ኪንጄኬቲሌ፥ የታንዛኒያ የነጻነት ተጋድሎ ፈር ቀዳጅ | አፍሪቃ | DW | 05.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ኪንጄኬቲሌ፥ የታንዛኒያ የነጻነት ተጋድሎ ፈር ቀዳጅ

ኪንጄኬቲሌ ንጓሌ በ20ኛው ክፍለ-ዘመን መባቻ አኹን ታንዛኒያ ብለን የምንጠራት ሀገር ዜጎች የጀርመን ቅኝ ገዢዎችን ተቃውመው እንዲታገሉ አበረታትተዋል። ተከታዮቻቸው ጥይት እንዳይመታቸው የሚጋርድ የተቀደሰ ውኃ አለኝ ሲሉ ቃል በመግባታቸውም ይታወቃሉ። አንዳንዶች ኪንጄኬቲሌን ለሕዝባቸው ተስፋ እና ብርታትን ያሰነቁ ጀግና አድርገው ይመለከቷቸዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:12

ታንዛኒያዊው ኪንጄኬቲሌ ንጓሌ

ኪንጄኬቲሌ ንጓሌ በአፍሪቃ ታሪክ አወዛጋቢ ሥፍራ አላቸው። በ20ኛው ክፍለ-ዘመን መባቻ አኹን ታንዛኒያ ብለን የምንጠራት ሀገር ዜጎች የጀርመን ቅኝ ገዢዎችን ተቃውመው እንዲታገሉ አበረታትተዋል። ተከታዮቻቸው ጥይት እንዳይመታቸው የሚጋርድ የተቀደሰ ውኃ አለኝ ሲሉ ቃል በመግባታቸውም ይታወቃሉ። አንዳንዶች ኪንጄኬቲሌን ለሕዝባቸው ተስፋ እና ብርታትን ያሰነቁ ጀግና አድርገው ይመለከቷቸዋል። ሌሎች ደግሞ ሰውዬው ሕዝባቸውን ወደ ሞት የነዱ አታላይ ነበሩ ይሏቸዋል።

በምሥራቅ አፍሪቃዋ ታንዛኒያ ከረዥም ጊዜያት በፊት የኾነ ሰው ሐይቅ ውስጥ ተሰውሮ ለ24 ሰአታት በጥልቊ ውኃ እንደተነከረ መቆየቱን የሚተርክ አፈ-ታሪክ አለ። አፈታሪኩ ሲቀጥል፦ ሰውዬው ከውኃው ሲወጣ ልብሶቹ አንዳችም ርጥበት ሳይነካቸው ደረቅ ነበሩ ይላል። ይኽ ሰው በእጆቹ አፍሶ የወጣው ውኃም አስማታዊ ከመሆኑ የተነሳ ፈሳሽን ወደ ጥይት ይቀይራል እየተባለ ይነገርለት ነበር። ሰውዬው ኪንጄኬቲሌ ንጓሌ ይባላሉ። እነሆ የእኚህ ሰው ታሪክ።  

እ.ጎ.አ. በ1898 የጀርመን ቅኝ ገዢዎች ያኔ ታንጋኒካ ተብሎ የሚጠራውን የታንዛኒያ አብዛኛውን ክፍል ወረሩ። ነዋሪውንም ለጉልበት ብዝበዛ በመዳረግ ብሎም ከፍተኛ ግብር በመጣል እጅግ ጨካኝ አስተዳደር ተከሉ። ሀገሬው ተማረረ፣ ተሰቃዬ።  

በ1904 ግን ሁሉን ያውቃሉ የተባሉ አንድ ሰው ብቅ ሲሉ የነዋሪው ተስፋ ለመለመ፤ ሰውዬው ኪንጄኬቴሊ ይባላሉ። ውስጤን እባብ ተቆጣጥሮታል ይሉ የነበሩት እኚህ ሰው ከማሽላ ዱቄት እና ከውኃ ተቀይጦ የተዘጋጀ «ማጂ» የተባለ ጥይት መከላከያ ፈሳሽ አንዳች መንፈስ እንደሰጣቸውም አስወሩ።  

ሰዎች በቀላሉ አምነው ተቀበሏቸው። እናም ሀገሬው ጦሩን እየነቀነቀ በማጂ ውኃ መነከሩን ተያያዘው። የመጀመሪያዎቹ የማጂ ማጂ ጦረኞች የሚባሉትም ጀርመኖችን መፋለም ጀመሩ ይላሉ የዳሬሠላም ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር በርትራም ማፑንዳ።

ዓማጺያኑ የዘመቻ ዝግጅታቸው በተቀላጠፈበት ወቅት ባሕላዊ ሐኪሞች እና ዐዋቂዎች አንዳች ግራ የኾነ ነገር ጠምቀው ለሀገሬው በማደል ላይ ናቸው መባሉ ጀርመኖች ዘንድ ደረሰ። ዐዋቂዎቹ ሲጠየቊም እንደ አሣማ ያሉ እንስሳትን ከእርሻቸው ለማራቅ ያደረጉት መኾኑን በመግለጥ ዐይናችንን ግንባር ያድርገው አሉ።

ዓማጺያኑ በአካባቢው የሚገኙ የጀርመን ባለሥልጣናት ላይ ጥቃት ከከፈቱ በኋላ ግን ኪንጄኬቲሌ በሀገር ክህደት ወንጀል በሚል በስቅላት ተቀጡ። ምንም እንኳ ማጂ ውኃቸው ተከታዮቻቸውን ከጀርመኖች ጥይት ባይታደግም ዓመጻ በየሥፍራው እንዲስፋፋ ግን ሰበብ ኾኗል። ለሚቀጥሉት ኹለት ዓመታትም 20 የተለያዩ ጎሣዎች ጀርመኖችን ተፋልመዋል። እንደ ፕሮፌሰር ማፑንዳ ከኾነ ኪንጄኬቲሌ የዘሩት የተስፋ እና የእምነት ዘር መክኖ አልቀረም። 

ያን እምነት በሰዉ ልብ ባያሰርፁ ኖሮ ማንም ባልተፋለመ ነበር። ባይፋለሙ ኖሮ ደግሞ በአፍሪቃ ፀረ ቅኝ አገዛዝ ተጋድሎ ጉልኅ ሥፍራ ከሚሰጣቸው አመፃዎች አንዱ ስለኾነው ስለ ማጂ ማጂ አመፃ ዛሬ ማውራቱ ባላስፈለገን ነበር። 

ጀርመኖች ዓመፃውን ለማዳፈን በከፈቱት ጥቃት ከ180,000 እስከ 300,000 የሚገመት ሰው አልቋል። ረሐብ እንዲከሰትም አድርጓል። ምንም እንኳ ጀርመኖቹ በወቅቱ ባይሸነፉም ዓመጻው ጠቃሚ ማሻሺያዎችን እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል። ኪንጄኬቲሌ በአኹኑ ወቅት ስለሚታወሱበት ለየት ያለ ነገር ፕሮፌሰር ማፑንዳ እንዲህ ይገልጣሉ። 

ልንረዳ የሚገባን ነገር ምንድን ነው፤ ሰዎች ሥነ-ልቦናቸው ከፍ እንዲል፤ እምነታቸውም እንዲጸና ከረዳህ በቊርጠኝነት እንደሚፋለሙ ነው። እንደ እኔ አስተሳሰብ ኪንጄኬቲሌ ጀግና ነበሩ! ሕዝቡን የዋሹ ቀጣፊ ናቸው ብለው የሚያስቡም አሉ። 

ጀግናም ኾኑ አልኾኑ ኪንጄኬቲሌ በታንዛኒያ ታሪክ ልዩ ሥፍራ የሚሰጣቸው ግለሰብ ናቸው። የነፃዋ ታንጋኒካ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ኒዬሬሬ የማጂ ማጂ ዓመጻን ሀገራቸው በ1961 ለተቀዳጀችው ነጻነት የተጋድሎው መንደርደሪያ አድርገው ቆጥረውታል።  

ጄምስ ሙሐንዶ/ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

 ይህ ዘገባ አፍሪቃዊ ሥረ መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አካል ነው።

 This report is part of African Roots, a project realized in cooperation with the Gerda Henkel foundation.

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች