ካርዛይ እና የምዕራቡ ግፊት | ዓለም | DW | 19.11.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ካርዛይ እና የምዕራቡ ግፊት

የአፍጋኒስታን ፕሬዚደንት ሀሚድ ካርዛይ ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን ዛሬ ቃለ መሀላ ፈጸሙ።

default

ስምንት መቶ እንግዶች፡ ከነዚህም የዩኤስ አሜሪካ እና የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች፡ እንዲሁም፡ የፓኪስታን ፕሬዚደንት ጭምር በተገኙበት እና ጠንካራ ጥበቃ በተደረገበት ስነ ስርዓት ላይ ካርዛይ ባሰሙት ንግግር በሙስና እና በሀገራቸው በተስፋፋው የዕጸ ሱስ ንግድ አንጻር እንዲሚሰሩ አስታውቀዋል። ከሁለተኛው ዙር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ራሳቸውን ያገለሉት ዋነኛ ተፎካካሪያቸው ዶክተር አብዱላ አብዱላ አዲሱን የብሄራዊ አንድነት መንግስት እንዲቀላቀሉ ካርዛይ ጥሪ አቅርበውላቸዋል። የውጭው ዓለም ካርዛይ የገቡትን ቃል ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ግልጽ አድርጎዋል።

የአስመራጩ ኮሚሽን ከአስራ ሰባት ቀናት በፊትሀሚድ ካርዛይ የፕሬዚደንታዊው ምርጫ አሸናፊ መሆናቸውን ያረጋገጠበት መግለጫ ነበር ያዳመጣችሁት። እርግጥ ምዕራቡ ዓለም፡ የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ፡ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ጎርደን ብራውን፡ የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ጭምር ወዲያውኑ አጠር ያለውን የደስታ መግለጫ አስተላልፈዋል።

Afghanistan ISAF Soldaten aus Kanada im Provinz Kandahar mit Armee Afghanistans

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግን በዚሁ ጊዜ በሰፊው ያገነዘበው አፍጋኒስታን አሁን የተሳካ ውጤት የሚያስገኝ የመንግስት አመራር ማቋቋም እንደሚጠበቅባት ነበር በግልጽ ከማስታወቅ አልቦዘኑም። ይህንን በተመለከተ የአፍጋኒስታን ፕሬዚደንት ሀሚድ ካርዛይ ለአሜሪካውያኑ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ ሲመልሱ እንዲህ ነበር ያሉት።
« ምዕራቡ ዓለም ለአፍጋኒስታን ጥቅም ብሎ አይደለም ወደዚህ የመጣው። ወደዚህ የመጣው ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ነው። ዩኤስ አሜሪካ እና አጋሮችዋ ከመስከረም አንድ በኋላ ነው ወደአፍጋኒስታን የመጡት። አፍጋኒስታን ግን ከዚያን ጊዜ በፊት ጀምሮ ነበር ግዙፍ ችግር የነበረባት። ግን ማንም ደንታ አልሰጠውም ነበር። እነርሱ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ይፈልጋሉ፤ ይህንን ፍላጎታቸውን እኛም የምንጋራው ነው። »
ይህ አባባል በምዕራቡ እና በአፍጋኒስታን መካከል ያለው ግንኙነት አንዱ ከሌላው ምንም የማይጠብቅበት ጉድኝት ነው ማለት ይሆን? ፕሬዚደንት ካርዛይ በሀገራቸው ሙስናን እንዲዋጉ፡ በመንግስታቸውም ውስጥ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች እንዲሾሙ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በግልጽ ጠንካራ ግፊት አሳርፎባቸዋል፤ ከሞላ ጎደልም ዛቻ እስከማሰማትም ርቆ የሄደበት ጊዜም አልጠፋም፤ ልክ የተመድ ልዩ የአፍጋኒስታን ልዑክ ካይ ኤንደ እንዳደረጉት።
« አንዳንዶች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአፍጋኒስታን የጀመረው እንቅስቃሴ፡ ይህችው ሀገር በያዘችው ስልታዊ ትርጓሜ የተነሳ ወደፊትም ይቀጥላል ብለው ያምናሉ። ይህ ትክክል አለመሆኑን ልገልጽ እፈልጋለሁ። ይኸው ታታሪነት መቀጠል አለመቀጠሉ በለጋሽ ሀገሮች እና የጦር ኃይል በሚያዋጡ ሀገሮች ህዝቦች አስተያየት ላይ ጥገኛ ነው። ባለፉት ጊዚያት በነዚሁ ሀገሮች የቀጠለው ክርክርም ወሳኝ ሁኔታ ላይ እንደምንገኝ የሚያሳይ ነው። »
ካርዛይ በምዕራቡ በሚያገኙት ገንዘብ ላይ ጥገኛ ሲሆኑ፡ ካለዚሁ ገንዘብ ፕሬዚደንት ሊሆኑ ባልበቁ ነበር። በአፍጋኒስታን የተሰማራው የውጭ ጦር ኃይል ከወጣም ፕሬዚደንት ሆነው የሚቆዩበት ጊዜ ረጅም አይሆንም። ይህም ሆኖ ግን፡ ካርዛይ ለአሜሪካውያኑ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ካለዓለም አቀፉ ርዳታ ራስዋን ችላ የቆመ ሀገር ርዕሰ ብሄር መሆናቸውን ለማሳየት ነው የሞከሩት። በአፍጋኒስታን በሚገኙት የተመድ ሰራተኞች ላይ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በመዲናይቱ ጥቃት ከተጣለባቸው በኋላ ድርጅቱ ከፊሉን ሰራተኞቹን ያስወጣበት ድርጊት በሀገራቸው ላይ ያሳረፈው ተጽዕኖ ስለመኖሩ ለቀረበላቸው ጥያቄ ፕሬዚደንት ካርዛይ ሲመልሱ፡
« አንድም ተጽዕኖ አላሳረፈም። ባሉበት መልካሙን እንመኝላቸዋልን። »
ነበር ያሉት።
ይህ አነጋገራቸው አፍጋኒስታን ራስዋን ችላ ትቆም ዘንድ ከብዙ ዓመታት ወዲህ በየቀኑ ህይወታቸውን ስጋት ላይ ጥለው ለሚሰሩት ሰዎች የማይ ነው። እንግዲህ ፕሬዚደንቱ በሚቀጥሉት ሳምንታት የሚከተሉትን አሰራር፡ ማለትም፡ ምዕራቡ አስቸኳዩንና ሁነኛውን ተሀድሶ እንዲያደርጉ ያቀረበላቸውን ጥያቄ ተቀብለው ማሟላታቸውን ጠብቆ ማየቱ ግድ ይሆናል። ምክንያቱም፡ ምዕራቡ እንደሚያምነው፡ ካርዛይ ይህን ሲያደርጉ ብቻ ነው ጨቅላውን እና ጉዳት የደረሰበትን የአፍጋኒስታን ስርዓተ ዴሞክራሲን ለማጠናከር የሚቻለው። ለዚህም፡ እንደፖለቲካው ተንታኝ ሀሩን ሚር አስተያየት፡ ካርዛይ ብዙ ጊዜ የላቸውም።
« ታሊባን በሚቀጥሉት ስድስት ወራት መሸነፍ አለበት ወይም የካቡልም መንገዶች አስፋልት ይሁኑ ማለቴ አይደለም። እኔ የምለው አንዳንድ የመሻሻል ሁኔታዎች መታየት አለባቸው ነው። ህዝቡ በአስቸኳይ የሚያስፈልገው ፍትህ፡ ጸጥታ እና መሰረታዊው አገልግሎት ነው። »
ብዙ ታዛቢዎች እንደሚሉት፡ ፕሬዚደንት ካርዛይ በምርጫ ዘመቻውና ከምርጫው በኋላም በምርጫው ወቅት ተካሄደ በተባለው የማጭበርበር ተግባር የተነሳ ተዓማኒነታቸውን በመጎዳቱ ጠንካራ ፕሬዚደንት አይደሉም። ይህንኑ የካርዛይን መዳከም ምዕራቡ ዓለም ምናልባት እንደጥንካሬ ሊመለከተውና በካርዛይም ላይ ተጽዕኖውን ለማሳረፍ ይጠቀምበት ይሆናል ብለው የሚያምኑ ብዙዎች ናቸው።

ካይ ኪውስትነር/አርያም ተክሌ
ሂሩት መለሰ