ከ ማውዘር (መውዜር) እስከ «G 36- «ሄክለር» ዝነኛው ጠብመንጃና እክሉ? | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 13.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ከ ማውዘር (መውዜር) እስከ «G 36- «ሄክለር» ዝነኛው ጠብመንጃና እክሉ?

«በጀርመን ሀገር የተሠራ -Made in Germany » ሲባል ፣ በዛ ያሉ፣ ከመድኃኒት እስከ አውቶሞቢል አያሌ የኢንዱስትሪ ምርቶች ትዝ ሊሉን ይችላሉ። የጀርመን የኢንዱስትሪ ውጤቶች በዓለም ዙሪያ በጥራታቸው ማለፊያ ስም እንዳላቸው የታወቀ ነው።

default

የጦር መሣሪያዎቿ ጭምር! ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ራሱ የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የሚያነግበው ጠብመንጃ ፣ ታዋቂው G-36 በጥቂቱም ቢሆን እክል አለው ተብሎ ሥራ ላይ እንዳይውል ውሳኔ እስከማሰልፍ ተድርሷል። ከዚህ ውሳኔ ያደረሰው ሰበብ 4 ዓመት ሆኖታል። እ ጎ አ በጸደይ ፤ በጎርጎሪዮሳዊው በዓለ ሥቅለት፣ ኩንዱዝ ፤ አፍጋኒስታን ውስጥ፤ በዓለም አቀፉ የአፍጋኒስትን አረጋጊ ኃይል ማዕከል አቅራቢያ ፤ ታሊባኖች 32 የጀርመንን አየር ወለድ ወታደሮች ፍጹም ባልጠበቁት ሁኔታ ዙሪያቸውን ይከቡና መግቢያ -መውጫ ያሳጧቸዋል። ምርጫ አልነበረም ሽንጥ ገትሮ ከመዋጋት በስተቀር! 9 ሰዓት የፈጀ ውጊያ ተካሄደ! ምርጡ ጠብመንጃ ፣ G- 36 ከመጠን በላይ ጋለ! የአየር ወለድ ወታደሮቹ ፤ የነበራቸው አማራጭ ማፈግፈግ ነበር። ወደ ኩንዱዝ ሲመለሱ፤ አንድ ብረተ ለበስ ተሽከርካሪ በመንድ ዳር በተቀበረ ቦታ ላይ ሲከንፍ በፈንጂ ይነጉድና 3 ጀርመናውያን ወታደሮች ይሞታሉ። ታዲያ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ነበረ Heckler & Koch ኩባንያ የሚሠራው እጅግ ዘመናዊ የተሰኘው ጠብመንጃ እስከምን ድረስ አስተማማኝ ነው? የሚል ጥያቄ ያስሰነዘረው!

G-36፣ 890 ሚሊሜትር ቁመትና 2,9 ኪሎ ግራም ክብደት ያለው ጠብመንጃ ነው። የ G-3 ተከታይ የሆነው G-36 ፤ ከቀዝቃዛው ጦርነት ፍጻሜ በኋላ፣ እ ጎ አ በ 1995 ዓ ም አዲስ ጠብመንጃ ሠርቶ እንዲያቀርብ ፈቃድ ያገኘው ሄክለርና

Sturmgewehr G36 von Heckler & Koch

ኮህ ኩባንያ፤ እ ጎ አ ታኅሳስ ወር መግቢያ 1997 አዲሱን ዘመናዊ ጠብመንጃ ለጀርመን መከላከያ ሠራዊት አቀረበ።

የጀርመን የሀገር መከላከያ ጦር ሠራዊት ብቻ ሳይሆን፤ ከእስፓኝ እስከ ብራዚልና ኢንዶኔሺያ የብሪታንያ ልዩ የአየር ኃይል ሠራዊት ፤ የፈረንሳይ ፖሊስ ፣ ቤልጅግ ፤ አውስትሬሊያ ፣ ጭምር ባጠቃላይ ከ 17 የማያንሱ ሃገራት ጦር ሠራዊታቸውን ያስታጠቁት በ ዚህ ሲይዙት ቀለል በሚለው እጅግ ዘመናዊ ጠብመንጃ ነው።

ኢትዮጵያም ፤ G -36 ባይሆንም G -3 የጀርመን ጠብመንጃ አላት። ይሁንና G-36 እንከን አለበት በመባሉ፤ የጀርመን መከላከያ ሠራዊት የታጠቀው 170,000 ያህል G-36 ጠብመንጃ ተመላሽ እንዲሆን ከጥቂት ሳምንታት በፊት የመከላከያ ሚንስትር ወ/ሮ ዑርዙላ ፎን ዴር ላየን መወሰናቸው ነው የተገለጠው።

ዘመናዊ የተባለው ጠብመንጃ ምንድን ነው የተገኘበት እንከን? እንደተባለው ከሆነ ፤ G-36 ፣ «በውጭው ኃይለኛ የአየር ሙቀት ወይም በመሣሪያው የተኩስ ግለት ሳቢያ ፤ ወይም በሁለቱም ምክንያቶች፣ ዒላማውን ፤ መቶ በመቶ አስተካክሎ አይመታም »። የመከላከያ ሚንስቴሩ እንደገለጠው፤ የጠብመንጃው አካል በብረትና በሌሎች ሰው ሠራሽ ቁሳቁሶች ተገጣጥሞ የተሠራ በመሆኑ በ 23 «ዲግሬ ሴልሲየስ » ለውጥ ስለሚያሳይ፤ የሚተኮሰውን ጥይት በቀጥታ ወደ ዒላማው አያስፈነጥርም። G-36፤ በንጽጽር ከ ፈረንሳዩ FAMAS F1 ወይም ከአሜሪካው Colt AR-15 እጅግ ቀለል ያለ ነው።

በሄክለርና ኮህ የጠብመንጃ መሥሪያ ኢንዱስትሪ ፤ ኤፍ ጄ ዩንግ የተባሉት የጠብመንጃ ሥራ ባለሙያ---- ስለተጠቀሰው ዘመናዊ ጠብመንጃ እንዲህ ነበረ ያሉት።

«G-36 ከ G-3 ቀለል ያለና ዓላማን አስተካክሎ በመምታትም የላቀ ነው። ወታደሮችም መሣሪያውን ሲጨብጡት ደስ የሚያሰኝ ስሜት ነው የሚፈጥርላቸው። ወጣት ተኳሾችም ወደፊት በዚህ mm,ሣሪያ መጠቀማቸው የማይቀር ነው። ወደውጭ በይፋ የሚሸጠው ፤ እ ጎ አ በ 1998 ዓ ም፤ በተሰጠው ፈቃድ መሠረት ለ NATO አባል ሃገራት ሲሆን፤ እስፓኝ በዚህ ግንባር ቀደም ተጠቃሚ ናት፤ ሜክሲኮም ይህን መሣሪያ ለማምረት ፈቀድ መጠየቋ ታውቋል።በመካከለኛው ምሥራቅም አንድ ሀገር G-36 ለማምረት ፈቃድ አለው። የጀርመን ፌደራል መንግሥት ግን ስለዚያ ሀገር ምንነት መግለጽ አልፈለገም።»

NO FLASH Waffen von Heckler & Koch HK G36

ስለ G-36 የሄክለርና ኮህ ኩባንያ ምርት ስለሆነው ጠብመንጃ ከአስተዳዳሪዎች ማርቲን ሌምፐርለ እንዲህ ብለዋል።

የመከላከያ ቴክኒክ እንደድሮው ፤ ዛሬም ለብዙ የአካባቢው ኑዋሪዎች የሥራ ዕድል ያስገኘ ነው። የጀርመንን ጦር ሠራዊት ወደአፍጋኒስትንም ሆነ የትም ዱላ ይዞ እንዲዘምት አናደርግም።»

ያም ሆነ ይህ፤ ምርጥ ከተባለው ጠብመንጃ የሚጠበቀው ፣ አነጣጥረው ሲተኩሱበት ዒላማውን መምታቱ በመሆኑ፤ ባለፉት ወራት የተለያዩ ፍተሻዎች ተካሂደዋል። ሁለቱ ሙከራዎች ወይም ፍተሻዎች የተመሩት በጀርመን የመከላከያ ጦር ሠራዊት ሲሆን ፤ አንደኛው በአንድ, የግል ድርጅት ነው። ሁሉንም ያስተባበሩት እርግጥ የጀርመን መከላከያ ሚንስትር ወ/ሮ ዑርዙላ ፎን ዴር ላየን ናቸው። እናም ፍተሻውን የተከታተሉት ጠበብት፤ የደረሱበት ውጤት ብዙዎችን ለመምከር-ለመዝከር የጋበዘ ነበር። የጀርመን ጦር ሠራዊት የሚጠቀምበት G-36 ፣ 30 ጥይት ጎራሽ ሲሆን፤ 100 ጥይት የሚያቀባብል ድስት መሰል አካል ያለው ጠብመንጃም አለ ፤ ይህም ቢሆን 80 ጥይቶችን ብቻ ነው ማቀባበል የሚችለው። አለበለዚያ የብረት እርስ በርስ መፋጨትን ያስከትልና ዒላማውን መምታት ይሳነዋል። 40, 20, 10, እና 2 ጥይት ብቻ የሚተኮስባቸው ጠብመንጃዎችም አሉ።

በ 200 ሜትር ርቀት ፣ የ 50 ሜትር ማጋደል ፤ በ 500 ሜትር ርቀት ደግሞ የ 6ሜትር ማፈንገጥም ሆነ ዒላማ የመሳት ሁኔታ ያጋጥማል ።

የመከላከያ ሚንስትር ፎን ዴር ላየን፤ «G-36 አሁን ባለበት ሁኔታ ፤ በጀርመን ጦር ሠራዊት ውስጥ ተቀባይነት አይኖረውም፤ በአሠራሩ ስህተት አለበት፤ ተፈላጊ አይደለም ፣ ምናልባትም ሕገ -ወጥ ነው» ማለታቸው ተጠቅሷል። የ G-36 ጠብመንጃ ሠሪ ኩባንያ «ሄክለር እና ኮሕ» ግን የሚንስትሯን ወቀሳ አልተቀበለውም፤ እንዲያውም ስሕተቱ ያለው በሰው ሠራሹ ቁሳቁስ ሳቢያ ሳይሆን፤ በብረቱ ክፍል ነው ፤ አደገኛ ግለት እንዲያጋጥመው የሚያደርገውም ብረቱ ነው ብሏል። ይኸው ኩባንያ ፣ የጀርመን ፤ ብሔራዊ ጦር ሠራዊት በሰፊው የታጠቀበትን ጦር መሣሪያ በማቅረብ ወደር የሌለው ሲሆን ፤ ጀርመን በዓለም አቀፍ ደረጃ በጦር መሣሪያ ሽያጭ የ 3ኛነቱን ደረጃ እንድትይዝ ማብቃቱንም በኩራት ይናገራል።

Heinz Schulte የተባሉት የመከላከያና የጦር መሣሪያ ጉዳይ ባለሙያ ግን DW ባደረገላቸው ቃለ ምልልስ «ሄክለር እና ኮህ » ኩባንያ የተለያዩ የሥራ ዘርፎች ስላሉት በዚያ በኩል ራሱ ኩባንያው ሥራ በዝቶበት ካልሆነ በስተቀር፤ G-36

ጠብመንጃ አንዳች እንከን የለበትም ፤ የቴክኒክ እክል ተገኝቶበታል መባሉም መሠረተቢስ ነው ነው ያሉት። ሹልተ እንደሚገምቱት ከሆነ የጀርመን የመከላከያ ሠራዊት፣ ሄክለርና ኮህ የጦር መሣሪያ ፋብሪካ ከሚሠራቸው የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች፤ ከዚህም ከዚያም የሚያስፈልጉትን በመቀላቀል ለመጠቀም ጥረት ያደርጋል እንጂ፤ ከእነአካቴው ውሉን አያፈርስም ።

የጠብመንጃ ሥራ ያገነናት ንዑስ ከተማ ዖበርንዶርፍ፤

«ሄክለርና ኮህ» በሚል ስያሜ የተወቀው ጠብመንጃ አምራች ኩባንያ ፣ ከ 203 ዓመት በፊት የማውዘር ወንድማማች፤ ፓውልና ቪልሄልም ማውዘር ፤ እስከ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ ታዋቂ የነበረውን ማውዘር እኛ መውዜር የምንለውን ጠብመንጃ መሥራት በጀመሩባት ከተማ ፣ በባደን ቩርተምበርግ ፌደራል ክፍለ ሀገር፤ ከራይን ወንዝ ገባሪ ፣ ኔካር ወንዝ ዳር በተመሠረተችው ንዑስ ከተማ በዖበርንዶርፍ ነው የሚገኘው። ማውዘር --መውዜር እ ጎ በ 1870 -71 በጀርመንና በፈረንሳይ ጦርነት ጀርመንን ለድል ያበቃ በዚያ ዘመን እጅግ ዘመናዊ የተባለ ጠብመንጃ እንደነበረ ይነገርለታል።

ባሁኑ ዘመን ባንዳንድ የጦር ክፍሎች በክብር ተይዞ ሥራ ላይ የሚውል ቢሆንም ፤ በአሁኑ ጊዜ የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ጠብመንጃ በመሆን ማውዘርን የተካው ፤ አሁን ትንሽ እንከን ተገኘበት የተባለው G-36 ነው።

ጀርመን ፤ ጠብመንጃዋ ብቻ ሳይሆን ታንኮቿ እንዲሁም ባህር ሠርጓጅና የተለያዩ የጦር መርከቦቿም በዓለም ዙሪያ እጅግ ተፈላጊዎች ናቸው። በመሆኑም ከትናንት በስቲያ እንኳ፤ ለእሥራኤል 430 ሚሊዮን ዩውሮ የሚያወጡ ፈጣን የጦር መርከቦች ለማቅረብ ውል መፈራረሟ የሚታወስ ነው።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች