ኬንያ እና የገጠማት የክፍፍል ስጋት | አፍሪቃ | DW | 02.12.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ኬንያ እና የገጠማት የክፍፍል ስጋት

በኬንያ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ባለፈው ሰኞ፣ ህዳር 18፣ 2017 ዓም ቃለ መሀላ የፈፀሙት ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በፖለቲካ ውዝግብ የተከፋፈለችውን ሀገራቸው አንድ ለማድረግ ቃል መግባታቸው የሚታወስ ነው። ይሁንና፣ በፕሬዚደንታዊው ምርጫ ውጤት ሰበብ በተፎካካሪዎቹ እጩዎች ደጋፊዎች መካከል የተፈጠረው ልዩነት የሚጠብ አይመስልም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:06

ኬንያ

እአአ ነሀሴ ስምንት፣ 2017 ዓም የተካሄደው የመጀመሪያው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ውጤት ተጭበርብሯል ሲሉ ተቃዋሚዎች ከከሰሱ በኋላ የኬንያ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ከተሰረዘ እና ሁለተኛው ፕ/ምርጫ ባለፈው ጥቅምት 26፣ 2017 ዓም እንዲደረግ ከተወሰነ በኋላ በተከተሉት ወራት በተከሰቱ ግጭቶች ብዙዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። የተቃዋሚዎቹ እጩ ራይላ ኦዲንጋ ራሳቸውን ባገለሉበት ሁለተኛው ፕ/ምርጫ  ምርጫ ኬንያታ 98 ከመቶ ድምጽ አግኝተዋል ቢባልም፣ ተቃዋሚዎች ውጤቱን ያጣጣሉበት ድርጊት ፣ በኬንያ ሰላም እንደገና የሚወርድበት ሁኔታ የገጠመውን ተግዳሮት አሳይቷል።በፖለቲካ ታዛቢዎች አስተያየት መሰረት፣ ብዙዎቹ የኬንያ ዜጎች ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በተመረጠው መንግሥት ላይ እምነት የላቸውም። ይህም በሁለተኛው ዙር ፕ/ምርጫ ላይ በግልጽ ነበር የታየው። ያኔ ድምፁን መስጠት ከነበረበት ሕዝብ መካከል በምርጫው 39 ከመቶ ብቻ  መሳተፉ በሀገሪቱ ያለውን ሁኔታ ገላጭ መሆኑን ከዶይቸ  ቬለ ጋር ቃለ ምልልስ ያካሄዱት ናይሮቢ የሚገኘው የጀርመናውያኑ የፖለቲካ ጥናት ተቋም ፣ የሀይንሪኽ በል ሽቲፍቱንግ ስራ አስኪያጅ ኡልፍ ተርሊንደን ተናግረዋል።
« የምርጫው ሂደት በጠቅላላ ሀገሪቱን ከፋፍሏል። እርግጥ ፣ የተቃዋሚው ወገን ባንድ በኩል ራሱን ከሁለተኛው ፕ/ምርጫ አርቋል። ይሁንና፣ ይኸው ርምጃው የፈለገውን ውጤት አላስገኘለትም። በዚህም የተነሳ አሁን ኃይሉን ለማሳየት ሲል ቢያንስ ውዝግቡ እንዲቀጥል ለማድረግ ወይም ከተቻለም ለማባባስ እየሞከረ ነው።  እና ሁለተኛ ፕሬዚደንት ቃለ መሀላ እንዲፈፅም ማድረግ፣ መንግሥት በዝምታ የማያልፈው ትንኮሳ ነው። » 

የተቃዋሚዎች መሪ ራይላ ኦዲንጋ ኡሁሩ ኬንያታ ለሁለተኛ ዘመነ ሥልጣን ቃለ መሀላ በፈፀሙበት ዕለት ፣ የምርጫው አሸናፊ እሳቸው እንደሆኑ በማመልከት የፊታችን ታህሳስ 12፣ 2017  ቃለ መሀላ ለመፈፀም መወሰናቸውን አስታውቀዋል። ለዚህም ኦዲንጋ ፕሬዚደንት ብሎ የሚሰይማቸው የሕዝብ ሸንጎ ለማቋቋም ወስነዋል። ይህ ርምጃቸው ግን እንደ ታዛቢዎች ግምት፣ በሀገር ክህደት እንዳያስመሰርትባቸው ያሰጋል። 
ኡልፍ ተርሊንደን እንደሚሉት፣ የተቃዋሚው ወገን የሁለተኛው ፕ/ምርጫ ሕጋዊነት ማጠያየቅ መቀጠሉ ኬንያን አዳጋች ሁኔታ ውስጥ ጥሏታል።
« ችግሩ፣ ምንም እንኳን የመጀመሪያው ፕ/ምርጫ ውጤት ከተሰረዘ በኋላ የታየው የፖለቲካ ሂደት ሕግን የተከተለ ቢሆንም፣ በሕዝብ ዘንድ ታማኝነቱ እንዳጠያየቀ ይገኛል።  በኬንያ ያለው ታሪካዊ ውዝግብ በድርድር ብቻ የሚፈታ አይደለም። በኬንያ የቆዩትን ለምሳሌ፣ የመሬት ጉዳይን የመሳሰሉ ኢፍትሓዊ አሰራሮችን አስወግዶ ማህበረሰባዊውን ሰምምነት መልሶ ማደስ የሚያስችል ውይይት ማካሄድ ይቻላል ወይ ነው ጥያቄው።  ይህ ሲሆን ብቻ ነው ኬንያ ወደፊት መራመድ የምትችለው። አሁን ያለው ሁኔታ ግን ይህን የሚያበረታታ አይደለም። »
ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የኪኩዩ ጎሳቸው የማይገባቸውን መሬት በይዘዋል በሚል አብዝተው ይወቀሳሉ። ይህንኑ በመሬት ባለቤትነት ጥያቄ  ሰበብ የሚታዩትን ኢፍትሓዊ አሰራርን የሚያጣራ ኮሚሽን እንዲቋቋም የቀረበውን ሀሳብ  ግን የሀገሪቱ መንግሥት አልተቀበለውም።   

ሆኖም፣ በኬንያ እርቀ ሰላም እንዲወርድ ከተፈለገ ፣ ምንም እንኳን አዳጋች ቢሆንም፣ ውይይት ብቸኛው መንገድ ነው ብለው እንደሚያስቡ ነው ኬንያዊው የፖለቲካ ተንታኝ ማርቲን ኦሎ የገለጹት። 
« በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ በሚታዩት ሁኔታዎች ትልቅ ቅሬታ ነው ያለው። ምክንያቱም፣ ራይላ ኦዲንጋ እና ተቃዋሚዎቹ በኬንያታ ለሚመራው የሀገሪቱ መንግሥት እውቅና አልሰጡም።  ራይላ ኦዲንጋን ሕጋዊው የሀገሪቱ መሪ ለማድረግ የሚችሉበትን ሂደት ነው ለመጀመር የፈለጉት። »


ተቃዋሚዎች ብሔራዊ ሸንጎ ለማቋቋም የወጠኑት እቅዳቸው ግን ችግር ውስጥ እንደሚጥላቸው የፖለቲካ ተንታኙ ማርቲን ኦሎ ገምተዋል።
« የተቃዋሚው ወገን በዚህ አካሄዱ ከቀጠለበት እና መንግሥትም በሀገሪቱ የሚታየውን ክፍፍል ለማጥበብ ካልሞከረ፣ ክፍፍሉ ይበልጡን ይሰፋል፣ በተለያዩት ጎሳዎችም መካከል ያለው ውጥረትም ይበልጡን ይካረራል፤ ይህም፣ መንግሥት እንደሚፈልገው ስራውን እንዳያከናውን ያከላክለዋል። »
ማርቲን ኦሎ እንደሚሉት፣ ለፖለቲካዊው ክፍፍል ለብዙ አሰርተ ዓመታት የቀጠሉት ጎሳ ነክ ውዝግቦች ተጠያቂ ናቸው።  
ኬንያ በጎርጎሪዮሳዊው 1963 ዓም ከብሪታንያ ነፃነቷን ካገኘች ወዲህ ትልቁ የሆነው የኪኩዩ ጎሳ በሀገሪቱ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳረፉ ይነገራል። ኬንያን ከመሩት አራት ርዕሳነ ብሔር መካከል ከዳንኤል አራፕ ሞይ በስተቀር፣ መስራች አባት ኮሞ ኬንያታ፣ ልጃቸው ኡሁሩ ኬንያታ እና ምዋይ ኪባኪ የኪኩዩ ጎሳ  አባላት ናቸው።  በመሆኑም፣ ከሉዎ ጎሳ የሚወለዱት የተቃዋሚው ቡድን እጩ ራይላ ኦዲንጋን የመሳሰሉት የሌሎች ጎሳ ተወላጆች የተገፉ ያህል እንደሚሰማቸው የፖለቲካ ጠበብት ይናገራሉ።
« ሀገሪቱን ከምትገኝበት ክፍፍል ለማዳን እና እርቀ ሰላም ለማውረድ የሚቻልበትን ውይይት ለመጀመር አሸናፊው ፕሬዚደንት ትልቅ ትሕትና፣ ተሸናፊው የተቃዋሚ ቡድን እጩ ደግሞ ትልቅ ቆራጥነት ሊያሳዩ ይገባል። ሁለቱም ያለውን እውነታ በመመልከት አቋማቸውን ለውጠው ገሀዱን እስካልተቀበሉ ድረስ ፣ ትልቅ ተግዳሮት ይጠብቀናል። ከመሪዎቹ ጋር በቅርበት የሚሰሩ እና ገሀዱን ሁኔታ የማገናዘብ ችሎታ ያላቸው ሁሉ መሪዎቹ  «ሀገሪቱ ከናንተ በላይ ናት፣ እርቀ ሰላም እናውርድ፣ ትግሉን ወደ ሌላ ጊዜ እናስተላልፈው።» ብለው እንደሚነግሩዋቸው ተስፋ እናደርጋለን። »  
እንደተንታኞች አስተሳሰብ፣ በኬንያ ውዝግቡ በየአምስት ዓመቱ እንዳይደገም ከተፈለገ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ኢፍትሓዊ አሰራሮችን ከማስወገድ ጎን፣ በምርጫው ስርዓት  ላይ ተሀድሶ ለማድረጉ ጉዳይም ትኩረት ሊሰጡት ይገባል። 

አርያም ተክሌ/ማርቲና ሺቭኮቭስኪ

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic