ከጀርመን ምርጫ ሕዝቡ ምን ይጠብቃል? | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 21.09.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ከጀርመን ምርጫ ሕዝቡ ምን ይጠብቃል?

 ከምርጫው አስቀድሞ በሚካሄዱ መጠይቆች መሠረት የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ እጩ ኦላፍ ሾልትስ ከሌሎቹ ተወዳዳሪዎች የተሻለ ድምጽ ሊያገኙ ይችላሉ ተብሎ ተገምቷል። ባለፉት አስራ ስድስት ዓመታት የበላይነቱን ይዞ የቆየው የሜርክል የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ በሌሎቹ ፓርቲዎች እንዲተካ ህዝቡ ከፍተኛ ፍላጎት አለው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:06

ከጀርመን ምርጫ ሕዝቡ ምን ይጠብቃል?

ጀርመናውያን ፣የምክር ቤት እንደራሴዎችቻቸውን ከአምስት ቀናት በኋላ ይመርጣሉ። ምርጫው በተቃረበበት በአሁኑ ጊዜ እጩ ተወዳዳሪዎች በየመድረኩ የምረጡኝ ዘመቻቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። ለመራኄ ወ መራኂተ መንግሥትነት የሚወዳደሩት የዋነኛዎቹ ፓርቲዎች እጩዎችም ከትናንት በስተያ የመጨረሻ የቴሌቪዥን ክርክር አካሂደዋል። ጀርመንን ለ16 ዓመታት የመሩት የጀርመኑ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ አንጋፋ ፖለቲከኛ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የማይወዳደሩበት የዘንድሮው የጀርመን ምርጫ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።በጀርመን የመጀመሪያዋ ሴት መራኄ መንግሥት ሜርክል የሌሉበት ይህ  ምርጫ ከከዚህ ቀደሞቹ በዓይነቱ የተለየም ተብሏል። በአሁኑ ጊዜ ከሜርክል  በኋላ ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልገው መራጭ ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ ከአንድ ሳምንት በፊት በተለያዩ የጀርመን ከተሞች የተዘዋወረው የአማርኛው አገልግሎትን ጨምሮ የዶቼቬለ የአፍሪቃ ክፍል የጋዜጠኞች ቡድን ተረድቷል። ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ በእርግጠኝነት ለመገመት ያዳገተው የዘንድሮው የጀርመን ምርጫ ያልተጠበቀ ውጤት ሊያስከትል የመቻሉም ስጋት አለ ።ከጀርመን አገር አቀፍ ምርጫ አስቀድሞ ለመራኄ መንግሥትነት የሚወዳደሩ እጩዎች ከሚያካሂዱት የቴሌቪዥን ክርክር ፣ሦስተኛውና የመጨረሻው ከትናንት በስተያ ተካሂዷል። በዚህ ክርክርም የመሀል ግራ አቋም ያለው የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በምህፃሩ SPD እጩ ኦላፍ ሾልትስ Olaf Scholz እና ለተፈጥሮ ጥበቃ የሚሟገተው የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እጩ አናሌና ቤርቦክ Annalena Baerbock ተፎካካሪያቸውን የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ ማለትም የCDUን እጩ አርሚን ላሼትን በአመዛኙ በዚህ ክርክር በጋራ ተቃውመዋቸዋል። ከክርክሩ በኋላ በተካሄደ መጠይቅ መሠረት ኦላፍ ሾልትስ አሸናፊ ተብለዋል።ላሼት ደግሞ ሁለተኛውን ደረጃ አግኝተዋል። ሦስቱ ፖለቲከኞች  ከዚህ ምርጫ በኋላ የሚሰናበቱትን የጀርመን መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልን ለመተካት የሚወዳደሩ ግንባር-ቀደም የመራኄ መንግሥት እጩዎች ናቸው።  ከምርጫው አስቀድሞ በሚካሄዱ መጠይቆች መሠረት የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ እጩ ኦላፍ ሾልትስ ከሌሎቹ ተወዳዳሪዎች የተሻለ ድምጽ ሊያገኙ ይችላሉ ተብሎ ተገምቷል። ከአንድ ሳምንት በፊት በርሊን ፖትስዳም ሐምቡርግ  ሃለ እና አኽን በተባሉት ከተሞች የምርጫ እንቅስቃሴዎችን ተዘዋውሮ የተመለከተው የዶቼቬለ የአፍሪቃ ክፍል የጋዜጠኞች ቡድን በተለያዩ የጀርመን ከተሞች ባደረገው ቅኝት ህዝቡ ለውጥ ይመጣበታል ብሎ የሚያምነውን ይህን ምርጫ በጉጉት እየጠበቀ መሆኑን ተረድተናል። ባለፉት አስራ ስድስት ዓመታት የበላይነቱን ይዞ የቆየው የሜርክል የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ በሌሎቹ እንዲተካ ከፍተኛ ፍላጎት አለው። አኽን በተባለችው የምዕራብ ጀርመን ከተማ

ውስጥ ያገኘናት በእለቱ የአንድ የንግድ መደብርን ቅናሽ በማስተዋወቅ ላይ የነበረች ሽቴፋኒ ሽሮበል የተባለች  አንዲት ጎልማሳ እንደነገረችን የርስዋ ምርጫ የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ እጩ ሾልትስ ናቸው።እሳቸውን የምትመርጥበት ምክንያትም አላት። በአንጻሩ ተጨባጭ ነገሮች ላይ አያተኩሩም ያለቻቸው የክርስቲያን ዴሞክራቱ እጩ ላሼት የአኽን  ሰው ቢሆንም ድምጽዋን ለርሳቸው አትሰጥም።
« እንደሚመስለኝ የSPDው እጩ ሾልትስ አብዛኛዎቹን  ጀርመናውያን በጥሩ ሁኔታ ይወክላሉ ብዬ አምናለሁ።አርሚን ላሼት ግን የመመረጥ እድል ያላቸው አይመስለኝም። የርሳቸው ፖለቲካ አያስደስትም። ምክንያቱም ርሳቸው ብዙ ስህተቶችን ሰርተዋል። በጊዜያዊ  ነገር ላይ ከማተኮር ውጭ ተጨባጭ የሆነ መርሃ ግብር ራሳቸው  ነድፈው የሚንቀሳቀሱ አይደሉም። እውነቱን ለመናገር ላሼት መራኄ መንግሥት እንዲሆኑ አልመኝም።»
ሌላዋ የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ደጋፊ አነም CDU በቃው የሚል አስተያየቷን ነው የሰጠችን ።
«አርሚን ላሼትና የፓርቲያቸው CDU ፖለቲካ ለጀርመን ትክክለኛ ፖለቲካ አይመስለኝም በተለይ ለወጣቱ የሚሆን አይደለም።ከሚወጡ ጽሁፎች እንደምረዳው CDU ን የሚመርጡት እድሜያቸው የገፋ ሰዎች ናቸው።እኔም ብሆን ወጣት አይደለሁም።ልጆቼ ግን ሌላ ዓለም ሌላ ሕይወት እንዲኖራቸው ነው የምፈልገው ።»
መሀል ገበያ ውስጥ ከአንድ ማረፊያ ቦታ ላይ ተቀምጣ ልጅዋን እያበበለች ያገኘናት ላማራ የተባለችው ወጣት ምርጫ ደግሞ ፣የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ነው።እርስዋ እንደምትለው አሁን በጀርመን አጠቃላይ ለውጥ ያስፈልጋል።ምርጫውም ትኩረት የሚሰጠው ነው። 
«ይህ ምርጫ ለጀርመን እጅግ ወሳኝ ነው። በአጠቃላይ ሁለንተናዊ ለውጥ ያስፈልጋል። ለረዥም ጊዜ CDU መርቷል።አሁን ከተሰባሰበው አስተያየት ውጤት መረዳት የሚቻለው በመጀመሪያ  ደረጃ የመንግሥት ለውጥ እንደደረግ ነው የሚፈለገው።በበኩሌ የፓርቲውን እጩ መራኄ መንግሥት ባልደግፍም ድምጼን የምሰጠው ለአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ነው።ይህን የማደርግበት ምክንያቶች አሉኝ።እስካሁን ጥሩ ስራ ሰርተዋል።ከሁሉም  በላይ የተለያዩ ሃሳቦቻቸውንም እደግፋለሁ።» 
ዶቼቬለ ያነጋገራቸው አብዛኛዎቹ የአኽን ነዋሪዎች ላሼት ከአኽን ስለሆኑ ብቻ እንደማይመርጧቸው ነው የነገሩን።ማንም እጩ ከየትም ይሁን ከየት  ምን ሊሰራ ሊለውጥ ይችላል የሚለው ዋናው የምርጫ መመዘኛ መሆኑን ነው ያስረዱን። በከተማዋ ማዕከል ከባለቤታቸውና ከልጃቸው ጋር ያገኘናቸው ማርኩስ ይህን ካሉን አንዱ ናቸው።ስለ ዘንድሮው ምርጫ አስተያየታቸውን

ሰጥተውናል።
«ከባድ ምርጫ ነው።እኛ ራሳችን ማን መጨረሻ ላይ አሸንፎ  እንደሚመራን አናውቅ።ተወዳዳሪው ከአኽንም ይምጣ ከየት ያን ያህል ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም።ዋናው ነገር ምን ይዞ ይመጣል የሚለው ነው ቁም ነገሩ።»
ማርኩስ በአኽን ከግንባር ቀደሞቹ እጩዎች አንዱ የሆኑት ላሼት ይመረጣሉ ብለው ከሚያምኑት ውስጥ አንዱ ናቸው።የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ደጋፊ  አነ እንደምትለው ደግሞ የዘንድሮ መራጮች ትኩረት የአየር ንብረት ጉዳይ መሆኑ አይቀርም።በቅርቡ በተለያዩ የጀርመን ከተሞች ከፍተኛ ጥፋት ያደረሰውን የጎርፍ አደጋ ያስታወሰችው አነ ችግሩ የደረሰበትና በአዓይኑ ያየው ህዝብ አሁን ለአየር ንብረት ጉዳይ ትኩረት ይሰጣል ብላ ታምናለች ።
«የአየር ንብረት ለውጥ እየታየ ነው።ይህን ደግሞ የተገነዘቡት ይመስለኛል አንድ ነገር ማድረግ አለብን ይላሉ።ስለዚህ ምናልባት በዚህ ምርጫ ከዚህ ቀደም ለአየር ንብረት ደንታ የማይሰጣቸው ችግሩን አይቶ እንዳላየ ያልፉ የነበሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ምርጫ ድምጻቸውን ይሰጣሉ ብዬ አምናለሁ።»
ከአስተያየት መመዘኛዎች መረዳት እንደሚቻለው የሜርክል ፓርቲ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት የነበረው ድጋፍ እየቀነሰ የሄደ ይመስላል ።አሁን የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ጎልቶ በመውጣት ላይ መሆኑ ነው የሚታየው። በአኽን የፓርቲዎች የምርጫ መረጃ መስጫ ስፍራ ላይ ያገኘናቸው አንድ የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ እንዳሉን እስካሁን ከክርስቲያን ዴሞክራቶች ና ከከክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች ጋር ተጣምሮ ጀርመንን ሲመራ የቆየው SPD ከአሁን በኋላ ከነርሱ ጋር አብሮ የመስራት ፍላጎት የለውም።
«ከCDU እና ከCSU ጋር ተጣምረን መንግሥት መመስረት አንፈልግም። እኛ ተራማጅ ፖለቲካ አለን ብለን ነው የማናስበው። እነርሱ ወግ አጥባቂዎች ናቸው።እና በጀርመን ለውጥ ማምጣት አለብን ብለን እናምናለን። ይህ ደግሞ ከነርሱ ጋር በመስራት የሚመጣ አይደለም ስለዚህ ከአረንጓዴዎቹ ከግራዎቹ እንዲሁም ከነፃ ዲሞክራቶች ፓርቲ ጋር መነጋገር እንፈልጋለን።የጀርመንን ፖለቲካ የሚለውጥ ጥምረት ይፈጠራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ»
የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ይህን ቢልም CDU ግን እጅ አልሰጠም። ከሜርክል የበለጠ የፖለቲካ ልምድ አላቸው የሚባሉት ላሼት ብዙ ህዝብ በሚኖርበት በኖርድ ራይን ቬስትፋለን ፌደራዊ ክፍለገር ጠቅላይ ሚኒስትርነት፣በፊደራል ደረጃም በልዩ ልዩ ሃላፊነቶች እንዲሁም በአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ አባልነትም አገልግለዋል። አኽን ያደጉት ላሼት ጥሩ አውሮጳዊም ይባላሉ።ይህም ተባለ ያ የትኛው ፓርቲ ምርጫውን ያሸንፋል? ከማንስ ጋር ተጣምሮ መንግሥት ይመሰርታል የሚለው የምርጫ እለትና ከዚያ በኋላ ባሉት ቀናት ነው የሚታወቀው ምርጫው አምስት ቀናት በቀሩበት በአሁኑ ወቅት ውጤቱ እንዳጓጓ ቀጥሏል።  
 

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች