ኬንያና የዌስትጌት ጥቃት አንደኛ ዓመት መታሰቢያ | አፍሪቃ | DW | 20.09.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ኬንያና የዌስትጌት ጥቃት አንደኛ ዓመት መታሰቢያ

በኬንያ መዲና ናይሮቢ የሚገኘው ዌስትጌት የተባለው ትልቅ የገበያ ማዕከል በአሸባሪዎች ጥቃት ከተሰነዘረበት በነገው ዕለት ልክ አንድ ዓመት ይሞላል። ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደው የሶማልያ አክራሪ ታጣቂ ኃይል ታጣቂዎቹ እአአ መስከረም 21፣ 2013 ዓም ማዕከሉን በማጥቃት ለቀጠሉት አራት ቀናት በመያዝ ሕዝቡን ማሸበራቸው የሚታወስ ነው።

ዩኒስ ኽቫትሳ ጥቃቱ ሲጣል እቤቷ ነበረች። የገበያውን ማዕከል በደንብ ታውቀዋለች፣ ምክንያቱም የፀጥታ ኃይል አባል ባለቤትዋ የሚሰራው በዚያ ነበር ። የዩኒስ ኽቫትሳ ባለቤት በጥቃቱ ከተገደሉት ሰዎች መካከል አንዱ ነበር። ስምንት ጥይት ተተኩሶበት ሕይወቱን አጥቶዋል፣ ዩኒስ ባሏን ከማጣቷ ጎን የሰባት እና የዘጠኝ ዓመት ሁለት ልጆችዋን ብቻዋን የማሳደግ ከባድ ዕጣ ገጥሟታል።

« ልጆቼን መመገብ፣ ማስተማር፣ ቤት ክራይ መክፈል አለብኝ። አማቾቼ ግንኙነት ማድረግ አልፈለጉም፣ ወላጆቼ ደግሞ እንዳይረዱኝ ገንዘብ የላቸውም። የተደቀነብኝን ከባድ ፈተና ብቻዬን መወጣት አለብኝ። »

የኬንያ መንግሥት ባወጣው ይፋ ዘገባ መሠረት፣ የአሸባብ ሚሊሺያዎች በናይሮቢው የዌስትጌት በጣሉት ጥቃት 67 ሰዎች ሲገደሉ፣ በርካቶች ቆስለዋል፣ በጥቃቱ የተነሳ ትልቅ ችግር የደረሰባቸው ዩኒስ እና ልጆችዋን የመሳሰሉ ሰዎችም ቁጥር ብዙ ነው። ይሁንና፣ ዛሬ ከአንድ ዓመትም በኋላ ጥቃቱን በሚመለከት ብዙ ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮች አሉ። አንዳንድ ለምሳሌ፣ የአጥቂዎቹ ቁጥር 12 ነው በሚል ሲሰሙ የነበሩ ጭምጭምታዎች መሠረተ ቢስ እንደሆኑ እና አራት ብቻ እንደሆኑ ነው የተነገረው፣ አራቱም የኬንያ ፀጥታ ኃይላት ማዕከሉን ለማስለቀቅ ባካሄዱት የተኩስ ልውውጥ መገደላቸው ተገልጾዋል። በዌስትጌቱ ጥቃት የአንድ ሶማልያዊ አጥፍቶ ጠፊ ባልተቤት የሆነች እንግሊዛዊት ተሳትፋለች መባሉም እስካሁን ሊረጋገጥ አልቻለም። ይህ በዚህ እንዳለ፣ አጥቂዎቹን ረድተዋል ተብለው በተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሥርቶ ችሎት በመካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ቀጣዩ ቀጠሮ የፊታችን ማክሰኞ፣ እአአ መስከረም 23፣ 2014 መሆኑ ተገልጾዋል።

ከዌስትጌቱ የአሸባሪዎች ጥቃት ወዲህ፣ ጥቃቱ በሕዝቡ ዘንድ በፈጠረው የፍርሃት ስሜት የተነሳ ብዙዎቹ የናይሮቢ ነዋሪዎች ትላልቅ የገበያ ማዕከላት ከመሄድ ተቆጥበዋል። ሰዎች ወደ ትላልቅ የገበያ አዳራሾች እና ሕዝብ ወደሚገለገልባቸው ቦታዎች እንደ በፊቱ መሄድ እስኪጀምር ድረስ ብዙ ወራት ማለፉን በናይሮቢ የሚገኘው የናክመት የገበያ ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጅ አቱል ሻህ ገልጸዋል። በዌስትጌቱ ጥቃት ሶስት ሰራተኞቻቸው እንደተገደሉ እና መደብሩ አሁንም ገና አለመከፈቱን ያስታወቁት ሻህ፣ ተቋማቸው በጥቃቱ የደረሰበት ኤኮኖሚያዊ ጉዳት 500 ሚልዮን የኬንያ ሺሊንግ ወይም ከአራት ሚልዮን ዩሮ በላይ መሆኑን ገልጸዋል።

« ዌስትጌት ትልቁ እና ዋነኛው ቅርንጫፋችን ነበር። ጥሩ የንግድ እንቅስቃሴ የታየበት፣ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች የሆኑ ደንበኞች ያዘወትሩት የነበረ ቅርንጫፋችን ነው። ጥቃቱ ከሶስት ቀናት በኋላ ባበቃበት ጊዜ በዚያ የነበረንን ሁሉ አጣን፣ ናክመትን እንደገና መክፈት አልቻልንም። »

አሸባብ ይህንኑ በብዛት ሀብታሞች በሚኖሩበት በምዕራባዊው የናይሮቢ አካባቢ የሚገኘውን እና ከውጭ ዜጎችም ጎን ብዙ ኬንያውያን ደንበኞችም ያሉትን የዌስትጌት የገበያ ማዕከል ያጠቃው ከፍተኛ የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት እንደሚያገኝ በመገንዘብም ነበር።

በሶማልያ መንግሥት አንፃር የሚዋጋው አሸባብ ወደ ሶማልያ ጦር የላኩ ጎረቤት ሀገራትን ፣ እአአ ጥቅምት 2011 ዓም የላከችዋን ኬንያን ጭምር፣ የጥቃቱ ዒላማ በማድረግ በተደጋጋሚ ጥቃት መሰንዘሩን ቀጥሎዋል። ለምሳሌ በባህሩ ጠረፍ የሚገኘውን የላሙ ግዛት አጥቅቶዋል። ይህን በመሰለው ርምጃው ኬንያ ጦሯን ከሀገሩ እንድታስወጣ ለማስገደድ ነው ያሰበው። ባለፈው ሳምንትም በዩጋንዳ መዲና ካምፓላ ሊጥለው ነበር የተባለውን ጥቃት የዩጋንዳ ፖሊስ እንዳከሸፈው እና 19 ተጠርጣሪ አክራሪ ሙሥሊሞችን እንዳሰረ ተሰምቶዋል።

ኬንያ ሕዝቧን እና ቱሪስቶችን ከአሸባሪዎች ጥቃት ለመከላከል አስፈላጊውን ርምጃ መውሰዷን ብታስታውቅም እና የኬንያ ፖሊስ የአሸባሪዎችን ጥቃት ለማስወገድ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የፖሊስ ቃል አቀባይ ቢገልጽም፣ የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚሉት፣ አሸባሪዎች የደቀኑት ስጋት እንደበፊቱ ከፍ ያለ ነው። በአፍሪቃ ሽብርተኝነት የደቀነው ስጋት ከፍ እያለ መሄዱን የኬንያ የስለላ ድርጅት የሽብርተኝነት ጉዳይ ተመልካች ክፍል ኃላፊ ክሪስ ምቡሩ የአፍሪቃ ሀገራት የስለላ ድርጅቶች መሪዎች በሽብርተኝነት አንፃር በሚያደርጉት ትግል ላይ ትብብራቸውን ለማሳደግ ስለሚቻልበት ጉዳይ ባለፈው ነሀሴ በናይሮቢ በመከሩበት ጊዜ አስታውቀዋል።

የኬንያ መንግሥት በነገው ዕለት በሚውለው የዌስትጌት ጥቃት የመጀመሪያው ዓመት ላይ በጥቃቱ የሞቱትን ሰለባዎች በተለያዩ ዝግጅቶች ያስባቸዋል።

ኤቦላ እና ዓለም አቀፉ ርዳታ

የኤቦላ ወረርሽኝ ባለፈው መጋቢት ወር ጊኒ ውስጥ ከተከሰተ ወዲህ በምዕራብ አፍሪቃ ተስፋፍቶዋል። ላይቤርያ፣ ሲየራ ልዮን፣ ናይጀሪያ እና ሴኔጋል በወረርሽኙ ተጎድተዋል። በዓለም ጤና ድርጅት ዘገባ መሠረት፣ ከ2,500 ሲሞቱ፣ ከ5,00 የሚበልጡ በተኃዋሲው ተይዘዋል። የኤቦላ ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ ርዳታ ወደተጎዱት አካባቢዎች እየደረሰ ነው። ግን ርዳታው አቅርቦት እጅግ አዝጋሚ ነው። የላይቤርያ ፕሬዚደንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ወረርሽኙ ጊዜ እንደማይሰጥ በማስታወቅ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተጨማሪ ርዳታ እንዲያቀርብ ተማፀነዋል። ሰርሊፍ ካለ ተጨማሪ ርዳታ በኤቦላ አንፃር የተጀመረው ትግል እንደማይሳካ በማስጠንቀቅ፣ይህንኑ ተማፅኖአቸውን በቀጥታ ለጀርመን መራሒት መንግሥት አንጌላ ሜርክል አቅርበዋል።

ሰርሊፍ የኤቦላ ታማሚዎች ሞንሮቪያ ውስጥ የሚታከሙበት ቢያንስ አንድ ማዕከል በመገንባት ፣ እንዲሁም፣ ከመዲናይቱ ውጭ ያሉት ስራቸውን መቀጠል ያልቻሉ በሌላ በሽታ የታመሙን ህክምና የሚያገኙባቸውን አስር ሀኪም ቤቶችን እንደገና በማንቀሳቀሱ እና መድሀኒት እና የጤና ባለሙያዎችን በአይሮፕላን በማመላለሱ ረገድ ላይ እንድትረዳ ከጀርመን በተጨባጭ ጠይቀዋል። የጀርመን መንግሥት በምዕራብ አፍሪቃ ታማሚዎችን በመርዳት ላይ ላሉት ድርጅቶች ድጋፍ እንደሚያደርግ፣ በተለይም፣ መድሀኒት እና የጤና ባለሙያዎችን በአይሮፕላን በማመላለሱ ረገድ ላይ ድጋፉን እንደሚያጠናክር አስታውቋል። የማጓጓዙ ወጪ ውድ ሆኖዋል።

ጥሪውን ተከትሎ «አክስዮን ሜዴኦር» በመባል የሚታወቀው የህክምና መድሀኒት እና ቁሳቁስ ርዳታ አቅራቢ የሆነው የጀርመናውያኑ ግብረ ሠናይ ድርጅት አስፈላጊውን ርዳታ ለማቅረብ እየተንቀሳቀሰ ነው። በቶኒስፎርስት ከተማ በሚገኘው 3,000 ካሬ ሜትር መጋዘን ውስጥ የአክስዮን ሜዴኦር ሰራተኞች ወደ ምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት የሚላከውን ፣ ማለትትም፣ ለታማሚዎቹ መድሀኒት፣ ታማሚዎቹን ለሚያክሙት እና ለሚያስታምሙት ደግሞ ከራስ ፀጉራቸው እስከ እግር ጥፍራቸው የሚሽፍን ልዩ ልብስ፣ ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገልለግል የእጅ ጓንቲ፣ የአፍ መሸፈኛ የመሳሰሉትን ቁሳቁስ አዘጋጅተዋል። አክስዮን ሜዴኦር በሞንሮቪያ አቅራቢያ ክሊኒክ አቋቁሞ ከሚሰራው የጀርመናውያኑ ማርግሬት ጊራትስ ንሜኔ ጋ አብሮ ይሰራል። የአክስዮን ሜዴኦር ዋና ስራ አስኪያጅ ክርስቶፍ ቦንስማና ጓንቲን የመሳሰለ አስፈላጊ ቁሳቁስ መጓደሉን ነው የገለጹት።

« ወዳካባቢው ሀገራት፣ ላይቤርያ፣ ጊኒ እና ሲየራ ልዮን ለጤና ባለሙያዎችና እና ሀኪሞች አስፈላጊ የሆነውን ቁሳቁስ በብዛት መላክ ነበረብን። ይህ ተጓድሎ በመገኘቱ አስታማሚዎች እንደሚገባው ራሳቸውን መከላከል ባለመቻላቸው በተኃዋሲው ተይዘዋል። ይህን አድርገን ቢሆን ኖሮ የሀኪሞችንና ጤና ባለሙያዎችን ሕይወት ማትረፍ በቻልን ነበር። »

ከሁሉም በላይ በአሁኑ ጊዜ በተኃዋሲው ተይዘዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎችን ማቆየት የሚቻልበት ቦት ተጓድሎ እንደሚገኝ ነው ቦዝማን ያስታወቁት።

« ትልቁ እንቅፋት ታማሚዎችን ማከም የሚቻልበት አቅምም ሆነ ቦታ አለመኖሩ ነው። በዚህም የተነሳ የኤቦላ ታማሚዎችን እና የተጠረጠሩትን ከሕዝቡ ለያይተን የምናቆይባቸው ድንኳኖችን መትከል አለብን። »

ቦዝማን እና ቡድናቸው ታማሚዎች ከጤናኛው ሕዝብ ተለይተው የሚታከሙባቸው 44 አልጋዎች የሚኖሩዋቸው ሁለት ክሊኒኮችን መገንባት የሚያስችላቸውን ገንዘብ ያሰባሰቡ ሲሆን፣ ክሊኒኮቹን እስከያዝነው መስከረም ወር ሞንሮቪያ ውስጥ እንደሚገነቡ እና ስራቸውን እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።

በወረርሽኙ ያልተጎዱትም ያካባቢው ሀገራት አስፈላጊውን ዝግጅት ብሎም ከራስ ፀጉራቸው እስከ እግር ጥፍራቸው የሚሽፍን ልዩ ልብስ፣ ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገልለግል የእጅ ጓንቲ፣ የአፍ መሸፈኛ የመሳሰሉትን ቁሳቁስ አዘጋጅተው መጠበቅ እንደሚገባቸው አስረድተዋል።

ሮይብን ቻባ/አርያም ተክሌ

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic