ካይሮ፥ 224 ሰዎች የጫነ የሩሲያ አዉሮፕላን ተከሰከሰ | ዓለም | DW | 31.10.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ካይሮ፥ 224 ሰዎች የጫነ የሩሲያ አዉሮፕላን ተከሰከሰ

የሩሲያ A-321 የመንደኞች አዉሮፕላን ሲና በረሃ ግብፅ ዉስጥ ዛሬ ተከሰከሰ። 217 መንገደኞች እና 7 ሠራተኞችን የጫነዉ አዉሮፕላን በደረሰበት አደጋ ተሳፋሪዎቹ እንዳልተረፉ በግብፅ የሩሲያ ኤምባሲ በፌስቡክ ገጹ ላይ መግለፁን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።

ግብፅ ሲና ዉስጥ ከሚገኘዉ የሻርም ኤል ሼህ የመዝናኛ ስፍራ ወደ ሴንት ፔተርስበርግ ሩሲያ ሊያመራ የተነሳዉ አዉሮፕላን ከ23 ደቂቃ በኋላ ከቁጥጥር ዉጭ ሆኖ እንደተከሰከሰ ዘገባዉ አመልክቷል። ከመንገደኞቹ 214ቱ የሩሲያ ሦስቱ ደግሞ የዩክሬን ዜጎች መሆናቸዉም ተገልጿል። ሩሲያ የተሳፋሪዎቹን ስም እና እድሜያቸዉን ከ10 ወር አንስቶ እስከ 77 ዓመት መሆኑን የሚያሳይ ዝርዝር አዉጥታለች።

17ቱ ሕፃናት ናቸው። አንድ የግብፅ የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሥልጣን አደጋዉ ከመድረሱ አስቀድሞ ለመጨረሻ ጊዜ አብራሪዉ የአዉሮፕላኑ ራዲዮ ስልት ችግር እንደፈጠረበት እንደነገራቸዉ ገልጸዋል። የሩሲያ የመንግሥት የመጓጓዣ ቁጥጥር ዘርፍ፤ አዉሮፕላኑ ከዚህ በፊት የደህንነት ጥራት እክል እንዳገኘበት ጠቁሟል። ግብፅ ዉስጥ እራሱን «እስላማዊ መንግስት» ከሚለዉ ፅንፈኛ ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳለዉ የተገለጸ ቡድን በበኩሉ አዉሮፕላኑን መትቶ እንደጣለ መግለፁን የፈረንሳይ የዜና ወኪል ዘግቧል። መረጃዉ በሦስተኛ ወገን አልተረጋገጠም።

የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የአውሮፕላኑን መከስከስ በተመለከተ ከግብፁ አቻቸው አብደል ፋታህ አል ሲሲ ጋር በስልክ ተነጋግረዋል። አልሲሲ ለተጎጂ ቤተሰቦች መፅናናትን በመመኘት፤ የሩስያ ባለሙያዎች የአደጋውን መንስዔ በማጣራቱ ሒደት እንዲሳተፉ ሀገራቸው ሁኔታዎችን እንደምታመቻችም ገልጠዋል። የአውሮፕላኑን መረጃ የሚሰበስበው ጥቁር ሣጥን መገኘቱን የግብፅ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። ከዚህ ሣጥን አውሮፕላኑ በምን ምክንያት እንደተከሰከሰ መረጃ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ