ከየመን 141 ሰዎች በአውሮፕላን ተጓጓዙ | አፍሪቃ | DW | 14.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ከየመን 141 ሰዎች በአውሮፕላን ተጓጓዙ

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት 141 የውጭ ዜጎችን ከየመን ማውጣቱን አስታወቀ። አሁንም ከ16,000 በላይ ሰዎች ወደ አገራቸው ለመመለስ መመዝገባቸውን ያስታወቀው ድርጅቱ ከ100,000 በላይ ኢትዮጵያውያን በየመን ይገኛሉ ብሏል። ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች የመን የሰብዓዊ ቀውስ ሊገጥማት ይችላል በማለት ቢያስጠነቅቁም ሰሚ አላገኙም።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት( IOM) 141 ሰዎች የጫነ አውሮፕላን ሚያዝያ 4/2007 ከየመን ወደ ሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም መብረሩን አስታውቋል። የተልዕኮው መሳካት አሁንም በየመን የሚገኙ 16, 000 በላይ ፈቃደኛ የውጭ ዜጎችን ወደ አገሮቻቸው ለመመለስ በር ይከፍታል የሚል ተስፋ በድርጅቱ ዘንድ አሳድሯል። 141 ሰዎች ጭኖ ከሰንዓ በመነሳት ካርቱም ለደረሰው አውሮፕላን የበረራ ፈቃድ ለማግኘት እና ለተመላሾቹ የሚያስፈልጉ ጉዳዮችን ለማመቻቸት ከአንድ ሳምንት በላይ ወስዷል። የድርጅቱ ቃል አቀባይ ዦኤል ሚልማን አሁን ወደ ሱዳን የተጓዙት 141 ስደተኞች ወደ አገራቸው ለመመለስ የጠየቁ መሆናቸውን ይናገራሉ።

«አሁን ከየመን የምናወጣው ከአገሪቱ ደህንነታቸው ተጠብቆ ለመጓዝ የጠየቁ የውጭ አገር ዜጎችን ነው። አሁን ተልዕኮውን የምናከናውነው ከሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ሲሆን በዚህ ሳምንት መጨረሻ አካባቢ ወደ ኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ እንቀይራለን። ከ16,000 በላይ ሰዎች እና ከአርባ በላይ አገራት ከየመን መውጣት ስለሚችሉበት ሁኔታ ጠይቀውናል። ሰዎች ብዙ አይነት ርዳታ ይፈልጋሉ። እኛም የተቻለንን ያክል እየሰራን ነው።»

አሁን ወደ ሱዳን ከተጓዙት ስደተኞች መካከል ብዙዎቹ በሰንዓ አውሮፕላን ማረፊያ ለበርካታ ቀናት ሲጠባበቁ የከረሙ ናቸው ተብሏል። ወደ ሱዳን ለመጓዝ ከተመዘገቡትና ከየመን ለመውጣት ከተፈቀደላቸው የውጭ አገሮች ሰዎች መካከል በርካቶች ከአውሮፕላን ማረፊያው መድረስ ሳይችሉ መቅረታቸውን የጉዞው አስተባባሪ ሳባ ማልሜ ተናግረዋል። ከሰንዓ ወደ ካርቱም ከበረሩት የውጭ አገር ሰዎች መካከል የሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ዩ.ኤስ. አሜሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሶርያ፣ ኢራቅ፣ ኢንዶኔዥያና የአውሮጳ አገራት ዜጎች እንደሚገኙበት ዦኤል ሚልማን ተናግረዋል። ከየመን ለመውጣት የተመዘገቡት ሰዎች ቁጥር 16,000 ብቻ ቢሆንም በርካታ የሌሎች አገራት ሰዎች አሁንም በየመን አደጋ ውስጥ መሆናቸውንም ቃል አቀባዩ ያስረዳሉ።

«እጅግ በርካታ የውጭ አገር ሰዎች አሁን በየመን ይገኛሉ። ከ100,000 በላይ ኢትዮጵያውያን እና ወደ 250,000 የሚጠጉ ሶማሊያውያን አሁንም በየመን አሉ። ነገር ግን ሁሉም በአደጋ ውስጥ መሆናቸውንና እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አያውቁም። ከተለያዩ አገሮች የመጡ ዴፕሎማቶች፤የእርዳታ ሰራተኞች፤ነጋዴዎች፤ተማሪዎችና የውጭ አገር ዜጎች ቤተሰቦች በየመን ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች ከየመን ለመውጣት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ማወቅ ይሻሉ።»

ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች የየመን ጦርነት ከፍተኛ የምግብ እጥረትን ጨምሮ ወደ ሰብዓዊ ቀውስ ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋታቸውን በተደጋጋሚ ቢገልጹም ሰሚ አላገኙም። ሳዑዲ አረቢያና አጋሮቿ በሑቲ አማጽያን ላይ የሚያደርጉት የአየር ድብደባ ለሶስተኛ ሳምንት ቀጥሏል። በዚህ ሳምንት የመጀመሪያ ቀናት በአደን እና በሰሜናዊ የመን በምትገኘው የዳሌህ ከተማ ከፍተኛ ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዎች ሳኡዲ አረቢያና አጋሮቿ በሚያደርጉት የአየር ጥቃት በንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።


እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic