ኬንያ፤ ለምዕራብ አፍሪቃ ተጓዦች ድንበርዋን ዘጋች | አፍሪቃ | DW | 17.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ኬንያ፤ ለምዕራብ አፍሪቃ ተጓዦች ድንበርዋን ዘጋች

የኤቦላ ወረርሽኝ የአፍሪቃ መንግሥታትን ክፉኛ አሳስቧል። «የህዝቡ ጤንነት ስጋት ላይ በመዉደቁ» ስትል ኬንያ ቆራጥ ርምጃን ስትወስድ፤ የናይጄሪያ የህክምና ባለሙያዎች ደግሞ ከሙያዊ ግዴታቸው በመሸሽ ላይ ይገኛሉ።

ኬንያ ለላይቤሪያ፤ ለጊኒ እና ለሴራልዩን ተጓዦች ድንበርዋን እንደምትዘጋ አስታወቀች። ከነዚህ ሶስት የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የሚመጡ ተጓዦች ከፊታችን ማክስኞ እኩለ ለሊት ጀምሮ ወደ ሃገሪቱ እንዳይገቡ መከልከሉን የኬንያ መንግሥት አስታወቀ። ይህ የሆነዉ «የህዝቡ ጤንነት ስጋት ላይ በመዉደቁ» እንደሆነም ተያይዞ ተመልክቶአል። እንዲያም ሆኖ ኬንያ ዉስጥ እስካሁን በኤቦላ በሽታ የሞተ ሰዉ አለመኖሩ ነዉ የተዘገበዉ። በኬንያ እስካሁን በኤቦላ ተዋህሲ ተይዘዋል ተብለዉ የተጠረጠሩ አራት ህመምተኞች፤ ከበሽታዉ ነፃ መሆናቸዉን የሃገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጾአል። የኬንያ መንግስት የጉዞ እገዳዉን ይፋ ያደረገዉ የዓለም የጤና ድርጅት የ«WHO»ን ማስጠንቀቅያ ተከትሎ መሆኑም ተያይዞ ተጠቅሷል። በቅርቡ የዓለም የጤና ድርጅት፤ በኬንያ የኤቦላ ተዋህሲ መዛመት ሊጠነክር ይችላል ሲል መግለጫ ማዉጣቱ ይታወቃል። ኬንያ መዲና የሚገኘዉ ዓለማቀፍ የአዉሮፕላን ጣብያ፤ የአካባቢዉ ሃገራት መንገደኞች የሚዘዋወሩበት ማዕከላዊ ቦታ መሆኑ ይታወቃል። በኤቦላ ተዋህሲ እስካሁን ከ1100 በላይ ሰዉ መሞቱ ተረጋግጧል።

የናይጄሪያ የህክምና ባለሙያዎች ሽሽት

እስካሁን ናይጄርያ ውስጥ 11 ሰዎች በኤቦላ ተህዋሲ መያዛቸው ተረጋግጧል። በየጊዜው ሰዎች በበሽታው የተነሳ ህይወታቸውን እያጡ ይገኛሉ። ከነዚህም ውስጥ ከህሙማኑ ጋር በቅርበት የሚሰሩት የህክምና ባለሙያዎች ናቸው። ታድያ ሁኔታው ያሳሰባቸው የናይጄሪያ ሀኪሞች እና ነርሶች ህክምና ማዕከሎችን እየሸሹ እና ከስራቸው እየቀሩ ይገኛሉ። « ቻንች» የተሰኘው ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ በርካታ ባለሙያዎቹ እየከዱት ያሉት ሌጎስ የሚገኘው የ «ያባ ሙንላንድ ሆስፒታል» ነው። በርካታ የህክምና ባለሙያዎቹ ከስራቸው የቀሩት ለቤተሰቦቻቸው ሲሉ እንደሆነ አስታውቀዋል።

በሌላ ዜና፤ በላይቤርያ ታጣቂዎች የኤቦላ ታካሚዎች ማዕከልን በማጥቃት ህመምኞቹ እንዲያመልጡ ማድረጋቸዉ ተዘገበ፡፡ ታጣቂዎቹ የህክምና ባለሞያዎቹ ይጠቀሙበት የነበረን አንሶላ ፍራሽ ሁሉ መዉሰዳቸዉ ተገልፆአል። የኤቦላ ምልክት የታየበቸው ዜጎች፤ ከህክምና ቦታዉ ማምለጣቸው በሽታው በከፍተኛ ሁኔታ እንዳይስፋፋ ስጋት አሳድሯል።

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ

ተዛማጅ ዘገባዎች