ከ 500 በላይ ሰዎች ምዕራብ ጉጂ ዞን በቁጥጥር ስር ዋሉ | ኢትዮጵያ | DW | 22.06.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ከ 500 በላይ ሰዎች ምዕራብ ጉጂ ዞን በቁጥጥር ስር ዋሉ

የምዕራብ ጉጂ ዞን መስተዳድር የህብረተሰቡን ሰላም እያወኩ ነው ያላቸውን ከ500 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር አዋለ።በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል አንድ መቶ አስሩ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር ስም የተደራጁ ታጣቂዎች መሆናቸውን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ገልፀዋል። የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በበኩሉ በአሁኑ ወቅት ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ሰራዊት የለም ብሏል።

የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ ከዶቼ ቨለ ( DW ) ጋር ባደረጉት ቃል ምልልስ እንዳሉት ታጣቂዎቹና ተባባሪዎቻቸው ሰሞኑን በቁጥጥር ስር የዋሉት የኦሮሚያ ልዩ ሀይል ከአገር መከላከያ ሰራዊትና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ባደረጉት አሰሳ ነው። 
ግለሰቦቹና ቡድኖቹ በህዝቡና በጸጥታ አባላቱ ትብብር የተያዙት በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎችና ቀበሌያት ውስጥ በመዘዋወር በህብረተሰቡ ላይ የተለያዩ ጥቃቶችን በማድረሳቸው መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል። 

በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል አንድ መቶ አስሩ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር ስም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ታጣቂ ቡድኑን በተለያዩ መንገዶች ሲደግፉ የተደረሰባቸው መሆናቸውን ነው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ የጠቀሱት ። 
ታጣቂዎቹ በምዕራብ ጉጂ ዞን ነዋሪዎችንና በአጎራብች ድንበሮች ላይ በሚገኙ የአማሮና የቡርጂ ማህበረሰብ አባላት ላይ የግድያ ፣ የዘርፋ እና የአስገድዶ መድፈር ድርጊቶችን ሲፈድሙ መቆየታቸውን ዋና አስተዳዳሪው አስታውሰዋል ። 

Äthiopien West Guji Abera Buno

የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ


ከተያዙት መካከል የወንጀል ድርጊቶችን የፈጸሙት ለህግ የሚቀርቡ ሲሆን ሌሎች ዝቅተኛ ተሳትፎ ያላቸው ግን የታድህሶ ስልጠና ወስደው ወደ ህብረተሰቡ የሚቀላቀሉ ይሆናል ብለዋል። 
በአሁኑ ወቅትም ታጣቂዎቹን ከአካባቢው ጠራርጎ ለማስወጣትና የዞኑን ሰላም ለማረጋገጥ ሁጡራ የሚል ዘመቻ ተከፍቶ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝም አቶ አበራ ቡኖ አመልክተዋል። 

የምዕራብ ጉጂ ዞን መስተዳድር ያዝኳቸው ባላቸው ታጣቂዎች ዙሪያ አስከአሁን በኦሮሞ ነፃነት ግንባር በኩል የተሰጠ መግለጫም ሆነ ማስተባበያ የለም ። ዶይቸ ቬለ ( DW ) በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ ዳባ ኦነግ በአሁኑ ወቅት ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ሰራዊት የለውም ብለዋል። 

የምዕራብ ጉጂ ዞንና በአጎራባች የአማሮና የቡርጂ አካባቢዎች ታጣቂዎች በተደጋጋሚ በሚፈፅሟቸው የደፈጣ ጥቃቶች በርካቶች ለሞት ፣ ለአካል ጉዳትና ለመፈናቀል መዳረጋቸው ይታወቃል ። በዚህም ምክንያት የኦሮሚያ ክልልና የፌደራሉ መንግስት ሰላማዊ ዜጎችን ከታጣቂዎች ጥቃት ለመጠበቅ ዳተኝነት አሳይተዋል የሚሉ ተደጋጋሚ ትችቶች እየቀረበባቸው ይገኛል። 

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ልደት አበበ