ካርቦንን ለመቀነስ መሬት ዉስጥ መቅበር | ጤና እና አካባቢ | DW | 02.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ካርቦንን ለመቀነስ መሬት ዉስጥ መቅበር

ከባቢ አየር ለብክለት የዳረገዉን የጋዝ መጠን ለመቀነስ የተለያዩ ስልቶች እየተቀረቡ ነዉ። ለብክለቱ ታሪካዊ ተጠያቂነት ያላቸዉ በኢንዱስትሪ ያደጉ ሃገራት የሚለቁትን መጠን ለመቀነስ ቃል እየገቡ ነዉ። በከባቢዉ አየር ዉስጥ የተከማቸዉን ለማስወገድ መፍትሄ ከሚባሉት የደን መበራከት እንዳለ ሆኖ ካርቦንን ሰብስቦ ለዘመናት የማከማቸት ጥረትም አለ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:42

መሬት ዉስጥ ካርቦን ዳይኦክሳይድን ለዘመናት ማከማቸት፤

ከባቢ አየርን በመበከል ሙቀትንም በማመቅ ግንባር ቀደም ተወቃሽ የሆነዉን የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት ለመቀነስ ሃገራት ቃል ከገቡ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። ተግባራዊዉ ርምጃ ግን ዛሬም ዳተኛ ነዉ። በዚህ ምክንያትም የዓለም የሙቀት መጠን ከዓመት ዓመት ከፍ እያለ መሄዱ እና በወቅቶች መፈራረቅ ወቅትም ያልተለመደ የአየር ጠባይ ማስተናገድ ግድ እየሆነ መምጣቱ ብዙዎችን ያሳስባል። እናም የተለያዩ ስልቶችን ለመጠቀም ጥረቶች እየተደረጉ ነዉ። በመደበኛነት ከሚታወቁት አንዱ ዛፎችን በኢንዱስትሪ ያላደጉ ሃገራት ተክለዉ የደን ሀብታቸዉን እንዲያስፋፉ የሚደረገዉ ማበረታታት ሲሆን በለዉጡ በኢንዱስትሪ ያደጉት ሃገራት ለእነዚህ ሃገራት የሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍ ነዉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ከየኢንዱስትሪዉ የሚወጣዉን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ሰብስቦ ምድር ዉስጥ ማጠራቀም አለ። ሂደቱ እንዲህ ነዉ። ለምሳሌ ከቅሪተ አፅም ኃይል የሚያመነጩ ተቋማት፤ በሂደት የሚለቁትን ካርቦን ዳይኦክሳይድን ሰብስቦ ለዚሁ ተግባር በተዘረጋ ቧምቧ አማካኝነት ለማከማቸት ወደተዘጋጀዉ የመሬት ዉስጥ አካል ይላካል። ዶክተር ኒልስ ፖዉልሰን በአዉሮጳ የካርቦን ማጠራቀምን በሚመለከት ምርምር የሚያደርገዉ ተቋም ወኪል ናቸዉ። እሳቸዉ እንደሚሉት ይህ ተግባር ከተጀመረ ቆየት ብሏል። ኢንዱስትሪዎች እና የኃይል ማመንጫዎች የሚለቁትን ካርቦን ዳይኦክሳይድ አንዳንድ ሃገራት ለረዥም ጊዜያት አጠራቅመዋል።

«ኢንዱስትሪዎቹ ካርቦን ዳይኦክሳይድን ያመርታሉ፤ የኃይል ማመንጫዎች የሚወጣዉን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ለረዥም ጊዜ ሰብስቦ በመያዝ ላይ ይገኛል። በአንዳንድ ሃገራትም ለኃይል ማመንጫዎች የሚወጣዉን CO2 ለረዥም ጊዜ አከማችተዉት ይገኛል። አሁን ምርምሩ ወደ ሲሚንቶ እና የብረት ፋብሪካዎች ገብቷል። እነዚህ ምርቶች ልናስቀራቸዉ የምንችል አይነት አይደሉም። ነገር ግን የኃይል ማመንጫዎች ከቅሪተ አጽም የሚገኙትን መጠቀም በመተዉ በረዥም ጊዜ ሂደት ከዚህ ዉጭ የሆኑትን የኃይል ምንጮች ወደ መጠቀም መሸጋገር ይኖርብናል።»

Deutschland Klima Energie Kohle Kohleverstromung Schwarze Pumpe

ካርቦን ዳይኦክሳይድን በብዛት ወደከባቢ አየር እንዲገባ የሚያደርጉ የኃይል ምንጮችን ሃገራት መጠቀም እንዲያቆሙ በየጊዜዉ ጥሪ ይቀርባል። እንደጀርመን ያሉት 40 በመቶ ገደማ የኃይል አቅርቦታቸዉን ከድንጋይ ከሰል ያደረጉ ሃገራት የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎችን ትኩረት ስበዉ ግፊት እየተደረገባቸዉ ነዉ። ዶክተር ፖዉልሰን ታዳሽ ካርቦን ዳይኦክሳይድን ከሚያስከትሉ የኃይል ምንጮች መላቀቅ እንደሚገባ ተመራማሪዎቹ የሚያቀርቡት ሃሳብ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት እንዲያገኝ የሽግግር ጊዜ መስጠት እንደሚገባ ያመለክታሉ።

«ይህ ነገር ምናልባት እስከ 2050 ድረስ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ላይሆን ይችላል፤ ከቅሪተአጽም ኃይል የማመንጨቱ ተግባር ወደሌላ እስኪሸጋገር ጊዜ ያስፈልጋል። በዚህ ሂደት ግን ካርቦን ዳይኦክሳይንድ ወደከባቢ አየር መልቀቅ ሳይሆን አምቆ መያዝ ያስፈልጋል።»

ከየኢንዱስትሪዉ እና የኃይል ማመንጫ ዘርፉ የሚወጣዉ ካርቦን ዳይኦክሳይድ እንደታሰበዉ ተሰበሰበ እና ታምቆ ተቀመጠ እንበል። ከዚያስ ምን ይፈጠር ይሆን? ዳግም ሥራ ላይ የመዋል ዕድል አለዉ? ዶክተር ፖዉልሰን፤

«አንዴ ታምቆ እንዲከማች ከተደረገ በኋላ ካርቦን ዳይኦክሳይድን መልሶ ሥራ ላይ ማዋል የሚቻል አይመስለኝም። ምክንያቱም እጅግ ጥልቅ በሆነ ማከማቻ ማለትም ከአንድ እስከ ሁለት በሚደርስ ኪሎ ሜትር ርቀት ነዉ የሚቀመጠዉ። ከከርሰ ምድር ዉኃዉ አቅራቢያ። በዚያ ጥልቀት ላይ ለመጠጥ የሚዉል ዉኃ የለም። እዚያ ያለዉ ጨዋማ ዉኃ ነዉ። ካርቦን ዳይኦክሳይዱ ወደ ጨዋማዉ ዉኃ ይገባል፤ ከዉኃዉም ጋር ይቀየጣል። ልክ በቤታችን የቧምቧ ዉኃን ከጋዝ ጋር እንደምንቀላቅለዉ ማለት ነዉ።  ካርቦን ዳይኦክሳይዱን ከማከማቻዉ አዉጥቶ መለየት ቢፈለግ መጀመሪያ ጨዋማዉን ዉኃ ማጣራት ያስፈልጋል። ያ ደግሞ መቼም አይሆን፤ ምክንያቱም ጨዋማ ዉኃ አንፈልግም።»

ካርቦንን የመሰብሰቡ ዋና ዓላማ ከባቢ አየር ዉስጥ የተከማቸዉን እና ወደፊትም የሚገባዉን የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን ለመቀነስ እንደመሆኑ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች፤ የብረት ፋብሪካዎች፣ የወረቀት ፋብሪካዎች እና መሰል ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ከየጭስ ማዉጫቸዉ ላይ ካርቦን ዳይኦክሳይድን መሰብሰብ ይችላሉ ነዉ ተመራማሪዉ የሚሉት። ሃሳቡን ብዙዎች ሊስማሙበት ይችሉ ይሆናል። ግን ቴክኒዎሎጂዉ በቀላል ገንዘብ ተግባራዊ የሚሆን አይመስልም።

Norwegische Gasbohrinsel Sleipner

«እዉነት ነዉ በጣም ዉድ ቴክኒዎሎጂ ነዉ። በዝቅተኛ ደረጃ ሥራ ላይ የሚዉል ቴክኒዎሎጂም አይደለም። እሱን ለማድረግ ትልቅ የኃይል ማመንጫ፣ ግዙፍ የብረት ፋብሪካ የመሳሰሉት ሊኖሩ ይገባል። ምክንያቱም ሰፊ መዋዕለ ንዋይ ያስፈልገዋል።»

እንዲያም ሆኖ በከባቢ አየር መበከል የሚቸገሩ በማደግ ላይ የሚገኙ ሃገራት ይህን ቴክኒዉሎጂ ለመጠቀም ከተመራማሪዎቹ ጋር በቅርበት እየሰሩ እንደሆነም ዶክተር ኒልስ ፖዉልሰን ሳይገልጹ አላለፉም። በአንድ በኩል ከባቢ አየርን በክሏል እየተባለ የሚወቀሰዉ ካርቦን ዳይኦክሳይድ ተሰብስቦ መሬት ዉስጥ እንዲከማች ይፈለጋል። ይህ አየሩን ከብክለት ያድነዉ ይሆናል፤ መሬት ዉስጥ መከማቸቱ ለአፈሩ ችግር አይኖረዉ ይሆን?

«ካርቦን ዳይኦክሳይድን ስናከማች ከአንድ እስከ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ወደ ዉስጥ ገብተን ነዉ። በዚህ ርቀት የሚከማቸዉ ካርቦን ዳይኦክሳይድ ፈሳሽ ባለመሆኑ ለመዉጣት አስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ ይገባል። ወደላይ ወጥቶ ቦታ የሚይዝበት አጋጣሚም አይኖረዉም።በዚያዉ በማከማቻዉ ዉስጥ በዚያ ጥልቀት ለማቆየት ይቻላል። እናም በማከማቻዉ ዉስጥ ብቻ እንዲቀመጥ ማድረጉ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ነገር ነዉ። በዚያም ላይ ጥልቅ መሆኑ ጥሩ ነዉ ምክንያቱም ማከማቻዉን ለማዘጋጀት ጥናቱ በአግባቡ ሳይሰራ ቀርቶ ከሆነም የከርሰ ምድር ዉኃዉን ከብክለት ለመከላከል በተጨማሪ ሁለተኛ ደረጃ እና ሦስተኛ ደረጃ ካርቦን ዳይኦክሳይድን ሁሉ አምቆ የማከማቸት ዋስትና አለዉ። ምክንያቱም እንዲህ ያለ አጋጣሚ ሲኖር የነዳጅም ሆነ ጋር ልቀት ሊኖር ይችላል። »

ከማከማቻዉ የካርቦን ዳይኦክሳይድ ፍሰት ከሆነም ሊሄድ የሚችለዉ ወደላይ መሆኑን አክለዉ የገለጹት ተመራማሪዉ ፍንዳታ የማስከተል አቅም የለዉምም ይላሉ።  በዚያም ላይ በድንጋዮች መካከል ስለሚጓዝም ጉዞዉ እጅግ አዝጋሚ እንደሚሆንም ያመለክታሉ። በዚህ ሂደት ለመጠጥ ከሚዉለዉ የዉኃ ክምችት ጋር ሊቀላለቅ ይችላል። ግን ችግር የለዉም፤

«የሚጠጣዉ ዉኃ ከካርቦን ዳይኦክሳይድ ጋር ሊደባለቅ ይችላል። ይህም ያን ያህል ትልቅ የሚባል ችግር አይደለም። ይህ ደግሞ ከሶዳ ኢንዱስትሪዉ የሚታይ ነዉ። ማለትም ኮካም ሆነ ጋዝ ያለዉ ዉኃ ቢጠጣ መርዛማነት የለዉም። እናም ከዚህ አኳያ ችግር አይፈጥርም። ችግር የሚሆነዉ ካርቦን ዳይኦክሳይድ የአሲድነት  ባህሪ ስላለዉ የተገጣጠሙትን ነገሮች ሊያዝጋቸዉ ይችላል።»

Deutschland Klima Umwelt Speicherung von CO2

ይህም ቢሆን ይላሉ ተመራማሪዉ የካርቦን ዳይኦክሳይድ ሰብስቦ ማከማቻዉን ሥልት የሚከታተለዉ ዘርፍ ችግሩን ሊደርስበት ይችላል። ፍሰቱም እንዲቆም ይደረጋል። ዋናዉ ነገር ግን ለዚህ አገልግሎት የተመረጠዉ ቴክኒዎሎጂ አይነት ነዉ።

በነገራችን ላይ ካርቦን ዳይኦክሳይድን በመሬት ዉስጥ ማከማቸት የሚሰጠዉ ጥቅም ከባቢ አየርን ከካርቦን ማጽዳት ብቻ አይደለም። ይህን ስልት በተዘዋዋሪ ለሌላ ጥቅም ያዋሉት አሉ። ዩናይትድ ስቴትስ አንዷ ናት። ዶክተር ፖዉልሰን፤

«ካርቦን ዳይኦክሳይድን በመሬት ዉስጥ የማከማቸቱ ስልት ያለዉ ጠቀሜታ የታየዉ ከዩናይትድ ስቴትስ ነዉ። እዚያ ብዙ ነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ለማምረት ይጠቀሙበታል። ለዚህ ሲሉም በተፈጥሮ የነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ክምችት ባለበት አካባቢ ካርቦን ዳይኦክሳይድ እንዲገባ ያደርጋሉ። ካርቦን ዳይኦክሳይዱ በማከማቻዉ ዉስጥ ይዘቅጥና ዘይት እና ጋዙን ገፍቶ ያወጣዋል። ይህ ካርቦን ዳይኦክሳይድን ወደመሬት ዉስጥ የማስገባዉ እዉቀት ደግሞ በ1970ዎቹ የተጀመረ ነዉ። ከዚያም በ1990ዎቹ መጀመሪያ ገደማ ኖርዌይ የካርቦን ቀረጥን ስትቀንስ የኖርዌይ ነዳጅ ዘይት ኩባንያ ግብር መቀነስ ከተቻለ እንደዩናይትድ ስቴትስ ካርቦን ዳይኦክሳይድን ለማከማቸት ወሰነ። እናም ወደከባቢ አየር በመልቀቅ ፋንታ በሰሜን ባህር አካባቢ ካርቦን ዳይኦክሳይድን ማከማቸት ጀመረ። በዚህ ምክንያትም ቀረጥ ማስቀነስ ቻለ።»

አሁን ላለፉት 21 ዓመታት የኖርዌይ የነዳጅ ማጣሪያ ኩባንያ በየዓመቱ ወደከባቢ አየር ሊገባ የሚችል አንድ ሜጋ ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ እያከማቸ ይገኛል። የዘርፉ ተመራማሪ ዶክተር ኒልስ ፖዉልሰን ይህ እጅግም ብዙ የሚባል አይደለም ባይ ናቸዉ። በዚህ መንገድ ካርቦን ዳይኦክሳይድን እየሰበሰቡ ከሚያከማቹ ሃገራት ካናዳ እና ዩናይትድ ስቴትስ ንቁ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ነዉ ባለሙያዉ የሚናገሩት። ቻይና እና አልጀሪያም ካርቦንን ማከማቸቱን ተያይዘዉታል።

«በርካታ ሃገራት ካርቦን ዳይኦክሳይድን እየሰበሰቡ ለማከማቸት እየተንቀሳቀሱ ናቸዉ። ደቡብ አፍሪቃ፤ ናይጀሪያ፤ አዉስትራሊያ እንዲሁም በርካታ ሌሎች ሃገራትም ይህን ለማድረግ እያቀዱ ነዉ። ካርቦን ወደማከማቸት መግባት የሚፈልግ ሀገር ጥሩ የሆነ የማከማቻ ስፍራ ለመለየት ተገቢዉን ካርታ መስራት ይኖርበታል።  ይህ ደግሞ ልክ ነዳጅ  ዘይት እና ጋዝ ለመፈለግ የሚደረገዉ አይነት ቅየሳ ነዉ የሚሆነዉ። ይህ ግን ካርቦን ለማምረት ሳይሆን ለማከማቸት መሆኑ መታወቅ አለበት።»

Infografik CO2-Abscheidung und -Speicherung englisch

በዚህ ረገድ አዉሮጳ በሰፊዉ እየተንቀሳቀሰች መሆኗን ያመለከቱት ዶክተር ኒልስ ፖዉልሰን በከፍተኛ የኃይል ማመንጫ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በዝቅተኛ ኢንዱስትሪዎች ደረጃም ይህን ካርቦን ዳይኦክሳይድን እየሰበሰቡ የማከማቸቱ ሥራ ጅማሮዎች ተበራክተዋል። ለምሳሌም አሉ፤

«ጀርመን ዉስጥ ከበርሊን አቅራቢያ በምትገኘዉ ኬትሲን የምርምር ማዕከል አላቸዉ፤ የዚህ ማዕከል አንቀሳቃሽ ፖትስዳም የሚገኘዉ ኬኤፍ ሴት ተቋም ነዉ። የማከማቻ ስፍራዉን ከብበዉ በመለየት ላለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት እያከማቹበት ይገኛሉ። በዚህ ስፍራ ካርቦን ዳይኦክሳይድ እንዴት ያሉ ባህሪያት እንዳሉት ሁሉ  ክትትል  እየተደረገ ሲመዘገብ ቆይቷል። አሁን  በአግባቡ ለማከማቻነት እንዲዉል ተመራማሪዎቹ አካባቢዉን ለቅቀዉ ከሚወጡበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።»

እሳቸዉ እንደሚሉትም አንድ የካርቦን ዳይኦክሳይድ ማከማቻ ስፍራ ሥራ ከመጀመሩ አስቀድሞ ይህን መሰሉ ክትትል ሊደረግበት ይገባል። በዚህም ነዉ ከባቢ አየርን እንዳይበክል የተሰበሰነዉ ካርቦን ክምችት በአካባቢ ተፈጥሮ ላይ ሌላ ጣጣ እንደሚያስከትል  ማረጋገጥ የሚቻለዉ። በአንድ ስፍራ የተዘጋጀ የካርቦን ዳይኦክሳይድ ማከማቻ እንደመጠኑ ቢለያይም ተገቢዉ የቅርብ ክትትል እየተደረገበት ከ20 እስከ 60 ዓመት በዚሁ መልኩ ሥራዉን ለመቀጠል ይችላል ። ይህን የሚያደርገዉ አካል እየተሰበሰበ የሚከማቸዉ ካርቦን እንዴት መጠበቅ እንዳለበት በዓለም አቀፍ መመሪያዉ መሠረት ተግባራዊ መሆኑንም ማረጋገጥ ይኖርበታል። በአሁኑ ጊዜ ጥቂት የማይባሉ ሃገራት ይህን ለማድረግ ፍላጎቱ ቢኖራቸዉም በርካቶቹ ግን ከአቅም አኳያ እና ይህን ካርቦንን በማከማቸታቸዉ ሊያገኙት የሚችሉት ጥቅም እያነሰባቸዉ ሊሳቡ እንዳልቻሉ አመልክተዋል።

እስከዛሬ 220 ሚሊየን ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ መሬት ዉስጥ ማከማቻዎች እንዲገባ ተደርጓል። እስካሁን ባጠቃላይ በመላዉ ዓለም ያሉት 21 የከርሰ ምድር ማከማቻዎች በየዓመቱ 37 ሚሊየን ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ይሰበስባሉ። እስከመጪዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2040 ድረስም 2,500 የምድር ዉስጥ ማከማቻዎችን ለማዘጋጀት ዕቅድ ተይዟል። ለምድራችን ሙቀት መጨመር መፍትሄ ይሆን ይሆን? ጥያቄዉ በሂደት መልስ ያገኝ ይሆናል።

ሸዋዬ ለገሠ

ተስፋለም ወልደየስ

Audios and videos on the topic