ከጀርመን አንድነት ምን እንማራለን? | ባህል | DW | 08.11.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጀርመንን አንድነት ምን እንማራለን?

ከጀርመን አንድነት ምን እንማራለን?

ጀርመናዉያን ከተዋሃዱ በኋላ ያገኙት የኤኮኖሚ እድገት እና በዓለም ደረጃ ያላቸዉ ተሰሚነት መጨመሩ ብቻ ሳይሆን ፤ ኑሮአቸዉ የተሻሻለዉ ከተዋሃዱ በኋላ መሆኑ በግልፅ የታየ ነዉ። በሰላም መኖር የጀመሩትም፤ የዓለም ስደተኛ ሁሉ ወደ እነሱ መምጣት መፈለግ የጀመረዉ ሁሉ የሚከፋፍላቸዉ ግንብና ርዕዮተ ዓለምን ካስወገዱ በኋላ ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:39

አንድነት ኃይል ፤ መከፋፈል ደግሞ ድህነት ነዉ

«ጀርመናዉያን ከተዋሃዱ በኋላ ያገኙት የኤኮኖሚ እድገት እና በዓለም ደረጃ ያላቸዉ ተሰሚነት መጨመሩ ብቻ ሳይሆን ፤ ኑሮአቸዉ የተሻሻለዉ ከተዋሃዱ በኋላ መሆኑ በግልፅ የታየ ነዉ።  በሰላም መኖር የጀመሩትም፤ የዓለም ስደተኛ ሁሉ ወደ እነሱ መምጣት መፈለግ የጀመረዉ ሁሉ የሚከፋፍላቸዉ ግንብና ርዕዮተ ዓለምን ካስወገዱ በኋላ ነበር። እነዚህ ማኅበረሰቦች ወደ ጀርመን መምጣት መፈለግ ኤኮኖሚያቸዉ ስላደገ ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡም ያደገ በመሆኑ ነዉ። ጀርመናዉያን ከሌላዉ ለየት ያሉ ናቸዉ። ሰላምን የሚፈልጉ ናቸዉ። ጦርነትን የሚፈልጉ አይደለም ፤ ችግር ባለበት ቦታ ሁሉ ማማከልን፤ መሸምገልን  ይፈልጋሉ። ማስታረቅን ይፈልጋሉ።  አንድ ሁኑ ነዉ የሚሉት። ከአዉሮጳ ኅብረት እንግሊዞች እንዉጣ ሲሉ አዉሮጳን አንድ ለማድረግ ፊት ቆመዉ እየመሩ ያሉት ጀርመኖች ናቸዉ። ምክንያትም የአንድነትን ጥቅም በራሳቸዉ ስላዩት ነዉ።  ይህ ብቻ አይደለም። 40 ዓመት ተለያይተዉ ሲኖሩ የመለያየትን ጉዳትንም ጭምር ያዩ በመሆናቸዉም ነዉ»

አቶ መስፍን አማረ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ስለጀርመናዉያን አንድነት የተናገሩት ነበር። አቶ መስፍን አማረ ከ 30 ዓመት በፊት በምስራቅ ጀርመን የነጻ ትምህርት እድል አግኝተዉ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ያጠናቀቁ ናቸዉ። ጀርመን ተከፋፍላ ሳለ በምስራቅ ጀርመን ኖረዉ፤ ሁለቱ ጀርመኖችም ሲዋሃዱ፤ በርሊን ላይ ሆነዉ፤ ሁለቱ ጀርመኖች ተዋህደዉ 30 ዓመትን ካስቆጠሩ በኋላ ጀርመንን እድገት የፖለቲካ አካሄድ የህዝቡን ምንነት የባህሉን እንዴትነት ጠንቅቀዉ ያዉቃሉ። ዘንድሮ በያዝነዉ ወር ጀርመናዉያን በምስራቅና በምዕራብ የከፈላቸዉ ግንብ የተገረሰሰበትን 30ኛ ዓመት እያሰቡ ነዉ ። የዛሬ 30 ዓመት፤ በጎርጎረሳዉያኑ ኅዳር 9 ማለትም  November 9.ግንቡ የተገረሰሰበትን «ታሪካዊ ቀን» ሲሉ ያስቡታል። አቶ መስፍን በመቀጠል ስለ ጀርመን ዉኅደትእንደምታ ያወሳሉ። 

« ጀርመናዉያን የጦርነትንም ጉዳት አይተዋል። ይህ ሕዝብ በጦርነት ተጎድቶ አገሪቱ ድምጥማጥዋ ጠፍቶ ነበር። በኃያላን ሃገሮች በጀት በአዉሮፕላን ቦምብ ተደብድበዋል። ከዝያም አልፎ በሂትለር በተባለዉ በራሳቸዉ ሰዉ  ጦርነት ተጀምሮ ነዉ ሌሎችን መጉዳት የተጀመረዉ። በዚህም ምክንያት በሌሎች ላይ ክፉ ነገር ማድረግ እና ማሰብ በመጨረሻ መዘዙ ለራስ መሆኑንም አይተዉ ተምረዋል። ይሄንን ነዉ ለተቀረዉ ዓለም ማስተማር የሚፈልጉት፤ ሌሎችን አትንኩ በሰላም ኑሩ። ዓለም ለሁላችንም ትበቃናለች እያሉ እያስተማሩ፤ አሁን እነሱ አድገዉ ሌላዉ ዓለም ወደ እነሱ እየመጣ ነዉ። በቅርቡ አራት ሚሊዮን ስደተኛ የመጣበት የዓለም ሃገር ቢኖር ጀርመን ብቻ ነዉ። በዚህ ዓለም ይህን ያህል ቁጥር ስደተኛን የተቀበለ ሃገር የትም የለም ። ይህ የሚያሳየዉ አንድነት በዓለም ደረጃ እንዴት ከፍ አድርጎ ሊያሳይ እንደሚችል ነዉ።»   

 

በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወቅት ከመሃል አዉሮጳ የተነሳዉ የሂትለር ጦር ፤ ራሽያ ፈረንሳይ፤ ብሪታንያንን ጨምሮ አዉሮጳን ሁሉ ለመግዛት ሲነሳ፤ ከምስራቅ አዉሮጳ በኩል በናዚን ጦር ላይ ድል የተቀዳጀዉ የሶቭየት ሕብረት ጦር ምስራቅ ጀርመንን ተቆጣጠረ። ከሰሜን፣ ከደቡብና ከምዕራብ ጀርመን የዩናይትድ ስቴትስ፤ የብሪታንያ፣ የፈረንሳይና የተባባሪዎቻቸዉ ሐገራት ጦሮች የናዚ ጦርን እየገፉ በርሊን ላይ አንበረከኩት። የዝያን ጊዜዎቹ ኃያላን መንግሥታት ጦራቸዉ ወደ ጀርመን ዘልቆ የገባበትን እና የናዚ ጦርን የወጋበትን ግዛት ተቆጣጠረ ። የምስራቅ ጀርመንን የተቆጣጠረዉ የሶሻሊስት ርዕዮት ዓለምን የሚያራምደዉ የሶቭየት ሕብረት፤ መንግስት ብቻዉን ምስራቅ ጀርመንን ሲቆጣጠር ፤ የካፒታሊስት ርዕዮተ ዓለምን የሚያራምዱት በዩናይትድ ስቴትስ የሚመሩት መንግስታት በጋራ ምዕራብ ጀርመንን በመያዝ መምራት ጀመሩ።

ጀርመን በሁለት ርዕዮት ዓለም ተከፍላ ምዕራብ እና ምስራቅ ጀርመን ተብላ ፤ በግንብ ታጥራ ዘለቀች። የዛሬ 30 ዓመት ይህ ከፋፋይ ግንብ ተገርስሶ በምስራቅና በምዕራብ ጀርመን ተከፍሎ ይኖር የነበረዉ ሕዝብ፤ አንድነትን አግኝቶ፤ በኤኮኖሚ በቴክኖሎጂ እና በእድገት ጀርመንን መስርተዉ፤ ሃገራቸዉ ከዓለም ቀዳሚ ሐገራት አንዷ እንድትሆን አድርገዋል። ዛሬ ጀርመናዉያን ለሃገራቸዉ አንድነት ብቻ ሳይሆን፤ አዉሮጳንም አንድ ለማድረግ በሚያደርጉት ጥረት ቀዳሚዉን ስፍራ ይዘዉ ይገኛሉ። በምስራቅ ጀርመን ተማሪ የነበሩት አቶ መስፍን አማረ በምስራቅ ጀርመን ይኖር የነበረዉ ሕዝብ የጀርመንን አንድነት እጅግ ይፈልግ ነበር፤ መንግሥቱም ቢሆን ተገዶ ነዉ እንጂ አንድነትን ይሻ ነበር ሲሉ  አስታዉሰዋል።  

ሌላዉ የምስራቅ ጀርመን ተማሪ አቶ መኮንን ሽፈራዉ ይባላሉ። በጎርጎረሳዉያኑ 2010 ዓ.ም የጀርመን መንግሥት፤ በጀርመን ሃገር ድርጅት አቋቁመዉ የዉጭ ሃገር ዜጎች ከአገሪቱ ህዝብና ባህል ጋር ተዋህደዉ እንዲኖሩ ባደረጉት ጥረት ከመራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ጽ/ቤት የክብር ሜዳሊያ ተሸልመዋል።  አቶ መኮንን ጀርመን በተለያየ ርዕዮተ ዓለም ለሁለት ተከፍላ ሳለ በቀድሞዋ ምስራቅ ጀርመን የትምህርት እድል አግኝተዉ ነዉ ወደ አዉሮጳ የመጡት። ከ30 ዓመት በፊት ወደ ምስራቅ ጀርመን የመጡት አቶ መኮንን የጀርመንን ዉህደት አይተዋል። ዉህደቱ አንድነት ኃይል ብልፅግናን እና ክብርን እንዳመጣላቸዉም መስክረዋል።

አቶ መስፍን አማረ በበኩላቸዉ የጀርመኖች መዋሃድ በጣም ጥቂት የምስራቅ ጀርመን ነዋሪዎች ላይ ቅሬታን ቢፈጥርም በአጠቃላይ ግን ኑሮአቸዉን ሙሉ በሙሉ ወደ ጥሩ እንደለወጠዉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ መለያየትን፤ የብሔር ልዩነትን ማንሳት እየተለመደ ሆንዋል። የጀርመን ዉህደት 30ኛ ዓመትን ስናስብ፤ የሃገሪቱን የእድገት ደረጃ በአዉሮጳ ብሎም በዓለም የምጣኔ ሃብት መዘርዝር ቀዳሚዋ መሆንዋን ስናይ ምን ልንማር፤ ምን ልናይ ይገባል ይሆን?

ከ 30 ዓመታት በፊት በቀድሞዋ ምስራቅ ጀርመን የነፃ ትምህርት እድልን አግኝተዉ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ያጠናቀቁት እና አሁንም በጀርመን ነዋሪ የሆኑትን አቶ መስፍን አማረ እና አቶ መኮንን ሽፈራዉ ለሰጡን ቃለ-ምልልስ እያመሰገንን፤ ሙሉ ቃለ-ምልልሱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።  

 

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ  

Audios and videos on the topic