ከ700 በላይ ስደተኞች ሳይሰጥሙ አልቀረም | ዓለም | DW | 29.05.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ከ700 በላይ ስደተኞች ሳይሰጥሙ አልቀረም

ባለፉት ጥቂት ቀናት በሜድትራኒያን ባህር ላይ በተከሰቱ የጀልባ መስጠም አደጋዎች ከ700 በላይ ስደተኞች ሳይሞቱ እንዳልቀረ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት አስታወቀ።

በሦስት ቀናት በተከሰቱት የጀልባ አደጋዎች የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከጎርጎሮሳዊው ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. በኋላ ከፍተኛው ነው ተብሏል። ባለፈው ረቡዕ ከሊቢያ ባህር ዳር አቅራቢያ ላይ በሰጠመ የሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ጀልባ ላይ የነበሩ 100 ሰዎች እስካሁን የደረሱበት እንደማይታወቅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር (UNHCR) ቃል አቀባይ ካርሎታ ሳሚ ተናግረዋል። ከምዕራባዊ ሊቢያ የሳብራታ ወደብ የተነሳ ሌላ ጀልባም ሐሙስ ዕለት በመስጠሙ ከ550 በላይ ሰዎች እጣ ፈንታም እንደማይታወቅ ካርሎታ ሳሚ ጨምረው ገልጠዋል።

አደጋውን የተመለከቱ ስደተኞች ጀልባው ከመገልበጡ በፊት 670 ስደተኞችን ጭኖ፥ ሞተር ስለሌለው በሌላ በስደተኞች በተጨናነቀ ጀልባ ይጎተት እንደነበር ለተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት መናገራቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። ተጎታቹ ጀልባ ሲገለበጥ ሞተሩ ወደሚሠራው ጀልባ መድረስ የቻሉት 25 ሰዎች ብቻ ናቸው። ሌሎች 79 ሰዎች በዓለም አቀፍ የባሕር ጠረፍ ተቆጣጣሪ ጀልባዎች በባሕር ከመስጠም ተርፈዋል። የ15 ስደተኞች አስክሬኖች ተገኝተዋል። ጀልባውን ሲቀዝፍ የነበረው የ28 ዓመት ሱዳናዊ ወጣት በስደተኞች ጥቆማ በቁጥጥር ስር ውሏል።

በዕለተ አርብ በተፈጠረ ሌላ የጀልባ መስጠም አደጋ 135 ሰዎች በሕይወት ሲተርፉ 45 አስክሬኖች መገኘታቸውንና ሌሎች ቁጥራቸው የማይታወቅ ስደተኞች ደብዛቸው መጥፋቱን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት ቃል አቀባይ ካርሎታ ሳሚ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ