ካምፓላ-የሙሳቬኒ በዓለ-ሲመትና ተቃዉሞዉ | ፖለቲካ | DW | 12.05.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ፖለቲካ

ካምፓላ-የሙሳቬኒ በዓለ-ሲመትና ተቃዉሞዉ

የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ፣ ለ 4ኛ ጊዜ የስልጣን ዘመናቸው የሚራዘምበትንም ሆነ በፕሬዚዳንትነት አገሪቱን መግዛት የሚቀጥሉበትን ሁኔታ ፣ በዛ ያሉ መሰል አፍሪቃውያን መሪዎች በተገኙበት ልዩ ሥነ ሥርዓት፣ ቃለ-መሃላ ፈጽመዋል።

default

ይሁንና ክብረ በዓሉ፣ ባለፉት ሳምንታት ሲካሄድ በቆየውና በየጊዜው በኃይል እርምጃ ሲታረቅ በቆየው ሰላማዊ ሰልፍ ታጅቦ ነው የተከናወነው።

«እስከ ዕለተ-ሞቴ ፕሬዚዳንት ሆኜ እዘልቃለሁ» ! ይህ ነበረ የሙሴቬኒ የምርጫ ዘመቻ መፈክር! እንዲህ ዓይነቱን አባባል፤ የሰሜን አፍሪቃ ፈላጭ ቆራጭ መሪዎች በየጊዜው ተጠቅመውበታል ። በህዝብ ሀብትም አላግባብ በልጸገው ነበር። ግን ፍጻሜአቸው አላማረም። የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ፤ ባለፉት 25 ዓመታት እንሆ ሥልጣንን የሙጥኝ እንዳሉ ናቸው። ብዙዎች፤ እንደሚተቹት ሙሴቬኒ ለመራጩ ህዝብ ብዙ ገንዘብ በመበተን ነው ለመመረጥ የበቁት። በገፍ የናኙት ሺሊንግ ደግሞ፣ የሌላ አይደለም፣ በቀረጥም ሆነ በግብር ስም፤ ከህዝቡ የተሰበሰብ ገንዘብ ነው።

ሙሴቬኒ፤ ህዝብን ነጻ እናወጣለን በማለት ከተነሱትና በሥልጣን በመባለግ በሙስና ከተዘፈቁት፣ ያነገብነው ዓላማ ነው ያሉትንም ጉዳይ ፈጽሞ ከረሱት፣ ከቀድሞዎቹ አፍሪቃውያን የሓርነት ታጋዮች መካከል አንዱ ናቸው። ሰላማዊ ሰልፍ በሚያደርጉና በተቃውሞ ቡድኖች ላይ መንግሥት፤ የምርጫ ዘመቻ ይካሄድ ከነበረበት ካለፈው የካቲት ወር አንስቶ በዛቻ፤ በማዋከብና የኃይል እርምጃ በመውሰድ ለማሸማቀቅ ከመጣር የተቆጠበበት ጊዜ የለም። በተለይ ልዩው ፈጥኖ ደራሽ የፖሊስ ግብረ ኃይል ህዝቡን ከማ

ሸበር የተቆጠበበት ጊዜ የለም። የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ፤ የተጠቀሰውን የፖሊስ ኃይል፤ በግፍ እርምጃ ሰዎችን ቁም-ስቅል በማሳየት፤ ያለህግ እንዳሻው ይዞ በማሠርና በመደብደብ የታወቀ ነው ሲል በጥብቅ ይነቅፋሉ። መገናኛ ብዙኀንም ከተጠናከረው የጭቆና እርምጃ አላመለጡም። ሰላማዊ ሰልፈኞችና ፖሊስ በተጋጩበት ዕለት በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያለው ቴሌብዥን፤ ለአገሩ ጉዳይ ደንታቢስነት በማሳየት፤ የእንግሊዞቹን ኬትና ዊልያም ሠርግ ነበረ በቀጥታ ለእይታ ያቀረበው። አንድ ዘመን «የአፍሪቃ ዕንቁ » የተባለችው ለምለሚቱ ዩጋንዳ ምን ነካት? የቀድሞውም ፤ የአሁኑም መሪ ይህችን አገር ወደ ምንድን ነው እንድታመራ በማድረግ ላይ ያሉት? ሙሴቬኒ፤ ምነው ሥልጣንን እንዲህ የሙጥኝ አሉ? የመባልዕትና የመሳሰሉ ዕቃዎች ዋጋ እጅግ ናረብን ብለው ብሶት ለመግለፅ አደባባይ የወጡ ሰላማዊ ሰልፈኞችን ለምንድን ነው የሚጨቁኑት?ምናልባት እንደ ሰሜን አፍሪቃ መሪዎች፤ ከህዝቡ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት እርግፍ አድረገው በመተው በሌላ ዓለም ውስጥ ይሆን ወይ የሚዋዥቁት?ብዙዎቹ የዩጋንዳ ቤተሰቦች በቀን አንድ ጊዜ የበሰለ ምግብ ለመመገብ የቱን ያህል እንደሚጨነቁ ፕሬዚዳንቱ ማወቅ ተስኗቸው ይሆን?

አንዳንድ ፣ ንዴት መጥፎ ቃል የሚያናግራቸው ሰዎች እንደሚሉት ፤ ለህዝቡ የተድላ ኑሮ ዋስትና ይሰጣል የሚባለው በቅርብ ጊዜ የተገኘው የተትረፈረፈ የድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ሀብት፣ ቋቱ ጠብ ላይል ይችላል። ጠበብት እንደሚገምቱት የተገኘው ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት በብዙ ቢሊዮን በርሜል የሚገመት ነው። ነዳጅ ዘይት ከተገኘበት አካባቢ ኑዋሪዎች ቀየአቸውን ለቀው ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ መገደዳቸውም እየተነገረ ነው። ለህዝብ ታስቦ ከተሠራ፣ በተጠቀሰው የተፈጥሮ ሀብት እጅግ የደኸዩትን ዜጎች ኑሮ ማሻሻል አይገድም። ነገር ግን ናይጀሪያንና ቻድን ከመሳሰሉ አገሮች እንደታየው፤ በነዳጅ ዘይት ሀብት መክበር፤ ለሰፊው ህዝብ እርግማን ሆኖ መገኘቱን ለተፈጥሮ አካባቢም ጥፋት ማስከተሉን ነው መታዘብ የተቻለው። እስከ ዕለተ ሞት ፕሬዚዳንት ሆኖ መቀጠል--የሙሴቬኒ ህልም ነው። ለብዙዎች ዩጋንዳውያን ፤ በተለይ ሌላ መሪ አይተው ለማያውቁት የዩጋንዳ ወጣቶች ደግሞ ፣ ይህ በእንቅልፍ ልብ እንደሚያስጨንቅ ቅዠት ነው።

አንድርያ ሽሚት

ተክሌ የኋላ

ሂሩት መለሠ