ከጁፒተር ጥግ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 20.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ከጁፒተር ጥግ

አብዛኛው ክፍሏ በጋዞች ክምችት የተሞላ ነውጠኛ ፕላኔት ናት። የአቧራ ቧሂት ጀርባዋን እንደቀለበት ሸብቦ የሚጋልባት፤ መግነጢሳዊ ኃይሏ ያገኘውን ጎትቶ የሚፈጠፍጥ፦ ጁፒተር። ጸሐይ ስትፈጠር በቃኝ ብላ የተወቻቸው በርካታ ቁሶች ተግተልትለው የሰፈሩባት ግዙፏ የጋዝ ክምችት ፕላኔት፦ ጁፒተር። በ67 ጨረቃዎች ታጅባ ኅዋው ላይ ትዞራለች፤ ትዘውራለችም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:25

ንጉሥ ፕላኔት

ጠፈርተኞች የፕላኔቶች ንጉሥ ሲሉ ያሞካሿታል፦ ንጉሥ ፕላኔት።ለምዕተ ዓመታት ጁፒተር ከአድማሱ ወዲያ የምታበራ ኮከብ ነበረች፤ ለጋሊሊዮ እስኪገለጥለት ድረስ። የ17ኛው ክፍለ ዘመን ስነ-ፈለክ ሊቅ ጋሊሊዮ በጁፒተር ዙሪያ በስልት የሚሽከረከሩትን አራት ጨረቃዎች ማግኘቱ ግን እሳቤውን እስከወዲያኛው ቀይሮታል። በእርግጥም ያች በሩቅ የምታንጸባርቀዋ ኮከብ ከፕላኔቶች አንዷ፦ ሊያውም ግዙፏ ናት።

በሰአት 250,000 ኪሎ ሜትር እየከነፈች፤ ለአምስት ዓመታት ኅዋውን ሰንጥቃለች። ያለዕረፍት ለዓመታት ስትወነጨፍ ሰንብታም ሰሞኑን የጁፒተር ምኅዋር ውስጥ ገብታለች፤ ሰው አልባዋ ኅዋ ቃኚ መንኲራኲር፦ጁኖ። በብሔራዊ የበረራ ሳይንስ እና የኅዋ አስተዳደር (NASA) የተላከችው ልዩ እና እጅግ ረቂቋ መንኲራኲር ጁኖ በቅርበት የምትቃኛት ፕላኔት ጁፒተር ገጽታዋ ምን ይመስላል? በደቡብ አፍሪቃ ኖርዝ ዌስት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መምህር የኾኑት ኢትዮጵያዊው ተመራማሪ ዶክተር ጌትነት ፈለቀ ጁፒተር ከፕላኔቶች ሁሉ ቀድማ የተከሰተች ሳትሆን አትቀርም ይላሉ።

የናሳ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ፎን ቫዘን በበኩላቸው ጁፒተርን ግዙፍ የጋዝ ክምችት ሲሉ ነው የሚጠሯት። ጁፒተርን በውኃ ላይ የመንሳፈፍ ባሕሪ እንዳለው አንዳች በጋዝ የተሞላ ፊኛ (ባሉን) አርገን ልንመስላት እንችላለን ይላሉ። ከዚያ በተጨማሪም አስደናቂ ባሕሪ እንዳላትም ይናገራሉ።«ምናልባት ተጨማሪ አስደማሚ ነገሯ ጁፒተር በደመና የተዋጠች ፕላኔት መኾኗ ነው። ከዚህ ደመና ውስጥ ያለውን ነገርም መመልከት አንችልም። ጁፒተርን ከሸፈናት ደመና ስር ምን እንዳለ የምናውቀው ነገር የለም።»

ምድር ከምትገኝበት ጸሐያዊ ጭፍሮች ግዙፏ ፕላኔት ጁፒተር ከጸሐይ 484 ሚሊዮን ማይልስ ትርቃለች። ምድር ከጸሐይ ከምትርቀው አምስት እጥፍ ወዲያ ማለት ነው። እናም ኅዋ ቃኚዋ መንኲራኲር፤ ጁኖ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1610 ዓመት ጣሊያናዊው የሥነ-ፈለክ ሊቅ በግዙፍ አጉሊ መነጽር ለመጀመሪያ ጊዜ ከቃኛቸው አራት ግዙፍ ጨረቃዎች ተርታ ተሰልፋ ምኅዋሩ ላይ እየተሽከረከረች ጁፒተርን ትቃኛለች። ሳን አንቶኒዮ ቴክሳስ በሚገኘው የደቡብ ምዕራብ የምርምር ተቋም ውስጥ የጁኖ ቀዳማይ መርማሪ የኾኑት ስኮት ቦልተን 1 ቢሊዮን ዩሮ ወጪ ከተደረገባት ቃኚ መንኲራኲር የሚጠብቁት ብዙ ነው።

«እጅግ አስደናቂ ፕላኔት ናት። የጁኖ ዋነኛ ተግባር ከጁፒተር ገጽታ ሥር ያለውን መመልከት ነው። ዝቅ ብለን ተጠግተንም እውስጥ ምን እንዳለ እንመለከታለን። ፕላኔቷ እንዴት ተዋቀረች? ይኽስ ገጽታዋ ምን ያኽል ጥልቅ ነው? የሚለውን አንስተን ምሥጢሯን ለመረዳት እንጥራለን።»

ሁሉም ነገር በታቀደለት መሠረት የሚሰምር ከኾነ፤ ጁኖ በጁፒተር ምኅዋር ለአንድ ዓመት ያኽል ትሽከረከራለች። እየተሽከረከረችም መረጃዎችን ትሰበስባለች። ዛሬም ድረስ እንቆቅልሽ ለኾኑ ጥያቄዎች መልስ ትሰጣለች።ጁኖ 3,500 ኪሎ ግራም ትመዝናለች። ስፋቷ የቅርጫት ኳስ መጫወቻ ሜዳ ያኽላል። እንደ ባላ በተዘረጉት ሦስት ክንፎቿ 18,698 የጸሐይ ኃይል ማመንጫ ንጣፎች ተዘርግቶባቸዋል። በነዚህ ንጣፎችም ከጸሐይ ብርሃን 500 ዋት ኃይል ማመንጨት ትችላለች። የኃይል ምንጩም ጁኖ ላይ የተገጠሙት ዘጠኝ ልዩ መሣሪያዎች ያለ እንከን እንዲሠሩ ያግዛል። በዚህም ጁኖ በጸሐይ ኃይል የሚሠራ የመጀመሪያው ኅዋ ቃኚ መንኲራኲር አድርጓታል።

ለመኾኑ ጁኑ መረጃ ለመሰብሰብ የተላከችበት የጁፒተር ከባቢ አየር የተዋቀረው እንዴት ነው? የተዋቀረውስ ከየትኞቹ ጋዞች ነው? ጁኖ የእነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ዋነኛ ግቧ ነው። ጁኖ የጁፒተር ስበታዊ እና መግነ-ጢሳዊ ኃይል መስክን ቃኝታ ወደፊት መረጃዎችን ወደ ምድር ትልካለች። የጁፒተር ግዝፈት፤ ስበታዊ እና መግነ-ጢሳዊ ኃይሏ ተደምሮ ምድር በተወርዋሪ ጅራታም ኮከቦች እና ሰማያዊ አካላት እንዳትመታ እንደ ጋሻ ኾኖ ይከላከልላታል።

ዶክተር ጌትነት ፈለቀ ለዶክትሬት መመረቂያ ያቀረቡት ጥናታቸው የሚያተኩረው እርስ በርስ የሚሽከረከሩ ጥንድ ከዋክብት (binary stars) የሽክርክሪት ባሕሪያት ቅኝት ላይ ነው። የጁፒተር ውልደት ዛሬም ድረስ ለጠፈር ተመራማሪዎች ምሥጢር ነው። ሣይንቲስቶች ጁፒተር ምናልባትም አቧራ እና ጋዝ ከተቀየጠበት እጅግ ግዙፍ የደመና ልትሚያ በኋላ የተፈጠረች የመጀመሪያዋ ከፀሐያዊ ጭፍሮች አንዷ (ፕላኔት) ናት ብለው ያስባሉ።ጁኖ ከ20 ወራት በላይ የኅዋ ላይ ቆይታዋ የጁፒተር ምኅዋርን ለ37 ጊዜያት ተሽከርክራ ተልዕኮዋን እንደፈጸመችም ከጁፒተር ምኅዋር ተላቃ ኅዋው ላይ ራሷን በራሷ አንድዳ ትከስማለች። እስከዚያው ድረስ ግን ኅዋ ቃኚቷ፤ ሰው አልባዋ መንኲራኲር፤ ጁኖ ለአያሌ ጥያቄዎች መልስ ትሰጣለች፤ የናሳ ምኞት ነው። እንዲያም ኾኖ ግን በርካታ ጥያቄዎች ያኔም ገና ሳይፈቱ ሊቀሩ ይችላሉ።

በሞላላ ክበብ ምኅዋሯ ውስጥ ድኝ እና የረጋ የአለት ፍሳሽ የሚገኝበትን ጨምሮ በርካታ ጨረቆች ያለዕረፍት የሚሽከረከሯት ጁፒተር ምሥጢሯ ሙሉ ለሙሉ ይፈታል ባይባልም እንኳ በጁኖ በኩል ብዙ መታወቁ እንደማይቀር ሳይንቲስቱ ገምተዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic