ከ2000 በላይ የማደጎ ህጻናት አድራሻቸዉ አልታወቀም ተባለ | ኢትዮጵያ | DW | 06.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ከ2000 በላይ የማደጎ ህጻናት አድራሻቸዉ አልታወቀም ተባለ

 በኢትዮጵያ ከ 2007 ዓ.ም በፊት  በማደጎ ወደ ዉጭ ሀገራት ከተላኩ ህጻናት መካከል ከ 2000 በላይ የሚሆኑት አድራሻቸዉ እንደማይታወቅ ተገለጠ። ይህ የተገለጸዉ  ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሞኑን የስድስት ወራት ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት ነዉ። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:19

«የ175ቱ ህፃናት ወላጆቻቸዉ አቤቱታ አቅርበዋል።»


የሴቶችና የህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈዉ ኃሙስ ጥር 24 ቀን 2010 ዓ.ም ለፓርላማ አባላት ባቀረበዉ ሪፖርት እንዳስታወቀዉ እስካሁን በማደጎ ወደ ተለያዩ ሐገራት የተላኩ ህፃናትን በሚመለከት የመረጃ አያያዝ ችግር እንደነበር አመልክቷል። ይህንን ችግር ለመፍታት መስሪያ ቤቱ ባለፉት ስድስት ወራት አካሄድኩት ባለዉ መረጃ የማሰባሰብ ስራ ከ5000 በላይ ፋይሎችን  በዘመናዊ መንገድ ማስቀመጥ መቻሉን አመልክቷል። ይሁን እንጅ በጎርጎሮሳዊዉ 2014/15 ለዉጭ ሀገር አሳዳጊወች የተሰጡ 2273 ህጻናት የትና በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በዉል እንደማይታወቅ በሪፖርቱ ተገልጿል። ከእነዚህም ዉስጥ የ175ቱ ህፃናት ወላጆች ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አቤቱታ ማቅረባቸዉ ተጠቁሟል።
የህጻናቱን ደህንነት ለመጠበቅ የተሟላ መረጃ አያያዝ ወሳኝ ቢሆንም ልጆቹ ወደ ዉጭ ሀገር መሄዳቸዉ ላይ እንጅ ከሄዱ በኋላ ስለሚያጋጥማቸዉ ችግር ብዙም ትኩረት ባለመሰጠቱ የመረጃ ክፍተት መፈጠሩን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ማሞ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ይህንን ስራ ይሰራ የነበረዉ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መሆኑን ጠቅሰዉ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር በአዋጅ ከተቋቋመ ከ2003 ዓ.ም ወዲህ ፋይሎቹን ለማደራጀት ሙከራ ቢደረግም ተከታታይነት ያለዉ ስራ ባለመሰራቱ ችግሩ መከሰቱን ተናግረዋል ። 
የህጻናቱን ጉዳይ በተለይ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መስሪያ ቤቱ አስተያየት እንዲሰጥባቸዉ የተደረጉ

Madonna Malawi Adoption

ና በዚህም መሰረት ወደ ዉጭ የተላኩ ልጆች ፋይሎችን በተደራጀ ሁኔታ መያዝ የተጀመረዉ ከ2007 ዓ.ም ወዲህ መሆኑንም የሚናገሩት ኃላፊዉ የመረጃ አያያዙን ዘመናዊ ለማድረግ በአሁኑ ወቅት መስሪያ ቤቱ ባለሙያ ቀጥሮ እያሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
ይሁን እንጅ በዚህ የመረጃ አሰባሰብ ስራ ላይም ቢሆን ልጆቹ የተላኩበት መንገድ ግልፅ መረጃ ያልሰፈረበት በመሆኑ ብዙ ችግር አጋጥሞናል ይላሉ።ያም ሆኖ ግን የ ሁለት ሺህ አይደለም የአንድ ህፃን አድራሻም ቢሆን መጥፋት ስለሌለበት ልጆቹን የማፈላለግ ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ሀላፊዉ ይገልፃሉ።
የዉጭ ማደጎን የሚከለክለዉ የሀገሪቱ ህግ ከወጣ ወዲህ በቀረበዉ በዚህ የመጀመሪያ ሪፖርት፣ ተቋማትና ግለሰቦች ወላጅ አልቫና ችግረኛ ልጆችን እንዲያሳድጉ ለማድረግ የሀገር ሽማግሌወችና የሀይማኖት መሪዎችን ያካተተ ስራ እየተሰራ መሆኑ ተመልክቷል።  በዚህም ወደ 1500 የሚጠጉ ህጻናት በሀገር ዉስጥ በሚገኙ ተቋማት እንዲጠበቁ መደረጉንና ወደ 500 የሚሆኑት ደግሞ ኢትዮጵያዉያን አሳዳጊዎች ማግኜታቸዉ ተገልጿል።
ከዚህ በፊት በማደጎ ወደ ዉጭ የተላኩ ልጆችን ደህንነት የሚከታተል ቡድንም በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደረጃ መቋቋሙን ሀላፊዉ ጨምረዉ አስረድተዋል።
ከ 5 ዓመት በፊት በዩኤስ አሜሪካ ሃና የተባለች የ13 ዓመት ታዳጊ ባልታወቀ ምክንያት ከሞተችና አሳዳጊወቿም ለእስር ከተዳረጉ ወዲህ የዉጭ ሀገር የማደጎ ሁኔታ አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል።በቅርቡም የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን የዉጭ ሀገር ማደጎ የሚከለክል ህግ ማዉጣቱ ይታወቃል።

ፀሐይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic