ኬንያ ዉስጥ የቀጠለዉ ተቃዉሞ | አፍሪቃ | DW | 07.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ኬንያ ዉስጥ የቀጠለዉ ተቃዉሞ

ትናንት ኬንያ ዉስጥ መንግሥትን በመቃወም የተካሄዱ ሰልፎች ፍፃሜያቸዉ የሰዉ ሕይወት የጠፋበት ግጭትና አመፅ እንደነበር ዘገባዎች ያሳያሉ። የሀገሪቱ የተቃዉሞ ፖለቲካ ፓርቲ ጥምረት ለለዉጥ እና ዴሞክራሲ በእንግሊዝኛ ምህጻሩ CORD በተለይ ኪሱሙ በተሰኘችዉ ከተማ ለሶስተኛ ጊዜ ያካሄደዉ ታላቅ የተቃዉሞ ሰልፍ በፖሊስ ተኩስ ተበትኗል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:43

ተቃዉሞ በኬንያ

በተኩሱም የሁለት ሰዉ ሕይወት መጥፋቱ 61 ሰዎችም በጥይት ይና ስለት ተጎድተዋል።

ጥምረት ለለዉጥ እና ዴሞክራሲ፤ CORD ካለፈዉ ሚያዝያ ወር አንስቶ ነዉ በየሳምንቱ ሰኞ፤ ሰኞ የተቃዉሞ ሰልፎችን በተለያዩ የኬንያ ከተሞች የሚያካሂደዉ። ዋና ጥያቄዉ በመጪዉ ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ከሚካሄደዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ አስቀድሞ የኬንያ የምርጫ ኮሚሽን ይለወጥ የሚል ነዉ። የትናንትናዉን ጨምሮ ባለፉት አምስት ሰኞዎች የተካሄዱት የተቃዉሞ ሰልፎች በሰላማዊ መንገድ አልተጠናቀቁም። ፖሊስ ሰልፈኞቹን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ እና የፕላስቲክ ጥይት ብቻ ሳይሆን፤ ሕይወት የሚቀጥፍ እና የሚጎዳ አረሩንም በመጠቀሙ ሰዎች ተገድለዋል፤ ተጎድተዉም ሃኪም ቤት ገብተዋል። አመፅና ግጭቱ ያስከተለዉ ጉዳት ግን የተቃዉሞ ጥያቄ አቅራቢዎቹን ተስፋ አላስቆረጠም። እንደዉም ጥያቄያቸዉ ጆሮ አግኝቶ ለዉይይት በር ካልተከፈተ ሰልፍ የሚካሄድበት ቀን ከአንድም ሁለት ሊሆን እንደሚችል በኬንያ ምክር ቤት የተቃዉሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት የሆነዉ CORDን ወክለዉ አባል የሆኑት ጆንሰን ሙታማ ይናገራሉ።

« ለመንግሥት ይህን ሰላማዊ ሰልፍ ሰኞ ሰኞ እያካሄድን ነዉ፤ እናም ዉይይት እንዲካሄድ ካልፈለግህ፤ አስተዉል፤ ሰኞ እና ሐሙስም እናደርገዋለን እያልነዉ ነዉ። ሁለት ሳምንት ሰጥተናቸዋል፤ አዎንታዊ ምላሽ ካልሰጡን በሳምንት አራት ቀን እናደርገዋል። ከዚያም በሳምንት ሰባቱንም ቀን እናደርገዋለን፤ እያለም ያለማቋረጥ ለ24 ሰዓታት ይሆናል። ዴሞክራሲን ለማግኘት ምን ማድረግ እንደሚገባ እናሳያለን። ጎዳናዎች ላይ እንቀመጣለን፤ መንገድ ላይ እንተኛለን። እኛ በምንገኝበት ስፍራም ብስክሌት እንኳ የማለፍ ዕድል አይኖረዉም።»

ትናንት የCORD ጠንካራ ይዞታ እንደሆነ በሚነገርለት እና የኬንያዋ ሦስተኛ ትልቅ ከተማ ኪሱሙ የተካሄደዉ የተቃዉሞ ሰልፍ ቢያንስ የሁለት ሰዉ ሕይወት ጠፍቶበትና በርካቶችም በጥይት ተጎድተዉበት ነዉ ያከተመዉ። ፖሊስ ለሚተኩሰዉ ጥይት ተሰላፊዎቹ በድንጋይ መልስ ሲሰጡ እንደነበር ነዉ የተገለጸዉ። ከዚህ በተቃራኒዉ ዋና ከተማ ናይሮቢ ላይ ትናንት ሰኞ የተካሄደዉ ሰልፍ ከሌላዉ ጊዜ የተረጋጋ እንደነበር ቢነገርም ፖሊስ ግን እዚህም ሰልፈኞችን ለመበተን ጠንከር ያለ ኃይል መጠቀሙን ይናገራሉ። በናይሮቢ የፍሬድሪክ ኤበርት ተቋም ተጠሪ ዶክተር ሃይንስ ቦንጋርትስ ፖሊስ ሰልፉን ለመቆጣጠር፤ ተሰላፊዎቹም እጅ ላለመስጠት የተፋጠጡ ይመስላል ይላሉ።

«ፖሊስ እንደተናገረዉም ሆነ እስካሁን ሲያደርግ እንደሚታየዉ ባለን ኃይል ሁሉ የሚያስፈልገዉን እናደርጋለን ነዉ። ዉኃ የሚተፉ ተሽከርካሪዎችን እና አስለቃሽ ጭስ ይዘዉ ወዲህ ወዲያ ሲሯሯጡ የእርስ በርስ ጦርነት ያለ ነዉ የሚመስለዉ። ይህ ደግሞ በይፋ የመንግሥት ድጋፍ አለዉ። እናም ለተመለከተዉ በፖሊስ እና በተቃዋሚዎች መካከል የሚካሄድ ፍጥጫ ይመስላል።»

ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ሙስና ተንሰራፍቶበታል፤ ባለስልጣናቱም ገለልተኛ አይደሉም ያሉት የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን እንዲለወጥ ግፊታቸዉን ቀጥለዋል። መንግሥት የሚቀርብበትን ክስ ያዉቃል፤ በዚህ ምክንያትም ተቃዋሚዎቹ ላይ ጫናዉን አጠናክሯል። የሀገሪቱ የፖሊስ አዛዥ ጃፔት ኮሜ ባስተላለፉት ይፋዊ ማስጠንቀቂያ « ነፍሳችሁን የምትወዷት ከሆነ በሰልፉ እንዳትሳተፉ፤» ሲሉ ቁርጥ ያለ ዛቻ አሰምተዋል። እንዲያም ሆኖ በየሰኞዉ ዕለት በሺዎች የሚገመቱ በየከተማዉ ለሰልፍ ይወጣሉ። ዶክተር ሃይንስ ቦንጋርትስ እንደሚሉት በሰልፉ የሚሳተፉት አንዳንድ ወጣቶች ሥራ በማጣታቸዉ ተስፋ የቆረጡ ዓይነት ናቸዉ። እዚያ በመገኘታቸዉ ገንዘብ ሊከፈላቸዉ ይችላል። በሰልፉ ወቅትም የተዘረፉ ሱቆችም አሉ። በሌላ በኩል የኬንያ ፖለቲካ ሲታይም ይላሉ፤ የሰልፉን ዓላማ መስመር ለማሳት ተሰላፊዎቹ በሌላ አካል ገንዘብ ተከፍሏቸዉ ይሆናል። ኬንያ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2007ዓ,ም ከምርጫ ጋር በተያያዘ አመፅ እና እምቢታ ከ1ሺህ የሚበልጡ ዜጎች የሞቱባት ሀገር ናት። ፖሊስ ከሁለት ሳምንታት በፊት በዚህ የተቃዉሞ ሰልፍ ከተሳተፉት ሁለት ገድሏል። ትናንትም እንዲሁ፤ እስከሚመጣዉ ነሐሴ ምን ያህሉን ይቀጥፈዉ ይሆን?

አንቶኒዮ ካስካስ/ ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic