ኬንያ እና ድጋሚው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ | አፍሪቃ | DW | 11.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ኬንያ እና ድጋሚው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ

የኬንያ ከፍተኛ ፍ/ቤት ባለፈዉ ነሐሴ ስምንት፣ 2017 ዓም የተደረገዉ ፕ/ምርጫ የሀገሪቱ ሕ/መንግሥትና ሕግ በሚያዙት መሰረት ባለመደረጉ ዉጤት ዋጋ ቢስ ነው በሚል ዉጤቱን ዉድቅ አድርጎ፣ ምርጫው በ60 ቀናት ድጋሚ እንዲካሄድ መበየኑ ይታወቃል። ብይኑን ተከትሎ የሀገሪቱ አስመራጭ ኮሚሽን ምርጫው እአአ ጥቅምት 17፣ 2017 ዓም እንዲደረግ ወስኗል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 06:44
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
06:44 ደቂቃ

ኬንያ

የፕሬዚደንታዊ ምርጫ ውጤት ቆጠራ ያልተስተካከለ አሰራር ታይቶበታል በሚል ሲሰረዝ የኬንያው በአፍሪቃ የመጀመሪያው ነው። ተፎካካሪዎቹ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ራይላ ኦዲንጋ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንደሚቀበሉ ቢያስታውቁም፣ ኬንያታ ቆየት ብለው ለደጋፊዎቻቸው ባሰሙት ንግግር ብይኑን ያሳለፉትን ዋና ዳኛ ዴቪድ ማራጋን ወንጀለኛ ከማለታቸውም ሌላ፣ ድጋሚ ቢመረጡ በፍትሑ አውታር ላይ ርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል።

ይህ ያስቆጣቸው በኮራያንጎ ሶቲያንጎ የሚመሩት የኬንያ ሲቭል ማህበረሰብ ቡድኖች፣ እንዲሁም፣ የኬንያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኬንያታ ይቅርታ እንዲጠይቁ አሳስበዋል። የመብት ጠበቃ እና የሲቭል ማህበረሰብ አባል ንጆንጆ ሙዬ  የኬንያታ አስተያየት ሕገ ወጥ ነው ብለዋል።
« ፕሬዚደንት ኬንያታ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ዋና ዳኛ አንጻር መጮሀቸው ፣ መሳደባቸው፣ በፍትሑ አውታር አኳያ ያሰሙት የማስፈራራት ዛቻ እና የፍትሑንም አውታር የማስተካከል እቅድ እንዳላቸው መናገራቸው አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን ሕገ ወጥም ነው። እና ይህች ሀገር ካለፈው ነሀሴ 27፣ 2010 ዓም ወዲህ በስራ ላይ በዋለው የኬንያን ሕዝብ ፍላጎት በሚወክለው  ሕገ መንግሥት እንደምትመራ ፕሬዚደንቱ  ሊረዱት ይገባል። » 
በኬንያ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የተወዳደሩት የተቃዋሚው ቡድን እጩ ራይላ ኦዲንጋም  ሕጋዊ እና ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ካላገኙ በድጋሚው ፕሬዚደንታዊው ምርጫ ላይ እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል።

አዲንጋ እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫው ዕለትም እንዲቀየር ከመጠየቃቸው ጎን እስከምርጫው ዕለት በርካታ ጥያቄዎች እንዲሟሉ ቅድመ ግዴታ አሳርፈዋል።
የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ አሸነፉ የተባለበትን ምርጫ ውጤት ውድቅ በማድረግ ድጋሚ ይደረግ ያለውን ምርጫ ለሚቆጣጠረው ቡድንም የሀገሪቱ አስመራጭ ኮሚሽን ፣ በምህፃሩ አይኢቢሲ ስድስት አዳዲስ ባለስልጣናት መሾሙን የአይኢቢሲ ሊቀ መንበር ዋፉላ ቼቡካቲ አስታውቀዋል። 
ተቆጣጣሪው ቡድን ላይ የተደረገው ለውጥ የተቃዋሚው ቡድን እጩ ራይላ ኦዲንጋ አስመራጩ ኮሚሽን እንዲቀየር ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ሳይሆን እንዳልቀረ ተገምቷል። 
 ይሁንና፣ የራይላ ኦዲንጋህብረት ናሳ እና የተፎካካሪያቸው ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ የጁብሊ ፓርቲ በአስመራጩ ኮሚሽን አዲስ አወቃቀር እንዳልተደሰቱ በማመልከት ቅሬታቸውን ገልጸዋል።  በፕሬዚደንታዊው ምርጫ የራይላ ኦዲንጋ አጋር  ካሎንዞ ሙሶዮካ ተዓማኒ ምርጫ ለማካሄድ ከተፈለገ በአስመራጩ ኮሚሽን ውስጥ፣ የአስመራጩ ኮሚሽን ዋና ስራ አስኪያጅ እዝራ ቺሎባን የመሰሉ ባለስልጣናት ሊነሱ እንደሚገባ ቀደም ሲል ገልጸው ነበር።


«  ኬንያ ውስጥ ፍትሕ እንዲሰፍን ከተፈለገ  ቺሎባ መነሳት አለባቸው። በግሌ በወጣቱ ቺሎባ አንጻር ተቃውሞ የለኝም፣ ግን፣ ለኬንያ ዜጎች ትክክለኛውን ነገር ካልሰራህ፣ የሀገርህ ጠላት ነው የምትሆነው ብዬ ነው የማስበው። »   
የጁብሊ ፓርቲም  ለአስመራጩ ኮሚን ሊቀ መንበር በጻፈው ደብዳቤ ከምርጫ ተቆጣጣሪው ቡድን  አባላት መካከል ዘጠኙ ወገንተኞች ናቸው ብሏል። ከስልጣናቸው የተነሱት የአስመራጩ ኮሚሽን ዋና ስራ አስኪያጅ እዝራ ቺሎባ እና አምስት አቻዎቻቸው የኮሚሽኑንን ውሳኔ በመቃወም በሰራተኛ ጉዳዮች ተመልካች ፍርድ ቤት ክስ መስረተዋል፣ ሆኖም የናይሮቢው የዶይቸ ቤለ ወኪል ጄምስ ሺማንዩላ እንደገለጸው፣ፍርድ ቤቱ ጥያቄአቸውን አልተቀበለውም።
« ፍርድ ቤቱ አስመራጩ ኮሚሽን ቺሎባን እና ሌሎቹን አምስት አቻዎቻቸውን ከስልጣናቸው እንዲነሱ የደረሰውን ውሳኔ ለማስቆም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል፣ በዚህ ፈንታ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ወገኖች ሁሉ በጎርጎሪዮሳዊው መስከረም 20፣ 2017 ዓም ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ አዟል። »
ኡሁሩ ኬንያታ እና ራይላ ኦዲንጋ አስመራጩ ኮሚሽን የሾማቸውን ስድስት ባለስልጣናት የሚተኩ ሰዎችን ስም ለኮሚሽኑ አቅርበዋል። ይሁን እንጂ፣ የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ዋፉላ ቼቡካቲ፣ የኬንያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 249 ን በመጥቀስ በሰጡት ምላሽ  ኮሚሽኑ  ነፃ አካል እንደመሆኑ መጠን ማንምሰው ሆነ ባለስልጣን  ፍላጎቱን ሊጭንበት እንደማይችል አመልክተው የኬንያታና የኦዲንጋን ጥያቄ አጣጥለዋል። 
ምርጫው በኡሁሩ ኬንያታ እና ራይላ ኦዲንጋ መካከል ይካሄድ መባሉ የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ብይን የማያንፀባርቅ እና ሌሎቹን ፕሬዚደንታዊ እጩዎች የሚያገል ነው ያሉት አንዱ ቶፎካካሪ የነበሩት ዶክተር ኤኩሩ አውኮት በድጋሚው ምርጫ ስምንቱም እጩዎች እንዲሳተፉ በመጠየቅ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ክስ እንደሚመሰርቱ አስታውቀዋል።  በተቀናቃኞቹ እጩዎች መካከል በቀጠለው ውዝግብ የተሰላቸው የኬንያ ሕዝብ የድጋሚው ምርጫ ዕለት ደርሶ ድምፁን የሚሰጥበትን ዕለት በጉጉት እየተጠባበቀ ይገኛል።

ይህ በዚህ እንዳለ፣ የመብት ጠበቃ እና የሲቭል ማህበረሰብ አባል ንጆንጆ ሙዬ  ለዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ግልጽ መልዕክት አስተላልፈዋል። 
« ከውጭ ሀገራት የመጡት የምርጫ ታዛቢዎች ኬንያውን ድምፃቸውን በሰልፍ ስርዓት ጠብቀው ሲሰጡ በማየታቸው ብቻ ምርጫውን ትክክለኛ ነው ብለውታል ።  ግን በ2007፣ 2013 እና በዘንድሮው ምርጫ ያየነው ነገር፣ የኬንያ ምርጫ በምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ አይደለም የሚጨበረበረው።  ይህ በ90ኛዎቹ ዓመታት የሚደረግ ነበር።  አሁን ግን  የሚጭበረበረው በድምፅ ቆጠራው እና ውጤቱን በማስተላለፉ ወቅት ነው። እና እኛ ታዛቢዎቹን የምንነግራቸው  ምርጫ ሊታዘቡ የሚመጡ ከሆነ፣   መታዘብ ያለባቸው ምርጫውን እንጂ ፣  አፍሪቃውያን በሰልፍ ድምፅ መስጠት  መቻላቸውን እንዳልሆነ ነው። »

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች