ኪውባና ትዝታችን | ባህል | DW | 01.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

ኪውባና ትዝታችን

በኪዩባ የኖሩ ኢትዮጵያዉያን ተማሪዎች አባታችን የሚልዋቸዉ የዘጠና ዓመቱ ፊደል ካስትሮ ከዚህ ዓለም በመሞታቸዉ አዝነዋል። ኩዩባ ለኛ ለኢትዮጵያዉያን ብቻ ሳይሆን ለመላ አፍሪቃ ብሎም ለመላ ጭቁን ሕዝብ አባት ነዉ ሲሉ ነዉ፤ ለፊደልና ለኪዩባ ፍቅራቸዉን የሚገልጹት። በጨቅላ እድሜያቸዉ ከቤተሰቦቻቸዉ ተነጥለዉ ወደ ኪዩባ የሄዱት እነዚህ ተማሪዎች፤

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:37
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
15:37 ደቂቃ

ኪውባና ትዝታችን

ወደኪዩባ ሲጓዙ ብዙ ትዝታዎች አልዋቸዉ። ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱም ሁኔታዉን ለመልመድ ቀላል ሁኔታ አልገጠማቸዉም።   

« ምን አልሽ አልሽኝ አላዉቅም ጠዋት ነዉ በጓሮ በኩል ወጥቼ ነበር። ወደቤት ስገባ ባለቤቴ በድንገት የፊደል ካስትሮ ሞትን ነገረኝ ። ምንም አላኩም ወንበር ፈልጌ ተቀምጥኩ እንባዬ መዉረድ ጀመረ። ከዝያ በኋላ የሆነዉን አላዉቀዉም ፊደል ልክ እንደ አባቴ ነዉ አይሙት አልልም እድሜዉ ነዉ ይሙት ግን ፤ ለኪዩባ ተማሪዎች በሙሉ ፊደል ካስትሮ ከወላጅ አባታችን ቀጥሎ ምሳልያችን ፊደል ነዉ። ፊደል እድለኛ ነዉ በእሱ እድሜ በጣም የብዙ ሰዎችን ሥራ ሰርቶ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ለዉጦ ነዉ ያለፈዉ። ፊደልን ሁሌም እናስታዉሰዋለን። እናም,,,»

እናም ትቀጥላለች ወ/ሮ ገነት ወልደማርያም።ገነት ወልደማርያም።  የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትዋን ብሎም የኮሌክጅ ትምህርትዋን ያጠናቀቀችዉ በኪዩባ ነዉ። አባቴ ስትል የምትጠራቸዉ የኪዩባዉ ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት እንዳሳዘናት የምትናገረዉ ወ/ሮ ገነት ለኪዩባ ሕዝብ ምስጋናን ለማቅረብ ፍቅሩዋን ለመግለጽ ቤተሰቦችዋን ልጆችዋን ያዛ የዛሬ ሁለት ዓመት ወደ ኪዩባ ተመልሳ የትምህርት ቤት ባልንጀሮችዋን አግኝታለች። 

በሰሜናዊ ኢትዮጵያ በነበረዉ ጦርነት አባትዋን ማጣትዋ የምትናገረዉ ገነት ወልደማርያም የነጻ ትምህርት እድልን አግኝታ ወደ ኪዩባ ያመራችዉ የ 7 ኛ ክፍል ተማሪ  12 ዓመት ልጅ ሳለች ነዉ። በርግጥ ወዴትና ለምን እንደምትሄድ የምታዉቀዉ ነገር አልነበራትም ከእናትዋ ከቤተሰቦችዋ መለየትዋ በተመለከተ ለማዘን የነበራትም ጊዜ ብዙም አልነበረም። በኪዩባ የተደረገዉ አቀባበል ልዩ ነበር ለህጻናቱ በከረጢት ሙሉ ነዉ ቸኮላታ የቀረበልንም ትላለች። ግን 1200 የሚሆኑትን ሕጻናት የያዘዉ ግዙፉ መርከብ ከአሰብ ተነስቶ ኪዩባ የባህር ወደብ እስኪደርስ የአንድ ወር ጊዜ ፈጅቶበታል ፤ ከአዲስ አበባ ተነስተዉ በአሰብ ወደብ ለመድረስም ጉዞዉ ቀላል አልነበረም።  

« ከቤተሰብ ስትነጠይ ታለቅሻለሽ ግን ወዴት እንደምትሄጅም አታዉቂዉም። ለሕጻን ይህ የጨዋታ ያህል ነበር ። ትዝ እንደሚለኝ ጉዞዉ መጀመርያ ከአዲስ አበባ ወደ አሰብ ነበር። ትዝ ይለኛል መንገድ ላይ አድረናል እጅግ ከፍተኛ ሙቀትም ነበር። አሰብ እንደደረስን በጣም ትልቅና ዉብ የሆነ ፓርክ ዉስጥ ምሳ በላን። በዝያን ጊዜ ወደብ መሆኑን እንኳ አላዉቅም ነበር። ትዝ የሚለኝ የሆነ ትልቅ ግድግዳ ነገርን አስታከን ተሰልፈን መግባታችንን ነዉ። በዝያን ጊዜ የሆነ ቤት ዉስጥ የገባን ነበር የመሰለንትልቅ ሕንጻ ነዉ የሚመስለዉ። መርከብ እንደሆነም አላወቅምን ምክንያቱም መርከብ አይተን አናዉቅም። ከዝያ ሲንቀሳቀስ ነዉ መርከብ መሆኑን ያወቅነዉ። ከዝያም አንድ ወር አካባቢ ያህል ተጉዘን ነዉ ኪዩባ የደረስነዉ። በአጠቃላይ 1200 ሕጻናት ነበርን። ኩዩባ ሃቫና እንደደረስን ደማቅ አቀባበል ተደረገልን ከዝያ በትንንሽ መርከብ ወደ ወጣቶች ደሴት ይዘዉን ሄዱ ከዝያ ነዉ ለቅሶ የተጀመረዉ። »

ለምን አለቀሳችሁ?

«ለቅሶ የሆነበት ምክንያት ደሴቱ ላይ እንደደረስን ወደ ተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚወስደዉ አዉቶቡስ የተመደቡለትም ልጆች ሲወስድ ወንድሞቻቸዉንና እህቶቻቸዉን ያላገኙ ልጆች በድንጋጤ ማልቀስ ጀመሩ። ድልድሉ የተደረገዉ ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚሄዱት በአንድ አዉቶቡስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን የሚከታተሉት በሌላ ወገን በመለያየታቸዉ ነበር ገሚሱ እህት ወንድሙን ማግኘት ያልቻለዉ። እዝያ እስክንደርስ ግን በከረጢት ሙሉ ቸኮላት ተሰቶን ስለነበር እሱን እየበላን ሳቅና ጨዋታ ብቻ ነበር።»

በካናዳ ቶሮንቶ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ገነት ወልደማርያም የፊደል ካስትሮን ሞት ስትሰማ በጥልቅ ሃዘን ማልቀስዋን ትናገራለች።  ሌላዉ በ10 ዓመት እድሜ ወደ ኪዩባ የተላኩት አቶ ሳምሱን አለማየሁ በቴክኒክ ሞያ ሰልጥነዉ ከስምንት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። የፊደልን ሞት ስሰማ ይላሉ ።  

«በኪዩባ የተማርን ኢትዮጵያዉያን ለኩባ ሕዝብና ለፊደል ካስትሮ የተለየ አመለካከት ነዉ ያለን። ወደ ኪዩባ የሄድን ሰዎች በተለያዩ ጦርነቶች አባቶቻችን ያጣን ነን ። ፊደል ካስትሮ በሰጠዉ እድል ምክንያት ቤተሰቦቻችን ያጣን ልጆች የአባቶቻችን የደም ካሳ ይሆናል በሚል። ፊደል ካስትሮ ያን ጊዜ ይህን እድል በመስጠታቸዉ ዛሬ ቁጭ ብዩ ሳስበዉ በምንም አይነት ምክንያት የማናገኘዉን እድልን ማግኘታችን ትልቅ ዋጋ ያለዉ ነዉ። ምንም እንኳ በአስር ዓመት እድሜ ከእናት ጉያ ወጥቶ መሄድ ከባድም ቢሆን ፊደል ካስትሮ የሰጡት እድል ለኔ ብቻ አይደለም ፤ ከአፍሪቃ በብዙ  ሺህ የሚቆጠሩ ተምረዋል ከኩዩባ ዜጎች በላይ መብታችን እና ምቾታችን ተከብሮልን ነዉ የኖረዉ። ሕዝቡ ተቀብሎን ባህሉን አዉቀን እንድንኖር ያደረጉ መሪ ነበሩ ፊደል ።»     

የኩባን ባህል የኩባን ሕዝብ አፍቃሪዋ ወ/ሮ ገነት እንደምትለዉ ኢትዮጵያዉያኑ በኪዩባ ምግቡን ለመላመድ ብዜ ጊዜ አለጠየቀብንም ፤

« ወደ ኪዩባ ለመሄድ ስንዘጋጅ መጀመርያ ታጠቅ ጦር ሰፈር ነበርን ፤ እዝያ ስንኖር ሩዝ ምናምን ይቀርብልን ነበር። ሹካ አያያዝ ሁሉ ያስተምሩን ነበር ትዝ ይለኛል። ለነገሩ የፈረንጅ ምግብ ማን ይጠላል ዳቦ ምናምን ደግሞ ልጅ ይወዳል። እንጀራ ግን ለመጨረሻ ጊዜ የበላነዉ እዝያዉ ታጠቅ ጦር ሰፈር ነዉ። የኪዩባ ምግባቸዉም ያዉ ሾርባ ሩስ ምናምን ነዉ በርግጥ የማስታዉሰዉ ሾርባ ዉስጥ የዶሮ እግር ይቸምሩበት ነበር የዶሮ እግር ጥፍሩ ያለበትን ያ የማናዉቀዉ ነገር በመሆኑ መጀመርያ አካባቢ በጣም ይቀፈን ነበር ቆየት እያለ እግሩን እያወጣን ሾርባዉን መጠጣትና መብላት ጀመርን። ከዝያም ያዉ አንዱ መብላት ሲጀምር ሁላችንም መብላት ጀመርን ለካ እንዲህ ይጣፍጥ ነበር ብለን አሰብን ። አሁን የኪዩባ ተማሪዎች ያንን ያለምንም ችግር እንበላለን። » 

ሕጻናቱ  ተማሪዎች አማርናን ባህል እንዳይረሱ አማርና የታሪክ አስተማሪዎቻቸዉ አብረዋቸዉ ወደ ኪዩባ አቅንተዋል። ሕጻናቱ አንረዉ ስለኖሩም አማርና ቋንቋን ሳይረሱ ነዉ የተመለሱት ። የኪዩባን ባህልንም ይዘዉን ነዉ የተመለሱት ፤ በዚህም በተለይ ሴቶች ብዙ ችግር እንደገጠማቸዉ ወ/ሮ ገነት ወልደማርያም ትናገራለች።

« እንደሚመስለኝ እኛ አማርና ያልጠፋብን በቡድን ስለኖርን ነዉ ። ባህሉንም ቋንቋዉንም የሚያስተምረን ነበር። ይህ ይህ ሁሉ እንዳይጠፋ በደንብ አስበዉበት ነዉ። እዝያ የወሰዱን ቦታ በቤድን ያስቀመጡን። አስራ ሁለተኛ ክፍልን እስክንጨርስ ድረስ ከሌላዉ ተማሪ አልቀላቀሉንም። ወደ ኮሌጅ ስንገባ ነዉ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር የቀላቀሉን። በርግጥ እሁድና ቅዳሜን አንዳንድ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን እንድናደርግ ይወስዱናል ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ይቀላቅሉናል ዉኃ ዋና እግር ኳስ በመሳሰሉት ጨዋታዎች ላይ ማለቴ ነዉ»

ሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማርያምስ ይጎበኙዋችሁ ነበር?  

«አዎ ይጎበኙን ነበር እኔ እዝያ ሳለሁ አንዴ ነዉ ሁለቴ መጥቶ ነበር። ዉስጥ ድረስ ገብቶ ነዉ የሚጎበኘን። ለእዉነት ለመናገር እሱም ቢሆን ጥሩ ፕሬዚዳንት ነበር። እያንዳንዳንዱ መንግስት ጥሩና መጥፎ ጎን አለዉ እኔ በበኩሌ መንግስቱ በሁለተኛነት እንደ አባታችን የምናየዉ ነዉ። ያኔ በርግጥ እኛ ወደ ኪዩባ ስንላክ እናቶቻችን አልቅሰዋል እናቴ ነፍስዋን ይማራትና እንደነገረችን ከሆነ ልጆቻችንን በቡና ሸጥናቸዉ ነበር የምንለዉ ብላኛለች።  እናቴ እንድንሄድ አትፈልግም ነበር እያለቀሰች ነዉ የሰጠችን። አሁን ተመልሰን ከመጣን በኋላ ግን በኛ መማር እና ከፍተኛ ቦታ መድረስ በጣም ነዉ የምታደንቀዉ ምነዉ ያ ካስትሮ እነዚህንም በወሰደና ባስተማረልኝ ነበር የምትለዉ ። »

ኢትዮጵያ እያላችሁ ከቤተሰቦች ጋር ትገናኙ ነበር በደብዳቤ አልያም ወደ ኢትዮጵያ ጉጉዞ ታደርጉ ነበር?  

ደንዳቤ ወደ ቤት ጻፉ እየተባሉ በግዳጅ ደብዳቤ ይጽፉ የነበሩት ኢትዮጵያዉያኑ የኩዩባ ተማሪዎች ትምህርታቸዉን አጠናቀቁና ወደ ሃገር ተመለሱ ተባሉ፤ በአፍላ እድሜ ላይ የነበሩት ተማሪዎች ደሰተኞች አልነበሩም። ኢትዮጵያም ይዘዉት የመጡት ባህል አልተወደደላቸዉም ። ቢሆንም ዛሬ ከ 5 ሺህ የሚበልጡት የዚያን ጊዜዎቹ አፍላ ሕጻናት ለከፍተኛ ትምህርት በቅተዉ፤ በኢትዮጵያም ሆነ በተለያዩ የዓለም ሃገራት በተለያዩ የከፍተኛ ሞያ ላይ በማገልገል ይገኛሉ።  ሙሉዉን ቅንብር ከድምጽ ዘገባዉ እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ

 

Audios and videos on the topic