ክረምቱና የአዉሮጳ ክራሞት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 22.12.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ክረምቱና የአዉሮጳ ክራሞት

በአዉሮጳ የተናፈቀዉ በረዶ ባለፈዉ ሳምንት መገባደጃ ላይ ከባድ ቅዝቃዜዉን ጭኖ ከተፍ ብሏል።

default

በክፍለ ዓለሙ ብርድ ለህልፈተ ህይወት የዳረጋቸዉ ወገኖች ቁጥር 80መድረሱን ትናንት የወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ። ፖላንድ ዉስጥ ከዜሮ በታች 20ዲግሪ ዝቅ ያለዉ የአየር ሁኔታ አብዛኞቹ የጎዳና ተዳዳሪዎች መሆናቸዉ ለተገለፀ ለ42 ሰዎች ህልፈተ ህይወት ምክንያት ሆኗል። ዑክሬን 18ሰዎች በቅዝቃዜዉ ሲሞቱ ፈረንሳይ በበኩሏ ሁለት አልቦ ቤት የነበሩ ሰዎች መሞታቸዉን አስታዉቃለች። የመጓጓዣ ስልቶችን ሳይቀር ከመርሃ ግብራቸዉ ያዛባዉ በረዶና ቅዝቃዜ የበርካታ መንገደኞችን ጉዞ አስተጓጉሏል። ጀርመን ፤ፈረንሳይ፤ ኔዘርላንድ፤ ፖርቱጋልና ስፔን በርካታ በረራዎች ሰርዘዋል። ከአንዱ ወደሌላዉ የአዉሮጳ አገር የሚያስተላልፉ አዉራ መንገዶችም በተከመረባቸዉ 20 ኢንች የሚሆን በረዶ ምክንያት አገልግሎታቸዉ ተስተጓጉሏል። ከፓሪስ በብራስልስ ወደለንደን በሚወስደዉ የባህር ዉስጥ መንገድ ንብረትነቱ ዩሮስታር የተሰኘዉ የመጓጓዣ አገልግሎት የሆነ ባቡር ተበላሽቶ መገተር አዉሮጳ በዘንድሮዉ ክረምት የገጠማት ትርምስ አመላካች ተደርጎ ተወስዷል። ባለፈዉ አርብ አምስት አገር አቋራጭ ባቡሮች በመተላለፊያዉ መስመር ዉስጣ እንዳሉ ሲበላሹ ከ2,000 በላይ መንገደኞች ከምድር በታች በከፍተኛ ስጋት እንደተዋጡ ለመቆየት ተገደዋል። ዩሮስታር ባቡሮቹን ለብልሽት የዳረገዉ ከዉጭ ያለዉ ቀዝቃዛ አየር ወደመሸጋገሪያዉ የምድርና ባህር ዉስጥ መስመር ሲገባ ከሚያጋጥመዉ ሞቃት አየር ጋ መጋጨቱ መሆኑን ተናግሯል። የፈረንሳይ መንግስት ግን ምክንያቱ እንዲጣራ ጠይቋል። የጉዞ መርሃግብሩ መስተጓጎልም የመንገደኞችን እቅድ አዛብቷል። በጎዳና የተከመረዉ በረዶ ተሽከርካሪዎችን ለግጭት ተሳፋሪዎችን ለህልፈተ ህይወትም ዳርጓል። ፓሪስ ዉስጥ በበረዶ ተንሸራቶ መንገዱን የሳተ መኪና ከባቡ ተጋጭቶ 36 ሰዎች ሞተዋል ባቡሩ ተጨማሪ 300 ሰዎችን ጭኖ እንደነበር ተመልክቷል። በክሮሺያ ዋና ከተማ ዛግሬብ አንድ ባቡር ግጭት ደርሶበት 52ሰዎች መጎዳታቸዉ ተመዝግቧል። የአገሪቱ አደጋ መርማሪዎች ባቡሩ ለመቆም የሚያስችለዉ ልጓም ወይም ፍሬን ከስራ ዉጪ እንዲሆን ያበቃዉ ከዜሮ በታች 17 ዲግሪ የወረደዉ ቅዝቃዜ ነዉ ሲሉ የክረምቱን ብርድ ክብደት ጠቁመዋል። በፈረንሳይ ደግሞ በኮረንቲ መስመሮች ላይ በደረሰ ከፍተኛ ጫና ሁለት ሚሊዮን ሰዎች አገልግሎት እንዲቋረጥባቸዉ ምክንያት ሆኗል።

Schnee auf Flughafen Frankfurt am Main

ጀርመን ፍራንክፈርት አዉሮፕላን ማረፊያ

የክረምቱ በረዶና ብርዱ ያስተጓለዉ የአየር በረራዉን ጭምር እንደመሆኑ በአምስተርዳሙ ሺፖል የአየር ማረፊያ 700 መንገደኞች በተጣጣፊ አልጋዎች ምሽቱን ተኮራምተዉ እንዲያሳልፉ አስገድዷል። በርካታ በረዶ መዉረዱን ተከትሎም አዉሮፕላኖች እሁድ ማምሻዉን መሬት እንዲይዙ ተደርጎ ብዙ በረራዎች ተሰርዘዋል። በጀርመን እንዲሁ ከባድ በረዶ በመጣሉ በረራዎች ሰዓት አለማክበራቸዉ እንዳለ ሆኑ በፍራንክፈርትና ዱይስልዶርፍ አዉሮፕላን ማረፊያዎች እሁድ 500 በረራዎች ተሰርዘዋል። ሰኞ እለት ፈረንሳይ ከፓሪስ ቻርለስ ደጎል አዉሮፕላን ማረፊያ ከነበሯት 20በመቶዉን በረራ ሰርዛለች። ስፔን እንዲሁ 174በረራዎችን በአየር ጠባዩ ምክንያት ለመሰረዝ ተገዳለች። በሩሲያ ሞስኮ ከተማ የወረደዉን በረዶ ለመጥረግ 13,000 ገልባጭ ተሽከርካሪዎች መሰማራታቸዉን ባለስልጣናት ተናግረዋል፤ ያም በተከመረዉ በረዶ ላይ ተጨምሮ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅን አስከትሏል። በአገሪቱ ባለፈዉ እሁድ የወረደዉ በረዶ ከዛሬ አንድ መቶ ዓመታት በፊት የታየ መሆኑ ተነግሯል። በተመሳሳይ ከአትላንቲክ ማዶ በሰሜን ምስራቅ ዩናይትድ ስቴትስ የወረደዉ በረዶ በአንዳንድ አካባቢዎች እስከ 60ሴንቲሜትር ከፍታ ድረሱ ተገልጿል።

BdT Deutschland Wetter Winter in Schwarzwald

በአዉሮጳም ክረምቱ ገፍቶ ከመምጣቱ በፊት በዘንድሮዉ የገና በዓል በረዶ ይኖር ይሆን የሚል ስጋት እንዳልነበረ ሁሉ ከዓርብ ጀምሮ የወረደዉ መጠኑ ከፍ ያለዉ በረዶ የበዓሉን ድባብ ከቅዝቃዜዉ ባሻገር እንዳደመቀዉ የሚናገሩም አልጠፉም። እንደአየር ጠባይ ትንበያዉ ከሆነ በረዶዉ ለቀጣይ ቀናት እያዘናጋ መዉረዱ አይቀርም፤ የተጓጓለት ነጩ ገናም በነጩ በረዶ ይታጀብ ይሆናል። ያ ካልሆነም ቅዝቃዜዉ ከብዶ የሚቀጥል ይመስላል።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ