ኬንያ እና የፀረ ሽብር ዘመቻ ሰለባዎች | አፍሪቃ | DW | 21.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ኬንያ እና የፀረ ሽብር ዘመቻ ሰለባዎች

የመብት ተሟጋቹ ድርጅት «ሂውመን ራይትስ ዎች» የኬንያ ፀጥታ ባለስልጣናት በሶማልያ ዓማፅያን ቡድን አሸባብ አንፃር የሚያካሂዱትን ፀረ ሽብር ትግል እና መዘዙን አስመልክቶ ትናንት አንድ ዘገባ አውጣ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:13

ኬንያ

ዘገባው ባለፉት ሁለት ዓመታት ብዙ ኬንያውያን የት እንደደረሱ ሳይታወቅ ጠፍተዋል፣ ካለፍርድ ተገድለዋል ፣ በዚሁም ተግባር ላይ የሀገሪቱ ጦር እና ፀጥታ ኃይላት እጅ አለበት ሲል ወቀሳ ሰነዝሮዋል።የፀጥታ ኃያላት ሽብርተኝነትን ለመታገል የሚጠቀሙበት ዘዴ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በመዲናይቱ ናይሮቢ እና በሰሜን ምሥራቃዊ የሀገሪቱ አካባቢ ቢያንስ 32 ዝርያቸው ከሶማልያ የሆኑ ኬንያውያን ለጠፉበት እና 11 ካለፍርድ ለተገደሉበት ድርጊት ተጠያቂ መሆኑን የመብት ተሟጋቹ ድርጅት «ሞት እና መሰወር» የሚል ርዕስ በሰጠው 87 ገጾች በያዘው ዘገባው ብርቱ ክስ ሰንዝሮዋል። 11 ኬንያውያን በዚህ በተያዘው አውሮጳዊ 2016 ዓም ተገድለው የተገኙት ለጥያቄ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ እንደነበር የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ኬኔት ሮት ገልጸዋል።
« «ሂውመን ራይትስ ዎች» በሰሜን ምሥራቃዊ ኬንያ ሰዎች ሳይታወቅ የሚጠፉበት አስደንጋጭ አሰራር
መኖሩን ደርሶበታል። ብዙዎቹ የዚሁ አሰራር ሰለባዎች ዝርያቸው ከሶማልያ የሆኑ ኬንያውያን እና ሙስሊሞች ናቸው። ሰለባው ምንም እንኳን በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ መኖሩ ባይመዘገብም ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲመጣ ይደረጋል። »
ኬንያ በአሸባብ አንፃር ክትትሏን ያጠናከረችው ያማፂው ቡድን እጎአ በ2015 ዓም በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ 140 ተማሪዎችን ከገደለ በኋላ ነው። ሽብርተኝነት አሳሳቢ ስጋት ቢደቅንም፣ ካለፍርድ የሚፈፀም ግድያ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ነው «ሂውመን ራይትስ ዎች» ያስታወቀው።


« ሽብርተኝነት ለደቀነው አሳሳቢ ስጋት መልሱ፣ ሰዎቹን ማሰር፣ ክስ መመስረት እና ለፍርድ ማቅረብ ይሆናል። እንዲሰወሩ ማድረግ አይደለም። ይህ ክትትሉ ባተኮረባቸው ማህበረሰቦች ዘንድ ጥላቻ እንዲስፋፋ ነው የሚያደርገው፣ አሸባብም የሚፈልገው ይህንኑ ነው። »
የ«ሂውመን ራይትስ ዎች» ተመራማሪ ኦሲየን ኦኝያሙያ አንድ በጦር ኃይሉ ተሽከርካሪ ይጓዙ በነበሩ አራት የኬንያ መከላከያ ኃይል አባላት የታሰሩት ኑር አብዲዋሀድ ዲስ የተባሉ አንድ ሙስሊም ባለመደብር የት እንደደረሱ ሳይታወቅ መሰወራቸውን ተናግረዋል።
« የአብዲዋሀድ አስከሬን ከታሰሩ ከአምስት ቀናት በኋላ፣ ባለፈው ሚያዝያ አምስት፣ 2016 ዓም ተገኝቶዋል። የተገኘውም ከታሰሩበት ቦታ 50 ኪሎሜትር ርቆ ባለው ፊኖ በተባለ ቦታ ነው። አስከሬናቸው ሶስት ጊዜ በጥይት፣ ማለትም ፣ ራሳቸው እና ሁለት ትከሻዎቻቸው ላይ ተመተው እንደተገደሉ ያሳያል። »
ከአሸባብ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች በጦር እና ፀጥታ ኃይላት ከታሰሩ በኋላ፣ ክስ ሳይመሰረትባቸው አንዳንዴ ዓመታት እንደሚያልፉ፣ ወይም የት እንደተወሰዱ ሳይታወቅ በዚያው እንደሚሰወሩ፣ ዘመዶቻቸውም የት እናዳሉ መንግሥትን ቢጠይቁም መልስ ሳያገኑ እንደቀሩ የድርጅቱ ዘገባ አሳይቶ፣ ከአሸባብ ጥቃት ከለላ ሊደረግለት የሚገባውን በሰሜን ምሥራቃዊ ኬንያ የሚኖረውን ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው በደል ትልቅ ወንጀል ከመሆኑም በላይ በፀጥታ ኃይላት አኳያ ፍራቻ እና ጥርጣሬ እንደሚፈጥር ገልጾዋል።
ዘገባውን ያወጣው በጋሪሳ፣ ዋጂያ እና ማንዴራ የ117 ሰለባዎችን እና ያይን እማኞችን አነጋግሮ ሲሆን፣ ለኬንያ ፖሊስ፣ ጦር ኃይል ፣ ለመከላከያ እና ለሀገር አስተዳደር ሚንስቴሮች፣ እንዲሁም ፣ በግድያው እና ሰዎች በተሰወሩበት ወንጀል እጃቸው አለበት ለተባሉት ወገኖች ሁሉ ደብዳቤ ቢጽፍም መልስ አለማግኘቱን ገልጾዋል።

አንድሩ ዋሲኬ

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic