ኬርኤፕሊፕሲ፤ ግንዛቤ ለማፍጠር እየጣረ ነው | ጤና እና አካባቢ | DW | 05.11.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ኬርኤፕሊፕሲ፤ ግንዛቤ ለማፍጠር እየጣረ ነው

ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች በተለምዶ የሚጥል በሽታ ተብሎ ስለሚታወቀው ኤፕሊፕሲ ያላቸው ግንዛቤ አሁንም መለወጥ እንደሚኖርበት እየተነገረ ነው። በቅርቡ አንድ ግብረሰናይ ድርጅት ተቋቁሞም ሰዎች የግንዛቤ ለውጥ እንዲያመጡ የበኩሉን ጥረት ጀምሯል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:48

«በየወሩ የአቻ ለአቻ የመረዳጃ መድረክ ያዘጋጃል»

ከወራት በፊት በተለምዶ የሚጥል በሽታ በመባል ስለሚታወቀው ኤፕሊፕሲ ምንነት ላይ ያተኮረ ለሁለት ሳምንት ተከታታይ መሰናዶ ማቅረባችን ይታወሳል። ይህን የተከታተሉ አበበ አያና የተባሉ አድማጭ ከኢትዮጵያ የላኩልን ስለጉዳዩ ተጨማሪ መረጃዎችን ያካተተ ደብዳቤ ከሰሞኑ ደርሶናል። የተከበሩ አድማጫችን በቅድሚያ ዝግጅቶቻችንን ስለሚከታተሉ ምስጋናችን ይድረስዎ! ስለኢፕሊፕሲ  ተጨማሪ መረጃዎችን ከእኛ ለመስማት በጉጉት እንደሚጠብቁም ገልፀውልናል።  የዝግጅታችን አድማጭ የሆኑት አበበ አያና የላኩልን  ስለጤና ችግሩ ታማሚዎችም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው ቢያውቁት ለመፍትሄ የሚረዱ ጠቃሚ መረጃዎች በመሆናቸው በአድማጮች ስም ልናመሰግናቸው እንወዳለን። ከመረጃዎቹ እንደተረዳነውም ትኩረቱን በዚህ የጤና ችግር ላይ ያደረገ ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛል። ኬርኤፕሊፕሲ ኢትዮጵያ ይባላል።  
ኬርኤፕሊፕሲ ኢትዮጵያ በሚያሰራጫቸው በራሪ ጽሑፎች አማካኝነት ሰዎች ስለበሽታው ምንነት እንዲረዱ፤ ለኤፕሊፕሲ መንስኤ ሊሆኑ ስለሚችሉ ምክንያቶች፤ ድንገት በሽታው ለጣለው ሰው ሊደረግ ስለሚገባው የመጀመሪያ ርዳታ እና ጥንቃቄ፤ በዝርዝር ይመክራል። ይህ የጤና ችግር ርግማንም ሆነ ከርኩስ መንፈስ ቁርኝት ጋር ምንም እንደማያገናኘው የሚያስረዳው ኬርኤፕሊፕሲ በወር አንድ ቀን የሚካሄድ የአቻ ለአቻ የመደጋገፍ መድረክ እያካሄደ ይገኛል። አጋጣሚው ደግሞ ታማሚዎች የመረጃ እና ተሞክሮ ልውውጥ እንዲያደርጉ ያመቻቻል።  
ኬርኤፕሊፕሲ በዚህ የጤና ችግር የሚሰቃዩ ወገኖች ትኩረት እና ህክምና እንዲያገኙ ፤ የበሽታው ምንነት ታውቆም ታማሚዎቹ በማኅበረሰቡ ውስጥ መገለል እንዳይደርስባቸው የማድረግ ራዕይ ሰንቆ በኢትዮጵያ ሥራ የጀመረ ቀዳሚ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው።

ከተቋቋመም አራት ዓመት ከመንፈቅ እንደሆነው ከመሥራች እና ሥራ አስኪያጇ ከወ/ሮ እናት የእውነቱ ለመረዳት ችለናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ግማሽ ሚለየን የሚሆኑ የኤፕሊፕሲ ታማሚዎች በቂ ህክምና ሳያገኙ ከችግሩ ጋር እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚህ ላይ ኅብረተሰቡ ይህን የጤና ችግር የሚረዳበት መንገድ ለታማሚዎቹ ተጨማሪ መገለልን እንዳስከተለም ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት ይናገራሉ። የኬርኤፕሊፕሲ መሥራች ወደዚህ ሥራ የገቡት ኅብረተሰቤ ስለዚህ ህመም ምንነት ይበልጥ እንዲረዳ በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል። 
ምንም እንኳን ግብረሰናዩ ድርጅት ከተቋቋመ  አጭር ጊዜ ቢሆንም ጥቂት የማይባሉ ወገኖች ግንዛቤ እንዳገኙ ወ/ሮ እናት ያስረዳሉ። ጉዳዩ ከእምነት እየተያያዘ ስለሚታይ ግን የሰውን አስተሳሰብ በቀላሉ ለመለወጥ አዳጋችነቱን ተገንዝበዋል። በዚህም ምክንያትም ታማሚዎቹ ካለባቸው የጤና ችግር በተጨማሪ ለስነልቡና ጉዳት እንደሚዳርግም ያስገነዝባሉ። 
በዚህ አጋጣሚም አዲስ አበባ በየካቲት 12፤ በዘውዲቱ፤ በጳውሎስ እንዲሁም በጦር ኃይሎች ሀኪም ቤቶች እንዲሁም በተለያዩ የግል ክሊኒኮች ለዚህ የጤና ችግር ህክምና እንደሚሰጥ ኬርኤፕሊፕሲ የሚያሰራጨው በራሪ ወረቀት ያመለክታል። ዝርዝር መረጃዎችን ወ/ሮ እናት በሰጡት አድራሻ በመደወልም ማግኘት እንደምትችሉ ልንገልጽ እንወዳለን። ለቃለ መልልሱ የተባበሩንን የኬርኤፕሊፕሲ መሥራች እና ሥራ አስኪያጅን እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች