ከጥምቀት አርሞኒካ እስከ ሰሞነኛው «ድርድር» | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 20.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ከጥምቀት አርሞኒካ እስከ ሰሞነኛው «ድርድር»

የጥምቀት በዓል አከባበርን በተመለከተ የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል። በተጨማሪምም ኢህአዴግ እና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር አደርገዋለሁ ያለውን ድርድር በተመለከተም ቅኝት ይኖረናል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 07:47

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዘንድሮ የጥምቀት በዓል ኢትዮጵያ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ ወዲህ  አደባባይ በመታደም የተከበረ በመሆኑ በርካታ ምዕመናን ስጋታቸውን በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ሲገልጡ ተስተውለዋል። ከጥምቀት ዋዜማ ከከተራው አንስቶ ወጣቶች አደባባዮችን እያጸዱ ለታቦታት ተሸካሚ ካህናት መሄጃ ረዣዥም ቀይ ምንጣፎች በመዘርጋት ሲታትሩም ታይተዋል። ሙሉ ወታደራዊ ትጥቅ ያነገቡ ወታደሮች ምስልም ከበዓሉ ታዳሚዎች ጋር ተቀይጦ ታይቷል። 

በስደት ላይ የሚገኘው የቀድሞው የአዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ «መልካም በዓል!» ሲል በተንደረደረበት የፌስቡክ መልእክቱ ስለበዓሉ፤ «ሥነ መለኮት፣ ባህል፣ ታሪክ እና ሥነ ጥበብ በየፈርጁ በአንድ ሰምረው የሚታዩበት ድንቁ ሀብት፤ ጥምቀት። የፈለከውን መዘህ መደመም፣ መመርመር፣ ከፈለክም መሳተፍ ትችላለህ። ኢትዮጵያችን ሌሎችም ብዙ መሰል ሀብቶች አሏት» ብሏል።

ሔዋን ዘ ስምዖን በትዊተር ገጿ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ ስለነበረው አከባበር «ጥምቀት በጃንሜዳ» ስትል ጽፋለች። «ጥምቀት ጃንሜዳ። ለማንኛውም የሰሞኑ ፌደራል ፖሊስ ትዕዛዝ በጥፊ መምታት ነው። ስንቱን ሲያላትሙ እንደዋሉ» ስትል ሔዋን በጃንሜዳ የተሰባሰቡ የበዓሉ ታዳሚያን ፎቶ አያይዛ አቅርባለች። በቃ አለ ሰው ደግሞ በትዊተር «መልካም ጥምቀት ለሁሉም! በኢትዮጵያዊነት!» ሲል አጠር ባለ ሐረግ መልእክቱን አስተላልፏል።

የጥምቀት በዓል ውሎ ምን ይመስል እንደነበር ተከታታዮቻችን እንዲያካፍሉን በሚል በዶይቸ ቬለ የአማርኛ ቋንቋ የፌስቡክ ገጻችን ላይ ጠይቀን ነበር። ከፌስቡክ ተከታታዮቻችን የተሰጡ የተወሰኑ አስተያየቶችንም አሰባስበናል። 

ሠላም ዴቭ በፌስ ቡክ አስተያየቷ ማዘኗን ገልጣለች። «ጎንደር በቀዘቀዘ መንፈስ፤ በአጋዚዎችና ወታደሮች ከአነስተኛ ሕጻናትና ሽማግሌዎች ጋር ነዉ የተከበረዉ። ባጭሩ የሀብታም ቀብር ላይ ከሚገኘዉ ሠዉ ጋር ይነፃፀራል። ያሳዝናል»  የሚል አስተያየት ስታሰፍር ዳዊት ተስፋዬ ደግሞ ፦ «እዚህ (መቀሌ) ላይ የበዓሉ አከባበር በጣም ደማቅና ልዩ ነው» ብሏል፡፡ «የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳ ፀባ በተባለ ቦታ ላይ ተሰብስበው በዓሉን አክብረውታል---ተጠምቀዋልም፡፡ ለኢትዮጵያውያን ኩራት፤ መልካም በዓል!» ሲልም ምኞቱን አክሏል።

በርናቫስ ጉዛራ የተባለ ሌላ የፌስቡክ ተከታታያችን፤ በጥምቀት በዓል ወቅት ከተለመዱ ክስተቶች መካከል የሎሚ ውርወራ ግራ ያጋባው ይመስላል። «ጉድ ሆንኩ» ሲል ይንደረደራል በርናቫስ ያሰፈረው የፌስቡክ መልእክት። «ሴት የምትወረውር መስላኝ ስጠብቅ ውየ ተመለስኩ።ለካስ ወንድ ኖሯል የሚወረውር» ሲል ጉድ ያደረገውን ክስተት አካፍሏል።  

የዋህ እንደ እርግብ ሁን የሚል የፌስቡክ ተጠቃሚ « አረ ጎበዝ እንድ ሎሚ 5 ብር ተገዝቶ አይወረወርም!» ሲል ጽፏል። አገኘሁ አምባቸው በበዓሉ ላይ በተለያዩ ቦታዎች በወጣቶች የሚዘወተረው አርሞኒካ የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት ጥያቄ አጭሮበታል።  «አርሞኒካ እና ጥምቀት ግን ምን?» ሲል ያጠይቃል። 
የበዓሉ አከባበርን የሚያስቃኙ የፎቶ እና የቪዲዮ ምስሎች ኢትዮጵያ ውስጥ እና ከኢትዮጵያ ውጪ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ምን ይመስል እንደነበር በከፊል አስቃኝተዋል። በተለይ ፌስቡክ ማንኛውም የፌስቡክ ተጠቃሚ የቀጥታ ቪዲዮ ሥርጭት የማከናወን ዕድል በመክፈቱ በዓሉን ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት  መመልከት ተችሏል።

ኢሕአዴግ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ሊወያይ ነው የመባሉ ዜና በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ከጥምቀት በዓል አከባበር ባሻገር በርካቶችን ያነጋገረ እና ጎላ ብሎ የወጣው ርእስ ነበር።

ወርቄ አለያም መርፌ ቁልፍ በትዊተር ገጿ ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር አደርገዋለሁ ያለውን ውይይት ከታይታ ውጪ ሌላ ትርጉም እንደሌለው ጠቁማለች። «የህወሃት እና ተቃዋሚዎች ውይይት ተብዬው ከቴአትር እና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ታይታ ውጪ የዘለለ አንዳችም ነገር የለውም» ይላል ጽሑፏ።

እሸቱ ሆማ ቄኖ በሰጠው የፌስቡክ አስተያየት በድርድሩ የታሰሩ የተቃዋሚ አባላት ከእስር ተፈትተው ሊሳተፉ ይገባል ብሏል። «እነዶክተር በየነ ጴጥሮስ ከኢህአዴግ ጋር ከመደራደራቸው በፊት በእስር የሚገኙ የትግል ጓዶቻቸው እንዲፈቱ መጠየቅ አለባቸው። የታሰሩት ተፈትተው የዋናው ድርድር አካል ሊሆኑ ይገባል። ኢህአዴግ ከምር መደራደር ከፈለገ በመጀመሪያ ያሰራቸውን ተቃዋሚዎች ከእስር ይልቀቅ። ይህ ካልሆነ እንደለመደው ከአሯሯጮቹ ጋር በር ዘግቶ ይንጫጫ። ይህ የኔ እምነት ነው» ሲል አስተያየቱን ቋጭቷል። 

የኢፍዴኃግ፣ የቅንጅት፣ የኢዴፓና የኢዴአን ፓርቲዎች በተዘጋጀዉ መድረክ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ መዘጋጀታቸዉን ማመልከታቸዉ በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ተጠቅሷል። ስለዚህ የዉይይት መድረክ እናንተስ ምን ትላላችሁ? አስተያየታችሁን አጋሩን። ብለን ላቀረብነው የመወያያ ርእስ በርካታ አስተያየቶች ደርሰውናል። 

ሕይወት ሲሳይ የሚከተለውን ጽፋለች፦ «ድንቄም ተቃዋሚዎች¡ እኔ የማይገባኝ እስከ መቼ እራሳቸውን እያታለሉና ከሕዝቡ ጋር የአይጥና ድመት ድብብቆሽ እንደሚጫወቱ ነው! በርካታ ዕድሎችን ቢያገኙም እነሱ ግን ስህተታቸውን አርመው ከሕዝብ ጋር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመታረቅ አለመቁረጣቸው ኋላ ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው ሳይታለም የተፈታ ሐቅ ነው»

ፍጹም አብርሃ ከሕይወት ጋር አይስማማም። «እንደኔ ከሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር መወያየቱ መልካም ነው እላለሁ!!! ግን መጀመሪያ የFDREን ሕገ መንግስት ማመን አለባቸው!!! ተቃዋሚ ማለት ሁሉንም መቃወም ማለት አይደለም!!! መጀመሪያ ሕገ መንግሥቱን ትቀበልና ባለህ ፖሊሲና ስትራተጂ ዙሪያ መከራከር ይቻላል!!! ስለዚህ ክርክሩና ውይይቱ እንደዚህ ከሆነ ደስ ይላል!!! ከውይይት ብዙ ነገር ይገኛልና እንዲህ ዓይነት ልምድ መቀጠል አለበት!!! ተሳዳቢዎች እንግዲህ,,,,» በማለት ጽሑፍን ሳይቋጭ በእንጥልጥል ትቶታል። 

ቴዎድሮስ ኃይሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ለድርድር የሚበቃ ተቃዋሚ እንደሌለ ይገልጣል። «እንወያይ ይላቸዋል ከዛ የልብ ትርታቸውን ያደምጣል፤ ከዛ ለያንዳንዷ የምትሆን የማጥፊያ ስልት ያበጅላቿል አለቀ» ብሏል። ደፋርሰው አይሞትም ደግሞ፦ «ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አለ እንዴ? ፓርቲ 97 ላይ ቀረ፡» ነዉ ያለዉ። 

እዮብ እዮብ «ተፎካካሪ ብላችሁ ስማቸውን የዘርዘራችኋቸው ወያኔ ለማታለያ የፈጠራቸው የውሸት ተፎካካሪ ናቸው። በትክክለኛ ተፎካካሪና ተቃዋሚዎችማ እስር ቤት ናቸው» ሲል አስተያየት ሰጥቷል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ
 

Audios and videos on the topic