1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ክረምት እና ችግኝ ተከላ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 13 2011

በኢትዮጵያ 4 ቢሊየን የዛፍ ችግኞች ሊተከሉ የመታቀዱ ዜና ከሰሞኑ ይፋ ሆኗል። የክረምት ወራትን እየተከተሉ ችግኞች ተተከሉ ዜና በሀገሪቱ ተጠናክሮ መደመጥ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። የተራቆተውን መልክአምድር ሲመለከቱ «ሀገሬ ኢትዮጵያ ዙሪያሽ ለምለም» በሚሉ ግጥሞች መሸነጋገሉ አንድ ቦታ ሊገታ እንደሚገባ እርስዎም ማሰብዎ አይቀርም።

https://p.dw.com/p/3Iqh5
Äthiopien Vertriebene aus Chilga
ምስል DW/A. Mekonnen

«የዛፍ ችግኙ ቢተከልም የሚከታተለው ይሻል»

4, ሚሊየን የዛፍ ችግኞች በያዝነው ዓመት የክረምት ወራት የመትከሉ ዕቅድ ከተማን ለማስዋብ እና የአረንጓዴ ልማትን ለማስፋፋት የታለመ ነው። ተነሳሽነቱም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሲሆን ያንን የሚያስተባብር የቴክኒክ ኮሚቴም የደን ባለሙያዎችን አካትቶ መዋቀሩን ከአባላቱ እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተረድተናል። የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ የደን ባለሙያ ዶክተር ተፈራ መንግሥቱ እንደገለፁልንም አፈጻጸሙ በመንግሥት ደረጃ  እየተዘጋጀ ነው።

ከዚህ ቀደም ተተከሉ የተባሉት የዛፍ ችግኞች ዕጣ ፈንታ እያነጋገረ አሁንም እንዲህ ያለው ዕቅድ መሰማቱ ጥያቄ ማስነሳቱ ግድ ነው እና ለመሆኑ ችግኙስ አለ ወይ? ስል ዶክተር ተፈራን ጠየኳቸው፤

« ይሄንን ታርጌት ተግባራዊ ለማድረግ ችግኝም ገንዘብም፤ ሌላውም የሚያስፈልጉ ነገሮች ምን ያክል እጃችን ላይ አለ የሚለው አሰስመንት እየተሠራ ነው። እስካሁን መረጃዎች እየተደራጁ ነው ያሉት።»

ስለ 4 ቢሊየን ችግኝ ተከላው ይፋ የሆነው ዜና 3 ቢሊየን ችግኞች በማፍያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ እና ቀሪው ከግሉ ዘርፍ እና ከማኅበረሰቡ እንደሚሟላ ነው ያመለከተው። የግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ብርሃኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነቃቁት ይህ ዕቅድ ግቡን እንዲመታ መሥሪያ ቤታቸውን የበኩሉን እያከናወነ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት ለተከላው እስካሁን ምን ያህል ችግኞች እንደተዘጋጁ የሚያሳይ የተጠናቀረ መረጃ እንደሌለ ገልጸዋል።

Äthiopien Wald
ምስል Imago/imagebroker

እንዲያም ሆኖ የችግኝ ተከላው በሀገሪቱ አካባቢዎች የአየር ጠባይ ይዞታውን ተከትሎ ከያዝነው ወር ግንቦት አጋማሽ እንደሚጀመር ነው አቶ ዓለማየሁ የገለፁልን። ይህም እንደየክልሎቹ ዕቅድ እና ዝግጅት ይወሰናል። በትክክል በተግባር የሚደረገውን ለመመዝገብ ያለውን የመረጃ ፍሰት ለማዘመን እና ለማስተካከል መሥሪያ ቤታቸው የራሱን ስልት ለመከተል እየሞከረ መሆኑንም ያስረዳሉ።

አንድ የደን ባለሙያ እንደሚሉት 4 ቢሊየን የዛፍ ችግኝ 400 ሺህ ሄክታር መሬት ይሸፍናል። ችግኙ በእርግጥ ከተገኘ የት ይሆን የሚተከለው? ዶክተር ተፈራ መንግሥቱ ምላሽ አላቸው።

ዶክተር ዓለማየሁ ዋሴ በተለይ ሀገር በቀል ደን የሚገኝባቸው አካባቢዎች ትልቅ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ የሚወተውቱ የደን ባለሙያ ናቸው። 4 ቢሊየን የዛፍ ችግኞች ለመትከል መታቀዱ መልካም ዜና መሆኑን በመግለፅ መረን የለቀቀ የግጦሽ ልማድ ባለበት ግን ውጤት ማየት እንደሚከብድ ነው የሚናገሩት።

እስከዛሬ ይላሉ የደን ባለሙያው ከችግኝ ተከላው በኋላ የሚገኘው ውጤት በአማካኝ ከ30 እስከ 40 በመቶ ያልበለጠ ነው። ይህም በዓመት ወይ በሁለት ዓመቱ ስለሚለካ መሆኑን በመጠቆም ከ10 ዓመት በኋላ ቢታይ ቀንሶ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

Äthiopien - Gonder
ምስል DW/A. Mekonnen

ኢትዮጵያን አረንጓዴ ለማልበስ ያለመው ፕሮጀክት የብዙዎች ድጋፍ እና ይሁንታ ያለው መሆኑ ብዙም አያነጋግርም። ጥያቄው  «ይህ ዕቅድ እንዴት ግቡን ይመታል?»  ነው።  ዶክተር ተፈራ ለክትትሉ ሲባል ኃላፊነቱ በጥምረት መዋቀሩን ገልጸዋል።

«ይህ ኢኒሼቲቭ አንድ ለየት የሚያደርገው ጆይንት ኢኒሼቲቭ ተደርጎ እንዲወሰድ ነው የተፈለገው ማለት ግብርና ሚኒስቴር፣ የአካባቢ እና ደን ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፤ የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሥራ ክፍፍል አድርገው በየራሳቸው ማንዴት ሥራ ይሠራሉ»

 

ችግኞች ላለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት የመተከላቸው ዜና የመነገሩን ያህል ውጤቱ አለመታየቱን አስመልክቶ ለተነሳው ጥያቄ የግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ እስከዛሬ በተተከሉት የደን ይዞታው ላይ  መሻሻሎች መኖራቸውን ጠቅሰው የሥራው አፈጻጸም ዘገባ ላይ እውነቱ ብቻ እንዲቀርብ መደረግ እንደሚኖርበት አመልክተዋል።

ዶክተር ዓለማየሁ እንደሚሉት የሀገሪቱ የተፈጥሮ ደን ሲመናመን በችግን ተከላ ዘመቻዎች ሰው ሠራሽ ደኖች ጭማሪ አሳይተዋል። የአሁኑ 4 ቢሊየን ችግኝ ተከላ ውጤት እንዲያመጣ ከተፈለገ ደግሞ አስቀድሞ ሊታሰብበት የሚገባ መሠረታዊ ጉዳይ አለ።

Äthiopien Wüstenbildung in Ostäthiopien
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

የ4, ቢሊየን ችግኝ ተከላው ዜና በማኅበራዊ መገናኛዎች እንደተሰራጨ የተለያዩ አስተያየቶችን ተመልክተናል፤ «የኢህአዲግ ቁጥሮች እየመጡጡጡ ...ነው!! በክረምቱ 4 ቢለየን ችግኝ ይተከላል እየተባልን ነው። የዛሬ 10 ዓመት በሚለንየሙ በጣም ብዙ(ለመጥራት እንኳን የሚከብዱ) ቢለየን ዛፍ እንደተተከለ ተንግሮን ነበር። እሱ ከምን ደረሰ? የት አለ ደኑ?» ሲሉ ደረጀ ገረፋ ቱሉ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ፤ እሸቱ ሆማ ኬኖ ደግሞ፤ ከ2008 ዓ,ም ጀምሮ በነበሩት ሦስት ተከታታይ ዓመታት የተለያዩ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በቢሊየን ስለሚቆጠሩ የችግኝ ተከላዎች ያወጧቸውን ዜናዎች ዐበይት ርዕስ በማጣቀስ «ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የተነገረው የ4, 3 ቢሊየን ችግኞች ዜና ዛሬ ፎረሸ» ብለዋል።  የሁሉም አስተያየት ውጤት ላይ ማነጣጠሩ ግልፅ ነው።

 ሸዋዬ ለገሠ

ተስፋለም ወልደየስ