ኪቤራን መልሶ የማልማት እቅድ | አፍሪቃ | DW | 13.07.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ኪቤራን መልሶ የማልማት እቅድ

በኬንያዋ ዋና ከተማ የሚገኘው የኪቤራ መንደር በአፍሪቃ ትልቁ የጎስቋሎች መንደር እንደሆነ ይነገራል። በዚህ መንደር ለ50 የመኖሪያ ቤቶች አንድ የመጸዳጃ ቤት ብቻ ሲሆን ያለው፣ ከመንደሩ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ግልጋሎት የሚያገኙት 20 ከመቶው ብቻ እንደሆኑ ይነገራል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:24

ኪቤራን መልሶ የማልማት እቅድ

በኬንያ የኪቤራ የድሆች የመኖሪያ መንደር የመልሶ ማልማት እቅድ በተሰሩ ቤቶች መካከል ውሃ ይፈሳል-ከታቀደለት የፍሳሽ ማስወገጃ ውጪ።የስድሳ ዓመቷ ማማ ሳቤቲ ኦምባሶ በመልሶ ማልማቱ እቅድ ተጨንቀዋል፤ግራም ተጋብተዋል።« እኛ ድሆች ነን። ድሆች እነዚህን ቤቶች ማግኘት አይችሉም። ወዴት ይሂዱ?»

ማማ ሳቤቲ ኦምባሶ ከመኖሪያ መንደራቸው ተነስተው በመልሶ ማልማት እቅዱ ወደ ተገነቡ አዳዲስ ቤቶች ከሚዘዋወሩ 600 ቤተሰቦች አንዷ ናቸው። ነገር ግን ከእድለኞቹ መካከል ላይሆኑ ይችላሉ።በድጎማ ከተገነቡት ቤቶች መካከል አንዱን ለማግኘት ለግንባታ ከወጣው 13,000 ዶላር አስር ከመቶውን መሸፈን ይኖርባቸዋል። ማማ ሳቤቲ ከኪቤራ የሚነሱት ግን ብቻቸውን አይደለም።በኪቢራ የሶዌቶ መንደር የሚኖሩ ከ300 በላይ ቤተሰቦች ከ10 ዓመት በፊት በተጀመረውና በሁለተኛው ዙር የመልሶ ማልማት የተገነቡ ቤቶችን ሳያገኙ ሊቀሩ ይችላሉ። ማማ ሳቤቲ በቀደመ የመኖሪያ መንደራቸው የነበራቸውን ማህበራዊ ግንኙነት ማጣታቸውም ያንገበግባቸዋል።

«መንግስት ወደ መጣሁበት ሊመልሰኝ ይገባል። በዚያ ጨው ከጎረቤቶቼ መበደር እችላለሁ። አስር ሺልንግ ቢቸግረኝ ከጎረቤቶቼ ማግኘት ቀላል ነው። አሁን ማን ሊረዳኝ ይችላል?»

የመንደሩ ነዋሪዎች አዳዲሶቹ ቤቶች ከተገነቡበት ወጪ 10 ከመቶውን መሸፈን ባለመቻላቸው እድሉን በመጠቀም ሃብታሞች ቤቶቻቸውን እየወሰዱባቸው እንደሆነ ያማርራሉ።

«ወደዚህ ስንመጣ የመኖሪያ ቤቶቹ ተጠናቀው እስኪገነቡ እንድንጠብቅና ከዚያ ቤታችን እንደሚሰጠን ተነግሮን ነበር። አሁን ግን ሃብታሞች ቤቶቻችንን እየወሰዱብን ነው። ይህን እቅድ የጀመሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው። አሁን ፕሬዝዳንቱ ምክትላቸውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ እዚህ ድረስ መጥተው ሊያነጋግሩን ይገባል።። እቅዱ እንዲከሽፍ ስለማንፈልግ አቅማችን በፈቀደ ልንታደገው እየሞከርን ነው። »

የኪቤራ ተነሽ ነዋሪዎች ሊቀመንበር ዴቪድ ንጊግ እቅዱ ከመነሾው መልካም ቢሆንም በውሳኔ አሰጣጡ ተሳታፊ እንዳልነበሩ ይተቻሉ።

«በመንደሩ ነዋሪዎች፤ባለድርሻ አካላትና በመንግስት መካከል በቂ ምክክር አልተደረገም። መንግስት ሳያማክረን በራሱ እየሰራ ነው። ይህ እጅጉን ያሳስበናል።»

አሁን ወደጊዜያዊ መቆያ ለተዘዋወሩ ተከራዮች ይህ እቅድ ከሽፏል። አከራይ ለነበሩት ሃና ዋጂሩ ግን ነገሩ ሁሉ ከዚህ ይለያል።
«አከራይ ነበርኩ። የመልሶ ማልማቱ እቅድ ሲጀመር ቤቲን አፍርሼ ወደዚህ መጣሁ። ሁሉም ነገር ርካሽ ነው። መንግስት ሃብታሞች እንዳልሆንን አይቶ ህይወታችን እንዲለወጥ ይፈልጋል።»ሃና ዋጂሩ ህይወታቸው መሻሻሉንና አሁን በአዲሱ የቤቶች ልማት እቅድ ላይ ተቃውሞ የሚያሳዩት ሰዎች የመንግስትን ጥረት ለማድነቅ እንዳልቻሉ ይናገራሉ።

በዛጉ ቆርቆሮዎቿ እና የጭቃ ግድግዳ የመኖሪያ ቤቶቿ የምትታወቀው የጎስቋሎች መንደር አሁን አዲስ መልክ እያበጀች ነው። በኪቤራ ከሶዌቶ አቅራቢያ ቀድሞ በጎስቋላዋ መንደር ይኖሩ የነበሩ ከ600 በላይ ቤተሰቦች የሚኖሩባቸው ዘመናዊ ቤቶች ይገኛሉ። ይህ ኪቤራን መልሶ የመገንባት እቅድ በኬንያ መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመኖሪያ ቤት ልማት በጋራ የሚሰራ ነው። አቅዱ የኬንያ መንግስት ከተቋሙ ጋር በጎርጎሮሳዊው 2003 የመግባቢያ ሰነድ ከተፈራረሙ በኋላ ነበር የተጀመረው። እቅዱ የመኖሪያ ቤቶችን፤የመሰረተልማትንና አስፈላጊ ግልጋሎቶችን የማሳደግ በአጠቃላይም በአነስተኛ የመኖሪያ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን አኗኗር የማሻሻል አላማ ያነገበ ነው።

የከተሞች ትብብር ወይም ሲቲስ አሊያንስ ከተባለ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የዓለም ባንክ የጋር ትብብር በተገኘ 250 ሺህ ዶላር በጎርጎሮሳዊው 2009 የተጀመረው እቅድ 600 ቤተሰቦችን ከአካባቢው በማንሳት ነበር የተጀመረው። አሁን በነ ማማ ሳቤቲ ኦምባሶ ቅሬታ የሚቀርብበት የእቅዱ ሁለተኛ ዙር ሲሆን 600 ቤተሰቦችን ወደ አዳዲሶቹ ቤተሰቦች ማዛወር ነበረበት። ይህም ለሚቀጥለው ዙር የኪቤራ ተነሺዎች ጊዜያዊ መቆያ ለማበጀት ሲባል የሚደረግ ነው።
ከስድስት አመታት በኋላ ቤቶቹ ተዘንግተዋል። የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች በሚጣልባቸው ቆሻሻዎች ተደፍነዋል። አሁን ማንም ሃላፊነት አይሰማውም። እቅዱን የጀመረው መንግስትን ጨምሮ።

በአፍሪቃ ትልቁ የጎስቋሎች መንደር እንደሆነ የሚነገርለትና ከ100 መቶ አመታት በፊት የተመሰረተው የኪቤራ መንደር ከናይሮቢ ነዋሪዎች አንድ አምስተኛው ማለትም አንድ ሚሊዮን ያህሉ ይገኙበታል። የንጽህና ጉድለት፤የቆሻሻ ክምርና የተደፈኑ የቆሻሻ ማስወገጃዎች የመንደሩ መገለጫዎች ናቸው። ከ600 በላይ መንግስታዊ ያልሆኑ ማህበረሰባዊ ድርጅቶች የኪቤራ ነዋሪዎችን ህይወት የማሻሻል አላማ ሰንቀው በመንደሩ ከትመዋል። ድህነትን ለመቅረፍ የቴክኖሎጂ ልማት እቅዶች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው። አሁን በዚህ መንደር ቡና እየጠጡ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት ይቻላል።
ዘ ሂዩማን ኒድስ እቅድ (The Human Needs Project) በኪቤራ ለሚሰሩ ስራዎች አንዱ ማሳያ ነው። የንጽህና ጉድለትና የንጹህ ውሃ እጦት በተወሰነ የኪቤራ ክፍል ተቀርፏል። በንጽህና ላይ በሚሰራ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅትና ዘ ሁዩማን ኒድስ በጋራ በኪቢራ ማዕከላዊ ስፍራ ተግባራዊ የሚያደርጉት እቅድ ወደ ፊት ወደማህበረሰቡ የማሸጋገር ሃሳብ መኖሩን ዋና ሃላፊው ቴድ ኒያማ ይናገራሉ።

«ታውን ሲቲ ሴንተር የሚባለው እቅድ ሰዎች የስራ፤የትምህርት እድልና የመሳሰሉትን የሚያገኙበት ነው። ከዚህ በተጨማሪ የመገበያያ ማዕከልም ነው። እቅዱ ራሱን ችሎ እንዲንቀሳቀስ ስለምንሻ ሰዎች ተመጣጣኝ ክፍያ እናስከፍላለን። ከፍ ያለ ግልጋሎት ለሚፈልጉም እናቀርባለን። የዚህ ሁሉ ዋና አላማ ሁሉም የማህበረሰቡ አባላት ስራ እንዲያገኙና እቅዱን የራሳቸው እንዲያደርጉት ነው።»

ከአንድ አመት በፊት የኢንተርኔት ግልጋሎት ለማግኘት እርቆ ይጓዝ የነበረው ተማሪ ኢቺየንግ ኦሞሎ አሁን የየኪቢራ ታውን ሲቲ ሴንተር ደንበኛ ሆኗል።

«ዘ ሂውማን ኒድስ እቅድ በጣም ጠቃሚ እቅድ ነው። እኔ ተማሪ በመሆኔ ብዙ ጥናቶች መስራት ይጠበቅብኛል። ብዙውን ጊዜ ወደዚህ በመምጣት ጥናቴን እሰራለሁ። ወደዚህ በመምጣት የገመድ አልባ ኢንተርኔት አገልግሎት በሌሎቹ አካባቢዎች በተሻለ ዋጋ ማግኘት ይቻላል።»

በኪቤራ ታውን ሴንተር የመንደሩ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን አገር ጎብኚዎችም እውነተኛውን የድህነት መልክ ለማየት ቢመጡም ራሳቸውን በተለየ ዓለም ያገኙታል። እንደ ሌላው ዓለም ሁሉ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት የሚያገኙ ነዋሪዎችን።


አልፍሬድ ኪቲ/እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic