ካለዩናይትድ ስቴትስ የአዉሮጳ ዕጣ ምን ይሆን? | ዓለም | DW | 02.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ካለዩናይትድ ስቴትስ የአዉሮጳ ዕጣ ምን ይሆን?

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳንን ወታደራዊ አቅም ግንባታ እና የሀገራቸዉን የንግድ ግንኙነት በተመለከተ የሚሰነዝሯቸዉ አስተያየቶች አዉሮጳና አሜሪካ ገንብተዉት የኖሩት ወዳጅነት ወዴት ያመራል የሚል ጥያቄ አስነስቷል። የአዉሮጳ ወታደራዊ ጉዳይ ጠበብትም፤ አጋጣሚዉ አዉሮጳ ቆም ብላ ማሰብ ከሚገባበት ጊዜ ደርሳለች ይላሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:21

ጥያቄ ላይ የወደቀዉ ዘመን የተሻገረ ትብብር፤

የጀርመን የንግድ ሥልት ላይ የሰላ ትችት የሰነዘሩት የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ፤ አስተማማኝ ያልሆነ ጉድኝት ተስፋ አይጣልበትም በሚል የመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ዜጎቻቸዉንም ሆነ አዉሮጳን በማሳሰብ የመልስ ምት አግኝተዋል። ከአትላንቲክ ማዶ ለማዶ የተወጠረዉ ግንኙነት ግን የትራምፕ ቃል አቀባይ ሾን ስፓይሰር እንደሚሉት «በደህና ሁኔታ እየተጓዘ » ላለመሆኑ  ትራምፕ ዳግም ትናንት በተለመደዉ የትዊተር መስኮታቸዉ ብቅ ብለዉ ጀርመን ላይ የሰነዘሩት ጠንካራ አስተያየት አመላካች ነዉ። ትራምፕ ፤ «ጀርመኖች ላይ የሚሳኤል ንግድ ጉድለት አለ፤ በዚያም ላይ ጀርመኖች ለኔቶ እና ወታደራዊዉ ዘርፍ የሚያወጡት ገንዘብ በጣም ትንሽ ነዉ፤ ይህ ደግሞ ለዩናይትድ ስቴትስ በጣም መጥፎ በመሆኑ ይለወጣል።» ብለዋል። የጀርመን ባለስልጣናት በበኩላቸዉ እንደ አዉሮጳ ኅብረት አባል ሀገር፤ ከአሜሪካን ጋር የሁለትዮሽ የንግድ ዉይይት ማድረግ እንደማይችሉ፤ በፍጥነትም ወታደራዊ ወጪዉ ን ከፍ ለማድረግም ዝግጁ እንዳልሆኑ እያሳሰቡ ነዉ።

የአዉሮጳ ወታደራዊ ጠበብት ትራምፕ አንዳንድ የአዉሮጳ መንግሥታት ለሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን የመከላከያ አቅም የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ትንሽነቱን መናገራቸዉ የመጋለጥ ስሜት እንዲያድርባቸዉ አድርጓል ባይ ናቸዉ። ያምሆኖ ግን አዉሮጳ ከዚህ የበለጠ በጉዳዩ ላይ በወጉ ማሰብ የሚገባት ጊዜ አጋጥሟት እንደማያዉቅ ያምናሉ። ከቡድን ሰባቱ ጉባኤ በኋላ አንጌላ ሜርክል በወደፊት ዕጣ ፈንታዋ አዉሮጳ ራሷን ለመቻል መንቀሳቀስ እንዳለባት ያሳሰቡትም በጥንቃቄ መጤን እንደሚገባዉ ያሳስባሉ። የዋሽንግተን ከምዕራብ አጋሮቿ ጋር ያላት ወታደራዊ የመደጋገፍ ባህል እና የኑኩሊየር ከለላ መለወጥም፤ በአካባቢዉ ሩሲያ በኃይሉ ሚዛን ላይ ሊኖራት የሚችለዉን ክብደት ሊያጎላዉ እንደሚችልም ግምታቸዉን ይሰነዝራሉ።  የቤልጅግ የሮያል የዉጭ ግንኙነት ጉዳይ ተቋም ዳይሬክተር ስቫን ቢስኮፕ ፤ እንደሚሉት በጦር ኃይል ደረጃ ሲታሰብ 28ቱ የአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት በጋራ ያላቸዉ 1,5 ሚሊየን ወታደር በራሱ ጠንካራ ከመሆኑም በላይ፤ ሩሲያ ካላት የሠራዊት መጠን ጋር አቻ ነዉ።

ከአዉሮጳ ዉጭ ሠራዊት የማዝመቱ ጉዳይ ሲታሰብ ግን ያለ ዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ ጥያቄ ላይ እንደሚወድቅ ቢስኮፕ ይዘረዝራሉ።

«እኔ እንደማስበዉ ሩሲያዎች አዉሮጳ ብቻዋን እንኳን ብትሆን በወታደራዊ ረገድ ለአዉሮጳ ስጋት አይደሉም። ይህ ግን እኛ ጠንካሮች ስለሆንን ሳይሆን፤ እነሱ ከእኛ የባሉ ደካሞች ስለሆኑ ነዉ። ነገር ግን ለምሳሌ ወደ ሊቢያ ሠራዊት ለመላክ ቢታሰብ፤ ወታደራዊ ኃይል ከራስ ግዛት ወደዉጭ በመላኩ ዕቅድ ካለ ዩናይትድ ስቴትስ አንችልም። ምክንያቱም ስልቱን ለማዘመን የተደረገነገር የለም፤ ለምሳሌ የረዥም ርቀት መጓጓዣዉ፣ ሳተላይቱ፣ ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች፣ የአዉሮፕላን ነዳጅ መሙያዎቹ ሁሉ በአሜሪካ አቅም የሚሟሉ ናቸዉ። »

እናም ይላሉ ቢስኮፕ የጀርመኗ መራሂተ መንግሥትም ሆኑ የፈረንሳዩ አዲሱ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ፤ ራሷን የቻለች አዉሮጳ ማየት ከፈለጉ በእነዚህ አስፈላጊ ነገሮች ላይ አቅማቸዉን ማፍሰስ ይጠበቅባቸዋል። በተቃራኒዉ ግን አዉሮጳዉያን ሃገራት ለኔቶ ከዓመታዊ ገቢያቸዉ ሁለት በመቶዉን እንኳ የማዋጣት ግዴታቸዉን በአግባቡ እየተወጡ እንዳልሆነ ነዉ የሚነገረዉ። ትራምፕ አሜሪካን ትቅደም መፈክራቸዉ ከሆነ ሰነባብቷል፤ አዉሮጳም ለራሷ በማሰብ «አዉሮጳ ትቅደም» ማለት የጀመረች ይመስላል። ይህ አካሄድ ወደፊት ተጠናክሮ በአንድ ወቅት በጋራ ቆሞ የነበረ ኃይል ለየብቻዉ አቅሙን ማጎልበት ልጀምር የሚል ከሆነም ዉጤቱ አፍራሽ ሊሆን እንደሚችል ቢስኮፕ ያሳስባሉ።

« ይህ አሉታዊ ዉጤት ነዉ የሚያስከትለዉ ምክንያቱም ሰዎችን ጠላቶች ያደርጋል። የተሻለ የሚሆነዉንም ለቡድኑ ጠላት ነዉ።»

ዶናልድ ትራምፕ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ሆነዉ ስልጣን ላይ መዉጣታቸዉ ይፋ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ የአዉሮጳ መንግሥታት ከአትላንቲክ ማዶ ዘመናትን ተሻግሮ የኖረዉ ግንኙነት ምን ሊሆን ይችላል በሚል የየግላቸዉን ግምት ይዘዉ ሲጠባበቁ ቆይተዋል። ወደሳዉድ አረቢያ ተጉዘዉ ከአረብ ሃገራት መንግሥታት ጋር ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ተማምለዉ ወደብራስልስ የመጡት ትራምፕ በኔቶም ሆነ በቡድን ሰባቱ ጉባኤ ላይ ከምዕራባዉያን አቻዎቻቸዉ ጋር ከተወያዩ በኋላ ያሳደሩት ስሜት፤ አዉሮጳዉያንን ስለራሳቸዉ እንዲያስቡ አድርጓል። የቤልጅግ የሮያል የዉጭ ግንኙነት ጉዳይ ተቋም ዳይሬክተር ስቫን ቢስኮፕ ይህን እንደመልካም አጋጣሚ መዉሰድ ይገባል ባይ ናቸዉ።

«የትራምፕ እዚህጋ መምጣት እጅግ ጠቃሚ ነዉ። ምክንያቱም ሰዎች በዩናይትድ ስቴትስ ላይ ሙሉ ሙሉ ጥገኛ መሆን አደገኛ መሆኑን እንዲያስተዉሉ ያደርጋል። ይህም ማለት በዩናይትድ ስቴትስ የምርጫ ዉጤት ላይ መተማመን በኃይትሃዉስ ዉስጥ ስለአዉሮጳ የሚገደዉ ሰዉ እንደማያመጣ ተረድተናል። ይህ በጣም አስፈላጊ ትምህርት ይመስለኛል። ከዚህ አልፎም በእኔ አስተያየት በአሁኑ ጊዜ የአዉሮጳ ፍላጎት እና የአሜሪካ ፍላጎት የሚመሳሰልበት አጋጣሚ ከቀድሞዉ ጋር ሲተያይ ትንሽ ነዉ።»

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች