1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አቶ ኦሞት አግዋ ተከላከሉ ተባሉ

ሰኞ፣ ኅዳር 5 2009

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በዛሬው ውሎው በእነ ኦሞት አግዋ መዝገብ ከተከሰሱ ሶስት ግለሰቦች ሁለቱን በነጻ አሰናብቷል፡፡ በነጻ የተሰናበቱት አሽኔ ኦስቲን እና ጀማል ኦማር ናቸው፡፡ አቶ ኦሞት ደግሞ በመጀመሪያ የተከሰሱበት የሽብር ወንጀል ተቀይሮ በመደበኛ የወንጀል ህግ አንቀጽ እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ በይኗል፡፡

https://p.dw.com/p/2SgW3
Symbolbild Justiz Richter Gericht Richterhammer
ምስል picture-alliance/dpa/U. Deck

Ethiopian court acquits 2 defendants on Omot etal case - MP3-Stereo

በሽብር ተከስሰው ለአንድ ዓመት ከስምንት ወር በእስር ላይ የቆዩት የቀድሞው የዓለም ባንክ አስተርጓሚ ኦሞት አግዋ እና ሁለት ተከሳሾች  ዛሬ ፍርድ አግኝተዋል፡፡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ከሶስቱ ተከሳሾች ሁለቱን በነጻ ሲያሰናብት አቶ ኦሞት ከተከሰሱበት የሽብር ወንጀል ህገመንግስታዊ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመጣስ መዘጋጀት ወደሚል የወንጀል ህግ አንቀጽ ተቀይሮላቸው ተከላከሉ ተብለዋል፡፡

ከክረምት እረፍት መልስ የተሰየመው ችሎት አንደኛ ተከሳሽ አቶ ኦሞት በክሱ ላይ ፈጸሟቸው ተብለው የተጠቀሱ ጉዳዮች በማስረጃ መረጋገጡን ማስረዳቱን የተከሳሹ ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን ለዶይቸ ቨለ ተናግረዋል፡፡ 

አቃቤ ህግ አቶ ኦሞትን በሽብር ሲከስሳቸው “ከጋምቤላ ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (ጋህነን) አመራር ጋር ተገናኝተዋል፣ ገንዘብ ተቀብለዋል፣ የድርጅቱ የሀገር ውስጥ አስተባባሪ ሆነዋል፣ የሽብር ወንጀል ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል” በሚል እንደነበር አቶ አምሃ ያስታውሳሉ፡፡ በዚህም መሰረት በጸረ-ሽብር አዋጅ “በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ ስለመሳተፍ” የሚያትተው አንቀጽ ተጠቅሶ ክስ ተመስርቶባቸው ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ በዛሬው ውሎው በአቶ ኦሞት ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔ አቶ አምሃ እንዲህ ያስረዳሉ፡፡

“ፍርድ ቤቱ ያለው እነዚህን ግንኙነቶች ማድረጋቸው በቀረበው ማስረጃ ተረጋግጧል፡፡ ነገር ግን የተረጋገጠው ድርጊት ጸረ-ሽብር አዋጁ ስለሽብርተኝነት ካስቀመጠው ትርጓሜ እና ስለሽብር ወንጀል ከዘረዘራቸው ድርጊቶች ውስጥ የሚካተት አይደለም፡፡ ይልቁንም በማስረጃ የተረጋገጠው ድርጊት የሚካተተው የወንጀል ህጉን አንቀጽ 256 (ሀ) ማለትም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ወይም የሀገሪቷን አንድነት በመጣስ ሙከራ ወይም ዝግጅት ወንጀል በሚል ነው ጥፋተኛ ያላቸው፡፡”

Flash-Galerie Äthiopien Land Grab
ምስል DW/Schadomsky

አቶ ኦሞት እንዲከላከሉ የተጠቀሰባቸው አንቀጽ እስከ 15 ዓመት እስራት የሚያስቀጣ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ የአቶ ኦሞትን መከላከያ ለመስማት ለጥር 17 የቀጠረ ሲሆን አብረዋቸው የተከሰሱትን አቶ አሽኔ ኦስቲን እና ጀማል ኡመርን በነጻ አሰናብቷል፡፡ ሁለቱን ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ በምን መነሻ ነጻ እንዳላቸው እና ቀጣዩ እርምጃቸው ምን እንደሆነ አቶ አምሃ እንዲህ ያብራራሉ፡፡

“ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ አሽኔ ኦስቲን እና ጀማል [ኡመርን] በተመለከተ የቀረቡባቸው ማስረጃዎች የተነገረባቸውንም ሆነ ሌላ ወንጀል የሚያቋቁም ስላልሆነ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ ይሰናበቱ በሚል ነው ብይን የሰጠው፡፡ እኛም እንግዲክ ከዚህ በመነሳት የሁለቱ በነጻ መሰናበት በጸጋ ተቀብለን የአንደኛ ተከሳሽ ይከላከሉ የተባሉበት የህግ አንቀጽ ደግሞ የዋስትና መብት የሚያስከለክላቸው ስላልሆነ የዋስትና መብታቸው ሊፈቀድ ይገባል የሚል አቤቱታ አቅርበን በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻ ለመወሰን ለነገ ተቀጥሯል፡፡”

አቶ አሽኔ እና አቶ ጀማል ታስረው ከቆዩበት ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ዛሬ ይለቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሶስቱም ተከሳሾች በቁጥጥር ስር የዋሉት መጋቢት 2007 ዓ.ም ናይሮቢ የሚካሄድ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ጣቢያ በተገኙበት ወቅት ሲሆን ለስድስት ወር ያህል በይፋ ሳይከሰሱ በእስር ቆይተዋል፡፡

ተከሳሾቹ ወደ ናይሮቢ ሊሄዱ የነበረው ጋህነን ባዘጋጀው ስብሰባ ሊሳተፉ ነበር ሲል አቃቤ ህግ ከስሷል፡፡ ተከሳሾቹ በበኩላቸው ሊሳተፉበት የነበረው ስብሰባ በምግብ ዋስትና ላይ የሚያተኩር እና በስዊዘርላንድ የወንጌላዊት አብያተ ክርስቲያናት ስር ባለው “ብሬድ ፎር ኦል” (Bread for All) ግብረ ሰናይ ድርጅት የተዘጋጀ እንደነበር ሲከራከሩ ቆይተዋል፡፡  ዛሬ ተከላከሉ የተባሉት ኦሞት እንደ ሌሎቹ ተከሳሾች ሁሉ የጋምቤላ ተወላጅ ሲሆኑ “የዓለም ባንክ በክልሉ የሚደግፈው ፕሮግራም ሰዎችን ለማፈናቀል ውሏል በሚል ለተቋቋመው አጣሪ ቡድን” በአስተርጓሚነት አገልግለዋል፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ