ክሬሚያ ድሮና ዘንድሮ | ዓለም | DW | 03.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ክሬሚያ ድሮና ዘንድሮ

ክሬሚያ። ዛሬ የዩክሬን ግዛት ናት።ዩክሬን ዳግም ከምዕራባዉያኑ ደጋፊዎች እጅ ከወደቀች ቅዳሜ-ሳምንት ሆናት።ፕሬዝዳት ቭላድሚር ፑቲን ግርማዊ ቀዳማዊ ንጉስ ኒኮላዉስ አይደለም።ዳግማዊ አሌክሳንደር፥ ሌኒን ወይም ስታሊኒንም አይደሉም።በክሬሚያ ሲመጣ ግን እንደሁሉም ሁሉ እጃችንን አጣጥፈን አንቀመጥም አሉ።


የዚያ ዘመኑ ዓለም ዘዋሪዎች ያዘመቱት ምርጥ ጦር ለሰወስት ዓመት በአረሩ እያነደደ፣ በአስከሬኑ አያጎደፋት በደሙ ጎርፉ እያቀዘቀዘ፣ አጥቧታል። ክሬሚያ። ክሪም ይሏታልም። ያ ጦርነት የተጀመረበት አንድ መቶ ስልሳኛ ዓመት ባለፈዉ ጥቅምት በተዘከረ-በወሩ የዘመኑ ሐያላን ሽኩቻ ኪየቭን በሰልፍ-ሲያስደልቃት ያቺን ግዛት ግራ፣ ቀኝ ያካልባት ነበር። የጥንቱ ጦርነት ያበቃዉ የካቲት ነበር። 1856 (ዘመኑ በሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።) ዘንድሮ ያስታወሰዉ የለም። በድሮዉ ጦርነት ባንድ ጎራ ተሰልፈዉ የነበሩት ሐይላት፣ የካቲት ኪየቭ ላይ በድል ፌስታ ሲያጨፍሩ፣ የድሮ ጠላቶቻቸዉ በድሮዋ የጦር አዉድ ለብቀላ አንድ ሁለት እያሉ ነዉ።ዉዝገት ንትሩክም ንሯል።ታሪክ ራሱን ደገመ ለማለት ችኮላ-ይሆን ይሆን፣ ያሁኑን እዉነት ያየ-የሰማ ግን የጥንቱን አለማስታወስ፣ የዛሬዉን አለመጠየቅ በርግጥ አይችልም።

ቱርክ የአዉሮጳ ማሕበር አባል ለመሆን ያመለከተችዉ የቀድሞዋ ሶቬት ሕብረት የምሥራቅ አዉሮጳ ሐገራትን በጠንካራ መዳፍ ክርኗ ፈጥርቃ እንደያዘች፣ ማሕበሩ ገና የአዉሮጳ ምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ በሚባልበት ዘመን ነበር። 1987።

እስከ ዛሬ አባል አልሆነችም። ሶቬት ሕብረት ከተፈረካከሰች በሕዋላ ኮሚንስታዊ ርዕዮተ-ዓለማቸዉን አዉልቀዉ የጣሉ አብዛኞቹ የምሥራቅ የአዉሮጳ ሐገራት ግን ባጭር ጊዜ የሕብረቱ አባል ሆነዋል። የአዉሮጳ ሕብረት መስራቾች፣ ዘዋሪዎችም ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ጀምሮ በዩናይትድ ስቴትስ የሚመሩት የምዕራብ አዉሮጳ ሐገራት ናቸዉ። ቱርክም ልክ እንደምዕራብ አዉሮጳ ሐገራት ሁሉ በዩናይትድ ስቴትስ የምትመራ፣ ልክ እንደ ምዕራብ አዉሮጶች ሁሉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ አባል የነበረችና የሆነች፣ ከነሱ ጎን ቆማ ቀዝቃዛዉን ጦርነት የተዘናገረች ሐገር ናት።

የበርሊን ግንብ ከተደረመሠ በኋላ የምዕራቡን ካባ አጥልቀዉ የምዕራቡን ማሕበር የተቀየጡት ሐገራት ጦር ሐይል፣ የምጣኔ ሐብት፣ የሕዝብ ብዛት ቢደመር ከቱርክ ቢያንስ እንጂ አይበልጥም። ግን ቱርክ ነጭ ያለሆነ-ያዉም ሙስሊም የሚባዘበት ሕዝብ ሐገር ነች።

ሌሎቹ ሲያድበሰብሱት በይፋ ያፈረጡት የቀድሞዉ የኢጣሊያ ጠቅላይ ሚንስትር ሲልቪዮ ቤርሎስኮኒ እንዳሉት ሙስሊማዊቷን ቱርክን አባል ማድረግ የማሕበሩንም የአባላቱንም ክርስቲያናዊነት ያረክሳል። ቤርሎስኮኒ የሚገርሙ ናቸዉ። ማሕበራቸዉ በቱርኮች እንዳይረክስ ሲታገሉ፣ በሰባ አመታቸዉ ለአካለ መጠን ያልደረሰች ሞሮኮዊት ኮረዳ ሲያማግጡ ተይዘዉ፣ ተዋርደዉ ከሥልጣን ወረዱ።

የአዉሮጳ ሕብረት መሪዎች ከቱርክ ይልቅ ምሥራቅ አዉሮጶችንና የቀድሞዋ ሶቬት ሕብረት ሪፐብሊኮችን አባል ለማድረግ የተጣደፉበት ሌላዉ ምናልባትም ዋናዉ ምክንያት ሞስኮ ዳግም አንሰራርታ ከጭብጧ ያፈተለኩ ሳተላይቶቿን ዳግም ከእቅፏ እንዳታስገባ ለመገደብ ነዉ። ምዕራባዉያኑ ሐገራት ሕብረቱን የተቀላቀሉትንም እስካሁን ያልተቀላቀሉትም የምሥራቅ አዉሮጳና የቀድሞ የሶቬት ሕብረት አብዛኞቹ ሪፐብሊኮች የኔቶ አባል በማድረግ የሩሲያን ተፅዕኖ እጅ ከወረች ጠፍረዉታል።አዉሮጳን በአብዛኛዉ እንደተቀማች የምታስበዉ ሩሲያ የእስያን ገበያ፣ የመካከለኛዉ ምሥራቅን ነዳጅ ዘይት፣የአፍሪቃን ጥሬ ሐብት ለማግኘት በየአካባቢዉ ከዘረጋችዉ የተፅዕኖ መረብ የተረፋት የሜድትራኒያንን ባሕር የምትቆጣጠርበት ሥልትና ጡንቻ ነዉ። የፕሬዝዳት በሽር አል-አሰድ መንግሥት ጥርስ-ጥፍር መርገፍ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሞስኮዎች ሶሪያ ላይ ያላቸዉ ትንሽ የጦር ሰፈር ጨርሶ የሚዘጋበት ጊዜ ሩቅ እንዳይደለ ማስላት ግድ ሆኖባቸዋል።

የሩሲያ ሁለተኛዉና ከፍተኛዉ ሐይሏ፥ ጀርመናዊዉ የባሕርል ሐይል ጉዳይ አጥኚ ክላዉስ ሞምዘን እንደሚሉት ሰቫስቶፖል የሚገኘዉ ጠንከራ የባሕር ጦሯ ነዉ።ሳቫስቶፖል-የክሬሚያ ወደብ ነዉ።

«ክሬሚያ ጥቁር ባሕር ላይ ሆኖ አካባቢዉን ለመቆጣጠር ትልቅ ሥልታዊ አቀማመጥ አላት።ግዛቲቱ ወደ ባሕሩ ዘልቃ የገባች ልሳነ-ምድር ናት።ሩሲያዎች ወደ ደቡብ ማለትም ወደ ሜድትራኒያን እና ወደ መካከለኛዉ ምሥራቅ ለመወርወር ግዛቲቱን እንደ መስፈንጠሪያ መስክ ይጠቀሙበታል። ከሶቬት ሕብረት ዘመን ጀምሮ፣ አዉሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች፥ ባሕር ሠርጓጅ ፈጣን ጀልባዎችን የሚያመረቱበት ጠቃሚ ኢንዱስትሪም እዚሕ ይገኛል።»

መቼም ይኸ መከከለኛዉ ምሥራቅ ጥንትም፥ ድሮም፥ ዘንድሮም መዘዘኛ ምድር ነዉ። ከ1200ዎቹ ዓመት ማብቂያ ጀምሮ ገሚስ ዓለምን የገዙት የኦስማን ቱርኮች በ1800 ዎቹ አጋማሽ ጠንካራ ክርናቸዉ መዛሉን፥ ያስተዋሉት ብሪታንያና ፈረንሳይ በቅድስቲቱ ምድር (ኢየሩሳሌም) የሚገኙ የክርቲያን (ባብዛኛዉ የካቶሊክ መካነ-ቅዱሳንንና) ክርስቲያኖችን ለመጠበቅ በሚል ቱርኮችን አስፈቅደዉ እግራቸዉን እዚያ ምድር ይተክላሉ።


የሩሲያዉ ዛር (ንጉስ) ቀዳማዊ ኒኮላስ ዘግየት ብለዉ እዚያዉ ምድር የሚገኙ የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችንና ቤተ-እምነቶችን የሚጠብቅ ጦር ማስፈር ይችሉ ዘንድ ቱርኮችን ይጠይቃሉ። የንጉስ ኒኮላስን ጥያቄ ከቱርኮች ቀድሞዉ ከቱርኮች አምርረዉ የተቃወሙት የቱርክን «ሞት» የሚጠብቁት የለንደንና የፓሪስ ገዢዎች ነበሩ።

ተቃዉሞዉ ተቃዉሞ አስከትሎ የሩሲያ ጦር ቱርኮች የሚቆጣጠሯትን የዛሬዋ ሩሜንያን መዳረሻ ግዛት ይቆጣጠራል። አሮጌዋ ተቀናቃኛቸዉ ቱርክ የምትሞትበትን ቀን ሲያሰሉ አዲስ ተሻሚ የመጣባቸዉ ብሪታንያና ፈረንሳይ በእስከዚያ ዘመን ታሪካቸዉ ለመጀመሪያ ጊዜ ግንባር ፈጥረዉ ከቱርክ ጎን ቆሙ።የዛሬዋ ኢጣሊያን ከስድስት መቶ አመታት በኋላ ዳግም ለማዋሐድ አንድ ሁለት ይሉ የነበሩት የሰርዲኒያዉ ንጉስ ቪክቶር አማኑኤል ዳግማዊ ሰወስቱን ሐያላን ተቀላቀሉ።

የኦስትሪያ ነገስታት በቀጥታ ባይሳለፉም የሩሲያዎችን እንቅስቃሴ በማወክ አራቱ ሐያላንን ደገፉ። አምስቱ ሐያላን ጀርመንን፥ ስዊስና ስላቪክን አስከትለዉ ያዘመቱት ጦር ከሩሲያና ሩሲያን ከሚደግፉት ከቡልጋሪያ፥ ከሠርቢያና ከግሪክ ጦር ጋር ክሬሚያ ላይ ይጨፋጨፍ ገባ።1853።

Der ehemalige Präsident Wladimir Putin spricht erstmals als neuer Regierungschef in Duma in Moskau

ጦርነቱ የካቲት 1956 በተባባሪዎቹ ሐይላት ድል ሲጠናቀቅ ያቺ ትንሽ ልሳነ ምድር ከሰወስት መቶ ሺሕ እስከ ሰወስት መቶ ሰባ አምስት ሺሕ በሚገመት የተባበሪዎቹ ሐገራት ወታደር፥ እና ከሁለት መቶ ሺሕ የሚበልጥ የሩሲያና የተከታዮቿ ወታደሮች አስከሬን ተከምሮባት ነበር።

ክሬሚያ። ዛሬ የዩክሬን ግዛት ናት።ዩክሬን ዳግም ከምዕራባዉያኑ ደጋፊዎች እጅ ከወደቀች ቅዳሜ-ሳምንት ሆናት።ፕሬዝዳት ቭላድሚር ፑቲን ግርማዊ ቀዳማዊ ንጉስ ኒኮላዉስ አይደለም።ዳግማዊ አሌክሳንደር፥ ሌኒን ወይም ስታሊኒንም አይደሉም።በክሬሚያ ሲመጣ ግን እንደሁሉም ሁሉ እጃችንን አጣጥፈን አንቀመጥም አሉ።

የሩሲያ የሕግ-መምሪያ ምክር ቤት (ዱማ) እንደራሴዎችም ፑቲን ያሉትን ገቢር እንዲያደረጉ ጠየቀ።

«ምክር ቤቱ፥(ዱማ) በዱማ አስተዳደር ስም (የሚከተለዉ) ማሳሰቢያ ለሩሲያ ፕሬዝዳንት እንዲደርስ አፅድቋል።ፕሬዝዳንቱ የክሬሚያን ሁኔታ ለማረጋጋት እርምጃ እንዲወስዱ እና ያለዉን አማራጭ በሙሉ ተጠቅመዉ የክሬሚያን ሕዝብ ከጉልበተኞች እና ከአመፀኞች እንዲከላከሉ የምክር ቤቱ እንደራሴዎች ጠይቀዋል።»

የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ሰርጌይ ናርይሽኪን።ቅዳሜ።አብዛኛዉ የክሬሚያ ሕዝብ ሩሲያዊ ወይም የሩሲያ ዝርያ ያለዉ ነዉ።ምጣኔ ሐብታዊ፥ ማሕበራዊ፥ ባሕላዊ ኑሮ-እንቅስቃሴዉ ሁሉ ከሩሲያ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነዉ።ይሕ ሕዝብ እንወክላለን የሚሉ ታጣቂዎች የቀድሞዉ የዩክሬን ፕሬዝዳት ቪክቶር ያኑኮቪች በአደባባይ ሠልፍ ከሥልጣን በተወገዱ ማግሥት የክሬሚያን አስተዳደር ፅሕፈት ቤት፥ የግዛቲቱን ምክር ቤት አዳራሽ፥ አዉሮፕላን ማረፊያዎችን ተቆጣጥረዉታል።ፑቲን ያዘዙት የሩሲያ ጦር ደግሞ በግዛቲቱ የሚገኙ ወታደራዊ ሠፈሮችን ያዘ።

ዩናይትድ ስቴትስ ባልደረበችበት ዘመን የዛሬዋን የዩናይትድ ስቴትስን ሥፍራ ይዛ የነበረችዉ ቱርክ ዛሬ-ዓለምን የመዘወር ጡንቻ፥ ሐብት፥ ተሰሚነትም የላትም።የጥንቷን ልዓለ ሐያል ቱርክን በዘማናዊ መልክ የተካችዉ ዩናይትድ ስቴትስም በምንም መልኩ ቱርክን አይደለችም።ሩሲያ ክሬሚያ ላይ ያደረገችና የምታደርገዉን ለማዉገዝ፥ ወይም የምዕራቡን ጥቅም ለማስከበር ግን እንደያኔዋ ቱርክ ሁሉ የሩሲያን ተቀናቃኞች ለመምራት ዘመናዊቱ ልዕለ ሐያል ሐገር አላመነታችም።

«የሩሲያ ፌደሬሽን ዩክሬን ዉስጥ ሥለ ምታደርገዉ ወታደራዊ እንቅስቃሴ የደረሰን ዘገባ በጣም አሳስቦናል።የዩክሬንን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን የሚጥስ ማናቸዉም (እርምጃ) አደፍራሽ ነዉ።ይሕ ለዩክሬን፥ ለሩሲያ፥ ለአዉሮጳም አይጠቅምም።»

ፕሬዝዳት ባራክ ኦቦማ። አይጥቀምም-ግን ሆኗል።ወይም እየሆነ ነዉ።የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚሉት ሩሲያም ሆነች ምዕራባዉያን ሐገራት በቀጥታ ቃታ ከሚያስብ ጠብ መግባቱን አይፈልጉም።የዚያኑ ያክል ሩሲያ ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ የተቆጣጠራችን ያቺን ግዛት ከጭብጧ ፈልቅቆ ለመዉሰድ የሚደረገዉን ሙከራ ጨርሶ አትታገሠዉም።

ነገሩ ከከረረ ሩሲያ የክሬሚያ ራስ ገዝ መስተዳድር ሕዝብ ከኪየቭ ማዕከላዊ መንግሥት ተገንጥሎ የራሱን ነፃ መንግሥት ለመመስረት በድምፁ (ሪፈረንደም) እንዲወስን እስከ መጠየቅ ትደርሳለች ነዉ-የሚባለዉ።የሩሲያን፥ እርምጃና ዕቅድ ምዕራባዉያኑ አይቀበሉትም።ንግስት ኤልሳቤጥ ንግሥት ቪክቶሪያ አይደሉም።ዴቪድ ካሜሩን ጆርጅ ሐሚልተን ጎርዶን አይደሉም።የሩሲያን እርምጃ ዕቅድ በመቃወም ግን ክሬሚያ የዛሬዋ ለንደን መሪዎች ካያት ቅድመ አያቶቻቸዉ አመሳሰለቻቸዉ።«የክሬሚያ ሁኔታ በጣም አሳስቦናል።ማንኛዉም ሐገር የዩክሬንን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት ማክበር አለበት።ሩሲያ ለዚሕ ቃል ገብታለች።ቃሏን መጠበቅ አለባት።ዓለም እየተመለከታት ነዉ።»

አሉ ኬሙን።ፕሬዝዳት ፍራንሷ ኦሎንድ ሉዊስ ናፖሊዮን ቦናፓርት ወይም ናፖሊዮን ሳልሳዊ አይደሉም።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሎራ ፋቢዮስም ማርሻል ዣክ ሌሮይስን አይሆኑም።ሩሲያን በመቃወም፥ ከለንደን-ዋሽግተኞች ጋር በማበር ግን ፋቢዮስ እንዳሉት ለፓሪስ ዘንድሮም ድሮ ነዉ።


«የሩሲያ ዉሳኔ የቡድን ሰባትንና ስምንትን መርሆች የሚፃረር ነዉ።ሥለዚሕ ሩሲያ እነዚሕን መርሆች እስክታከብር ድረስ ሶቺ-ሩሲያ ዉስጥ ለሚካሔደዉ የቡድን ስምንት ጉባኤ በሚደረገዉ ዝግጅት ላይ ፈረንሳይ ላለመካፈል አቋም ይዛለች።»

የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልም አከሉበት።ግን ዉይይት ብለዉ።

«ከታሪክ እንደተማርነዉ ግጭትን በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት አስፈላጊዉ ሁሉ መደረግ አለበት።አሁንም ዩክሬን (ለከተሰተዉ ችግር) ይሕን መሠረታዊ መርሕ ገቢር ማድረግ ይቻላል።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ሩሲያን እንዲያወግዝ ዩክሬን ጠይቃ ነበር።የኪየቭ መሪዎች ለመሪነቱ አዲስ ቢሆኑም ምክር ቤቱ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ያላትን ሐገር ማዉገዝ እንደማይችል በርግጥ አላጡም።የምዕራባዉያን ተባባሪዎቻቸዉን ሙሉ ድጋፍ ለማግኘት ግን መልዕክታቸዉ በርግጥ ሠርቷል።

ከዋሽግተን፥ ለንደን፥ ከፓሪስ፥ በርሊን የተንቆረቆረዉ ዉግዘት፥ ተቃዉሞ፥ የማዕቀብ ዛቻ ፉከራ ቢያንስ እስካሁን የሞስኮዎች አቋምን የሚያለሳልስ አለመሆኑ እንጂ-የኪየቮች ጭንቀት።እየሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የሰርጌይ ላቭሮቭ ምላሽ ደግሞ ለምዕራቦችም ለኪዮቮችም ጠንካራ ተቃዉሞ ጠጣር አፀፋ ነዉ-የሆነዉ።

Großbritannien Wahlen David Cameron Konservative

«እደግመዋለሁ።ይሕ የዜጎቻችንና የወዳጆቻችንን ደሕንነት ማስከበር ነዉ።በጣም አስፈላጊ የሆነዉን የሰብአዊ መብት አካል-የመኖር መብትን ማስከበር ነዉ።እኒያ-ሁኔታዉን እንደ ወረራ የተረጎሙት እና እኛን በማዕቀብና በማግለል ለመቅጣት የሚዝቱብን ሐይላት-እኒያዉ የሚያቀርቧቸዉን የዩክሬን ፖለቲከኞች ድርድርን እንቢኝ እንዲሉ እና ቀነ-ገደብ እንዲቆርጡ ሲገፋፏቸዉ የነበሩት ሐይላት ናቸዉ።የዩክሬንን ደቡባዊና ምሥራቃዊ ግዛት (ሕዝብን) ስጋት ከቁብ ሳይቆጥሩ የዩክሬን ሕዝብ እንዲከፋፈል ያደረጉ ናቸዉ።»

ትናንት በርግጥ ዛሬ አይደለም።ክሬሚያ ግን የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ እንዳሉት-ሃያ አንደኛዉ ክፍለ ዘመን-አስራ ዘጠነኛዉን ክፍለ-ዘመን እያስመሰለችዉ።´2004ትን እንደ 1850ዎቹ።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለስ


Audios and videos on the topic