ከ900 በላይ ስደተኞች የጫነች መርከብ ሰጠመች | አፍሪቃ | DW | 20.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ከ900 በላይ ስደተኞች የጫነች መርከብ ሰጠመች

ከሊቢያ ወደብ ተነስታ የሜድትራኒያንን ባህር በማቋረጥ ወደ ጣሊያን በማምራት ላይ የነበረች መርከብ በመስጠሟ ከ900 ሰዎች በላይ ሳይሞቱ አልቀረም። በመርከቧ ከተሳፈሩ ሰዎች መካከል 28 ስደተኞች ብቻ ተርፈዋል።

ስደተኞች የጫነች መርከብ በሜድትራኒያን ባህር በመስጠሟ ከ900 በላይ ስደተኞች ሳይሞቱ አልቀረም። ሰኞ እኩለ ለሊት የመስጠም አደጋ ከደረሰባት መርከብ ተሳፋሪዎች መካከል በህይወት የተረፉት 28 ብቻ ሲሆኑ እስካሁን የ24 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል። 20 ሜትር እርዝመት ያላት መርከብ የተገለበጠችው በሊቢያ የባህር ክልል ውስጥ ነው ተብሏል። የጣሊያንና የማልታ የነፍስ አድን ሰራተኞች ከ100-150 ሰዎች የጫኑ ሁለት ጀልባዎች ለመታደግ በጥረት ላይ መሆናቸው ሬውተርስ ዘግቧል። የአውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሃላፊ ፌዴሪካ ሞግሄሪኒ አባል አገራት ለአሳሳቢው ችግር አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጡ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። የጣሊያን የባህር ጠባቂዎችና የነፍስ አድን ሰራተኞች ዛሬም ፍለጋ ላይ ናቸው ተብሏል።

በጣሊያን እና ስዊዘርላንድ በመዘዋወር ለስደተኞቹ ትኩረት እንዲሰጥ የሚወተውቱት ዘ ኤጀንሲ አበሻ (THE AGENCY ABESHA) የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ሃላፊ አባ ሙሴ ዘርዓይ « ትልቅ እልቂት አሳዛኝ አደጋ ነው። ይሐ ግን በየ አመቱ የሚደገም ነው። አምና ወደ 3600 አካባቢ ሰው ነው የሞተው። የአውሮጳ ህብረት የስደተኞቹን ህይወት ለማዳን ያደረገችው ጥረት የለም።» ሲሉ ይወቅሳሉ።

የአውሮጳ የውጭ እና የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች በችግሩ ላይ ለመምከር ሉክሰምበርግ በከተሙበት ወቅት ከ300 በላይ ስደተኞችን የጫነች ጀልባ በመስጠም አፋፍ ላይ እንደምትገኝ አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አስታውቋል። በጀልባዋ ላይ የተሳፈረ ግለሰብ ጀልባዋ በመስጠም ሂደት ላይ መሆኗንና እስካሁን 20 ሰዎች መሞታቸውን በስልክ ድርጅቱ አስታውቋል።

አባ ሙሴ ዘርዓይ ከሊቢያ ወደ አውሮጳ የሚጎርፉ ስደተኞች ቁጥር በመጪዎቹ ወራት ሊጨምር እንደሚችል እርግጠኛ ናቸው።

«ካሁን ጀምሮ እስከ መስከረም ጥቅምት እየባሰ እንጂ እየቀነሰ አይሄድም።

የጀርመኗ መራሒተ-መንግስት አንጌላ መርክል ስደተኞች ለአውሮጳ የማይገባትን ክፍያ ከፍለዋል ሲሉ ተናግረዋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የአውሮጳ አገራት ስደተኞቹን ለመታደግ የባህር ላይ ነፍስ አድን ስራን ሊያጠናክሩ ይገባል ሲሉ ይሞግታሉ። የማልታው ጠቅላይ ሚኒስትር ጆሴፍ ሙስካት በጦርነት የፈራረሰችው ሊቢያ ችግር ለመፍታት የአውሮጳ አገራት ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ማለታቸውን ኤ.ኤፍ.ፒ. የዜና ወኪል ዘግቧል።

በዚህ አመት 31,500 ስደተኞች ከሰሜን አፍሪቃ በመነሳት የሜድትራኒያን ባህር አቋርጠው አውሮጳ መድረሳቸውን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አስታውቋል። በድርጅቱ መረጃ መሰረት በዚሁ አመት በተደረጉ ጉዞዎች ከ1000በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ 13,500 ስደተኞች በነፍስ አድን ሰራተኞች ተርፈዋል።

ኢጣልያ ማሬ ኖስትሩም ተብሎ የሚጠራውን የባህር ላይ የነፍስ አድን ተልዕኮ በመሰረዟ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ከፍተኛ ትችት ይሰነዘራል።

እሸቴ በቀለ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic