ክሪሚያና የፖለቲካው እሰጥ-አገባ፤ | ዓለም | DW | 19.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ክሪሚያና የፖለቲካው እሰጥ-አገባ፤

በጀርመን የሕዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት፤ የቀድሞው የውጭ ፖለቲካ ጉዳይ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሩፕሬሽት ፖሌንዝ ፣ ሩሲያ፣ የክሪሚያን ልሳነ-ምድር በኃይል መያዟ ፤ በኃላፊነት፤ የአውሮፓውን ሕብረት አይመለከትም አሉ። እንደርሳቸው ትዝብት፤ ትናንት፤

በክሪሚያ ልሣነ-ምድር፣ የተኩስ ልውውጥ መደረጉ፣ የውሳኔ ሕዝቡ ክንዋኔ ማዕከላዊውን መንግሥትም ባለማሳተፉ ፤ ሂደቱና ውጤቱ አዎንታዊነትን አላንጸባረቀም ።

የተበበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን፣ በክሪሚያ ሳቢያ የተነሣውን ውዝግብ ፤ የሩሲያና የዩክሬይን ባለሥጣናት ሰላማዊ መፍትኄ እንዲፈለጉለት ለማነጋገር ዛሬ ወደ ሞስኮ የተጓዙ ሲሆን ፤ ነገ ከፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲንና ውጭ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር ሐሳብ ይለዋወጣሉ። ከዚያም ወደ ኪቭ ያልፋሉ። ከውሳኔ ሕዝብ በኋላ፤ ክሪሚያ በተፋጠነ ሁኔታ በሩሲያ ፌደሬሽን አጠቃላይ ም/ቤት ድምፅ ፤ ከሩሲያ ጋር ተዋኽዳለች። በዚሁ ሥነ ስርዓትም ፑቲን እንዲህ ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው።

«ክሪሚያ ማለት ሴቫስቶፖል ናት፤ ከተማይቱና ታሪኳ! ዐበይtre ውጣ ውረዶችን ያሳለፈችው ከተማ! የምሽግ ከተማ፤ እንዲሁም የሩሲያ የጥቁር ባህር የባህር ኃይል ቋሚ ቦታ!»

በክሪሚያ የታየው ሂደት ዋናውን የዩክሬይን ምድር የሚያናጋ ሁኔታ ያስከትል ይሆናል ከሚለው ሥጋት ጋር በተያያዘ ፣ የሩሲያው መሪ እንዲህ ነበረ ያሉት።

«ዩክሬይን እንድትከፋፈል አንሻም። ነገር ግን ክሪሚያ የሩሲያ አካል ሆና ትኖራለች።

ክሪሚያ፤ ለሩሲያ ባካባቢው የሩሲያ እጅግ ጠቃሚ ስልታዊ ቦታ ናት።»

200 የሚሆኑ ጦር መሣሪያ ያልታጠቁ ሰዎች የዩክሬንን የባህር ኃይል ሠፈር ከወረሩ በኋላ ሩሲያውን ወታደሮች ባካባቢው ታይተዋል። የዩክሬይን የባህር ኃይል አባላት እንባ እየተናነቃቸው፤ ጦር መሣሪያ ሳይይዙ ዕቃቸውን ብቻ ጠቅልለው መውጣት ግድ ሆኖባቸዋል። በዚያ እንደተወለደና እንዳደገ 20 ዓመትም እንዳገለገለ የገለጠው ፤ ከ 20 ሺው የዩክሬይን የባህር ኃይል አባላት አንዱ የሆነው ቭላድ የተባለው ወታደር ፤ አሁን የት ነው የምሄደው? ሲል መጠየቁ ተመልክቷል።

የጀርመን መራኂተ መንግሥት ወ/ሮ አንጌላ ሜርክል፣ ትናንት የፖርቱጋሉን የመንግሥት መሪ ፓሶስ ኮልሆን ተቀብለው ሲያነጋግሩ ስለዩክሬይኑ ውዝግብ እንዲህ ነበረ ያሉት።

«ከዩክሬይን ጋር ተያይዞ የተነሣውን ጥያቄ በተመለከተ ፣ ከተወሰነው ማዕቀብ ጋር ውይይት እንቀጥላለን። እንነጋገራለን።»

የሩሲያ ምክትል የመከላከያ ሚንስትር አናቶሊ አንቶኖቭ፤ ከብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በኋላ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተገነባ ያሉትን በጎ ሁኔታ በተለይም ወታደራዊ ትብብርን ብሪታንያ በከፊል ማቋርጧን በጥብቅ ነቅፈዋል። የብሪታንያ ው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዊልያም ሄግ፤ ሩሲያ ክሪሚያን ጠቀለለች በማለት የሀገራቸውን አቋም እንደሚከተለው ነበረ የገለጡት።

«ሩሲያ ይህ ጉዳይ በረዥሙ ስለሚያስከተለው መዘዝ ግልጽ ሊሆንላት ይገባል። ብሪታንያ የሚያስከተለውን መዘዝ በተመለከተ አታፈገፍግም»የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ በበኩላቸው እንዲህ ነበረ ያሉት።

«ዩናይትድ ስቴትስና ፖላንድ ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈው፤ በዓለም ዙሪያ ወሳኝነት ባላቸው ተልእኮዎች፤ አብረው ይቆማሉ። ነገር ግን የቅርብ ጊዜ ድርጊቶች፤ የጋራ የመከላከያ ጉድኝነታችን እንደ ዐለት የጠነከረ መሆኑን ነው የሚያሳስበን።»በጥቁር ባህር ሰሜናዊ ጫፍ ፣ ሴቫስቶፖል የተባለው የባህር ኃይል የወደብ ምሽግ ጭምር የሚገኝበት የክሪሚያ ልሳነ ምድር በስልታዊ አቀማመጡ የታወቀ ሲሆን በተለያዩ ዘመናት መንግሥታት ውጊያ አካሂደወበታል።

ጥንት የሩሲያ አካል የነበረውን ልሳነ ምድር ፤ የዩክሬይን አካል እንዲሆን ያደረጉት የቀድሞው የሶቭየት ሕብረት መሪ ኒካታ ክሩሼቭ ናቸው። በልሳነ ምድሩ የሚኖሩት አብዛኞቹ ሩሲያውያን ናቸው። ከሰሞኑ የግዛቲቱ ህዝብ በሰፊ የድምፅ ብልጫ ከሩሲያ ጋር ለመዋኻድ ድምፅ ቢሰጥም፤ ከአዲሱ የዩክሬይን መንግሥት ሌላ የአውሮፓው ሕብረት አባል ሃገራትና ዩናይትድ ስቴትስ ተቃውመውታል ። ከፊል ማዕቀብም ጥለዋል።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic