»

ያም ሆነ ይህ የአውሮፓው ሕብረት ዓባልነት ለክሮኤሺያ ዕድገትም ጥርጊያ ከፋችነት አለው። ባልካኗ አገር ከእንግዲህ ከሕብረቱ በምታገኘው የገንዘብ ድጋፍ ጠቃሚ ዕርምጃ እንደምታደርግ የሚጠራጠር የለም። የሕብረቱ የአካባቢ ፖሊሲ ኮሜሣር ዮሐነስ ሃህን የክሮኤሺያ ዓባልነት ለአገሪቱ የሚያስከትለውን ጠቀሜታ ቀደም ብለው ባለፈው የካቲት ወር እንደሚከተለው ነበር የተነበዩት።

«ክሮኤሺያ ሕብረቱን በምትቀላቀልበት ጊዜ ሕብረቱ የሚያቀርብላት መዋቅራዊ ዕርዳታ ከመንግሥታዊ መዋዕለ ነዋይዋ አንጻር 70 በመቶውን ድርሻ የሚያክል ይሆናል። እርግጥ የዕርዳታውን ፍቱንነት በአዳዲስ የስራ መስኮች መፈጠርና በኤኮኖሚ ዕድገት መከሰት ሕዝቡ በተቻለ ፍጥነት እንዲሰማው ማድረግ አስፈላጊ ነው»

ክሮኤሺያ ከስሎቬኒያ ቀጥላ የአውሮፓን ሕብረት የተቀላቀለችው የቀድሞ ዩጎዝላቭ ሬፑብሊክ መሆኗ ነው። ታዲያ የ 90ኛዎቹ ዓመታት የባልካን የእርስበርስ ጦርነት ወልዶት የነበረው ጥላቻ ወደ ሕብረቱ ሰተት ብሎ ሊገባ ይችል ይሆን? የሚል ጥያቄን የሚያነሣ ምናልባትም አይታጣም። ፕሬዚደንት ዮሲፖቪች በበኩላቸው ይህ አይሆንም፤ ከሰርቢያ ጋር የነበረው ውጥረት በጣሙን ረግቧል ባይ ናቸው።

ዮሲፖቪች እንዲያውም ክሮኤሺያ በሕብረቱ ውስጥ የሰርቢያ ጥቅም አራማጅ ልትሆን እንደምትችል ነው የሚናገሩት። ጊዜው ከደረሰ ክሮኤሺያ የሰርቢያንም ሆነ የቦስናን የዓባልነት ጥያቄ በቬቶ መሻር አትፈልግም። ስሎቬኒያ በአንጻሩ በድንበር ውዝግብ የተነሣ የክሮኤሺያን የዓባልነት ድርድር ለወራት አግዳ መቆየቷ የሚታወስ ነው። በጥቅሉ ክሮኤሺያ የአውሮፓ ሕብረት ዓባል በመሆን የመበልጸግና በደህንነት የመኖር ተሥፋዋን አሳድጋለች። ግን ዓባልነቱ ከዚህ ባሻገርም ክብደት አያጣውም፤ በብራስልስ የአውሮፓ ፖሊሲ ምርምር ማዕከል የክሮኤሺያ ጉዳይ አዋቂ ኮሪና ስትራቱላት እንደሚሉት።

«ዓባልነቱ ክብርን፤ ደረጃን ከፍ የማድረግም ጉዳይ ነው። ክሮኤሺያ አሁን ዴሞክራሲያዊ እሴቶች ያሉት ሕብረት አካል ሆናለች። እናም ይሄው በዓለም ላይ ለአውሮፓው ሕብረት መስፈርቶች የቆመች ሆና እንድትታይ የሚያደርጋት ነው»

በሌላ በኩል የጊዜው ሁኔታ እንደመለወጡ መጠን የክሮኤሺያ ዓባልነትም የአውሮፓ ሕብረትን ተጨማሪ ሃይል የሚጠይቅ ነው። ይህም ቀላል አይሆንም። እርግጥ ለውጭ ተመልካቹ የሕብረቱ ማራኪነት እንዳለ ይቀጥላል። ከዚህ የተነሣም ክሮኤሺያ በአንዳንዶች ከፋፋይ እስከመባል የደረሰውን የጋራ ምንዛሪ ኤውሮን ትችቱ ሳይበግራት ከሶሥት እስከ አምሥት ዓመት በሚሆን ጊዜ ውስጥ ቅድመ-ግዴታዋን አሟልታ በስራ ላይ ልታውለው ትፈልጋለች።

ክሮኤሺያ በቱሪዝም፣ በቀላል ኢንዱስትሪና በእርሻ ልማትም ዳበር ያለች አገር ስትሆን ይሄው በሕብረቱ ጥላ ስር ለኤኮኖሚ ዕድገቷ ጠቃሚ ድርሻ እንዲኖረው ብዙ መጣር ይኖርባታል። የኤውሮን ምንዛሪ ዓባልነት በተመለከተ ምኞቱ በምን ፍጥነትና ሁኔታ ገቢር እንደሚሆን ጠብቆ መታዘቡ ግድ ነው። ለማንኛውም ክሮኤሺያ ለተቀሩት ጎረቤቶቿ የአውሮፓን ሕብረት ዓባልነት ጥርጊያ ከፍታለች። ምናልባትም ሰርቢያ ቀጣይዋ በቅርብ ትከተላት ይሆናል።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic