ከዓለም አግላይዋ ስትገለል | ዓለም | DW | 16.10.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ከዓለም አግላይዋ ስትገለል

ፕሬዝደንት ትራምፕ ስምምነቱን ኢራን ወይም ሌላ ወገን አፍርሶታል የሚል ምክንያት አላቀረቡም።ሊያቀርቡ አይችሉም።የሚያቀርቡት ምክንያት ሥለሌለም ሥምምነቱን በቀጥታ አላፈረሱም።ምክር ቤታቸዉ የስምምነቱን ይዘት ዳግም መርምሮ በስልሳ ቀናት ዉስጥ እንዲያቀርብላቸዉ ነዉ የጠየቁት።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:48
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
13:48 ደቂቃ

የትራምፕ ጉዞ

 

ኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብሯን ለማቆም፤ ኃያሉ ዓለም የጣለባትን ማዕቀብ ለማንሳት ከሁለት ዓመት በፊት ሲስማሙ እነሱ ሁለት ነበሩ።የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የሳዑዲ አረቢያዉ ንጉስ ሳልማን ኢብን አብዱል አዚዝ።ተቃወሙ።ባለፈዉ አርብ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ተጨመሩ።ሰወስት ሆኑ።እሷ አንድ ነበረች።ኢራን።እነሱ የአዉሮጳ ሕብረት፤ቻይና፤ ሩሲያ፤ ዩናይትድ ስቴትስ ፤ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ነበሩ።ዶናልድ ትራምፕ ዩናይትድ ስቴትስን ከተቀረዉ ዓለም ነጥለዉ፤ከቴልአቪቭ-ሪያዶች ጎራ እንደሚቀይጡ ባለፈዉ አርብ ሲዝቱ ኢራን ዓለምን ተቀየጠች።የትራምፕዋ ዩናይትድ ስቴት አቋም መነሻ፤የኑክሌር ስምምነቱ ማጣቃሻ፤ የዓለም ሠላም እንዴትነት መድረሻችን ነዉ። 

ዋሽግተን የሚገኘዉ የስልታዊ ጥናት ተቋም ኃላፊ ጆኤል ራቢን እንደሚሉት የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አሳሳቢ ችግር የሚሉ-የሚያደርጉትን ለመገመት አለመቻሉ ወይም ተለዋዋጭ መሆናቸዉ ነዉ።«እንዲሕ ዓይነት ተለዋዋጭነት ለዓለም ሠላም አደገኛ ነዉ።» ይላሉ ተንታኙ።«ያለዉ አደጋ የአለመተንበዩ አደጋ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ነዉ።

እንደማምነዉ ፕሬዝደንቱ እንዲሕ ዓይነቱ አቋም ዩናይትድ ስቴትስን ያጠናክራል፤ለመደራደር ይጠቅመናል ብለዉ ያምናሉ።ይሁንና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች የሚሉ-የሚያደርጉት አለመተንበዩ አለመረጋጋትን ያስከትላል።»

ሰዉዬዉ በርግጥም የሚሉትን የሚያዉቁ፤የሚያዉቁትን የሚሉ መሆናቸዉ ለብዙዎች አጠራጣሪ ነዉ።አሜሪካን ለማስቀደም ቃል በገቡ ማግስት አሜሪካ ከመሰረተች እና ከምትመራዉ የጦር ተሻራኪ ድርጅት (ኔቶ) አባልነት እንደሚያስወጡ አስጠነቀቁ።አስጠነቀቁ ግን ተዉት።

 

ከተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ እስከ ናፍታ፤ ከTPP እስከ ዩኔስኮ፤ከሜክሲኮ እስከ ሰሜን ኮሪያ፤ከኩባ እስከ አፍቃኒስታን የሚሉ-ያደረጉት ብዙዎች ያለሰቡ እና ያልገመቱት ነዉ።ኢራንን ማዉገዝ፤ ማሳጣት፤ መጎነጥ፤ የጀመሩት በርግጥ ከምርጫ ዘመቻቸዉ ጊዜ ጀምሮ ነዉ።አስራ-ሁለት ዓመት ያወዛገበ፤ያደራደረ፤ ያወያየዉን፤ ዓለም የተስማማበትን ዉል ለማፍረስ ይዝታሉ ብሎ መጠበቅ ግን ለዉጪዉ ዓይደለም ለመከላከያ ሚንትራቸዉም የማይታሰብ ነዉ።ኢራቅ ይዋጋ የነበረዉን የአሜሪካ ጦር ያዙ ነበሩት የቀድሞዉ ጄኔራል ጄምስ ማቲስ ፕሬዝደንቱ ከኢራን ጋር የተደረገዉን ዉል እንዲያከብሩ መክበረዉ ነበር።

                     

«እንደማምነዉ አሁን ባለንበዉ ሁኔታ--ፕሬዝደንቱ (ዉሉ) ማክበርን እግምት ማስገባት አለባቸዉ።»ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሬክስ ቲለርሰንም ተመሳሳይ አስተያየት ነበራቸዉ።ፕሬዝደንቱ ግን ባለፈዉ  አርብ እንዳሉት የሚንስትሮቻቸዉን ምክር አልተቀበሉም።«የሕግ-መምሪያዉና መወሰኛዉ ምክር ቤት ዋና ዋና መሪዎች የኢራንን የኑክሌር ስምምነት ደንብን የሚያሻሽል ረቂቅ እያዘጋጁ ነዉ።ማሻሻያዉ በዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መሠረት ኢራን አሐጉር አቋራጭ ሚሳዬል መስራቷን (ይሕ በጣም አስፈላጊ ነገር ነዉ) ለመገድ እና ኑክሌር  ለመስራት የምታደርገዉን እንቅስቃሴ ለዘለቄታዉ የሚያግድ መሆን አለበት።ይሕ በጣም አስፈላጊ ነዉ።እኔ እደግፈዋለሁ።»

የኢራን የ

ኑክሌር መርሐ ግብርን ለማስቆም የቴሕራንና የኃያላን መንግስታት ተወካዮች አስራ-ሁለት ዓመት ተደራድረዋል።በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ያላቸዉ የአምስቱ ሐገራት፤የጀርመንና የአዉሮጳ ሕብረት ተወካዮች ከረጅም ጊዜ ዉጣ ዉረድ ድርድርና ዉይይት መሠረት የደረሱበት ስምምነት አስጊ ጦርነትን በሰላም የመፍታት አብነት ነበር።

 

የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዚግማር ጋብርኤል በቀደም እንዳሉት ደግሞ ስምምነቱ ሌሎች ሐገራትም ሰላምና ደሕንነታቸዉን በሰላማዊ ድርድር ማስከበር እንደሚችሉ አብነት ነዉ።

                            

«ከኢራን ጋር የተደረገዉ ስምምነት ጦርነትን በድርድር ማስቀረት እንደሚቻል ለመጀመሪያ ጊዜ ያስመሰከረ ዉል ነዉ።ከሁሉም በላይ አንድ ሐገር የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዳትታጠቅ ለመከልከል የሚጠቅም ነዉ።ሰሜን ኮሪያን የመሳሰሉ ሐገራትን ምናልባትም ሌሎችንም ኑክሌር የጦር መሳሪያ ሳይታጠቁ ደሕንነታቸዉ እንደሚጠበቅላቸዉ ለማሳመን እንደ ጥሩ ምሳሌ የሚጠቀስም ነዉ።ይሕን ስምምነት ማፍረስ በመላዉ ዓለም የሚገኙ ሌሎች ኃይላት እንዲሕ አይነት ስምምነቶችን እንዳያምኑ ማድረግ ነዉ።ስለዚሕ አደጋዉ ከኢራንም ያለፈ ነዉ።»

በ2015 (እጎአ) በተፈረመዉ «የጋራ አጠቃላይ የድርጊት መርሐ-ግብር (JCPOA)» በተባለዉ ስምምነት መሠረት ኢራን የኑክሌር መርሐ ግብሯን ሙሉ በሙሉ ማቆምዋን የተባበሩት መንግሥታት የአቶም ኃይል ተቆጣጣሪ ድርጅት አረጋግጧል።ድርጅቱ በማረጋገጡም በኢራን ላይ የተጣለዉ ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ተነስቷል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ ስምምነቱን ኢራን ወይም ሌላ ወገን አፍርሶታል የሚል ምክንያት አላቀረቡም።ሊያቀርቡ አይችሉም።የሚያቀርቡት ምክንያት ሥለሌለም ሥምምነቱን በቀጥታ አላፈረሱም።ምክር ቤታቸዉ የስምምነቱን ይዘት ዳግም መርምሮ በስልሳ ቀናት ዉስጥ እንዲያቀርብላቸዉ ነዉ የጠየቁት።

                            

«ከምክር ቤቱና ከተባባሪዎቻችን ጋር በምንሰራዉ መፍትሔ ማግኘት ካልቻልን ግን ስምምነቱ ይፈርሳል።ሁል ጊዜ ይፈተሻል።እንደ ፕሬዝደንት የኛን ተሳትፎ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ማቋረጥ እችላለሁ።»

ወትሮም ስምምነቱን ሲቃወሙ የነበሩት ሳዑዲ አረቢያ እና እስራኤል የትራምፕን ዉሳኔ ለማወደስ የቀደማቸዉ የለም።የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ፌስ ኔሽን ለተባለ ጣቢያ እንደነገሩት የፕሬዝደንት ትራምፕን አቋም የምትደግፈዉ እስራኤል ብቻ አይደለችም።

                           

«ፕሬዝደንቱን የምትደግፈዉ እስራኤል ብቻ አይደለችም።ሳዑዲ አረቢያ እና ኤሚሬቶች ጭምር ናቸዉ።የምጠቁመዉ ነገር እስራኤል እና ቁልፍ የአረብ መንግስታት በአንድ ነገር ላይ ሲስማሙ ትኩረት ሊሰጠዉ ይገባል።በተጨባጭ ያለዉን ነገር በቅርብ እንሰማለን።ከኢራን አጠገብ ነን።ምን እንደምታደርግ እናዉቃለን።»

ፍልስጤምን ከዝንተ-ዓለም አገር አልባነት ለማዉጣት ቁልፍ የአረብ መንግስታት ከእስራኤል ጋር የማይተባበሩበትን ምክንያት ለፍልስጤሞች የሚነግር መጥፋቱ ነዉ-ክፋቱ።የትራምፕን አቋም በመደገፍ ቤንያሚን ኔትናያሁንና ሳልማን ኢብን አብዱል አዚዝን የሰማ እንጂ የተከተላቸዉ አለመኖሩ ነዉ ደግነቱ።

የዩናይትድ ስቴትስ የዴሞክራቲክ ፓርቲ የምክር ቤት እንደራሴ  እንኳን የፕሬዝደንት ትራምፕ «አሜሪካ ትቅደም፤ አሜሪካ ከወዳጅ

ደጋፊዎችዋ ትገለል ማለት እንዳይሆን ያሰጋል ነዉ ያሉት።የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በበኩላቸዉ «ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የተደረገዉ ስምምነት ካፈረሱ የምትገለለዉ ዩናይትድ ስቴትስ እንጂ ኢራን አይደለችም።» ይላሉ

የጀርመን፤የፈረንሳይ እና የብሪታንያ መሪዎች  በጋራ ባወጡት  መግለጫ እንዳሉት ፕሬዝደንት ትራምፕ ከኢራን ጋር የተደረገዉን ስምምነት አለማፅደቃቸዉ ሲበዛ አሳስቧቸዋል።ሐገሮቻቸዉ ስምምነቱን እንደሚያከብሩ በድጋሚ ቃል ገብተዋል።የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ  ፍሬድሪካ ሞግሔሬኒ ደግሞ ስምምነቱን አንድ ሐገር ሊያፈርሰዉ፤ሊያሻሽለዉም አይችልም ባይ ናቸዉ።የዓለም ስምምነት ነዉና።» አሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ሰነድ እያመለከቱ።

                                    

« የሁለትዮሽ ስምምነት አይደለም።የአንድ ሐገር ብቻ አይደለም።ስድስት ወይም ሰባት ወገኖችን ብቻ የሚያካትት ሥምምነት አይደለም።ይሕ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዉሳኔ ነዉ።በዚሕም ምክንያት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሐገራት በሙሉ ዉሳኔዉን ገቢር የማድረግ ግዴታ አለባቸዉ።»

ሰዉዬዉ ለዓለም አቀፍ አይደለም ለሐገራቸዉም ሕግ የሚገዙ አይደሉም።ግን ብዙ ሚሊዮኖች የመረጧቸዉ የዓለም ልዕለ ኃይል ሐገር መሪ ናቸዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ከሰሜን ኮሪያ ጋር በኑክሌር ጦር መሳሪያ ሰበብ የገጠመችዉን ጠብ ለማርገብ ዓለም ደፋ ቀና ሲል ትራምፕ በትንሺቱ ሐገር ላይ መዓት ለማዉረድ ፎከሩ።

ፉከራዉን የምር እንደማያደርጉት ሲያዉቁ በሕዝብ ደምፅ የተመረጡት የሰባ አንድ ዓመቱ አዛዉንት ከ33 ዓመቱ ወጣት አምባገነን ጋር ስድድብ ገጠሙ።ዩናይትድ ስቴትስ ከአፍቃኒስታን እስከ ኢራቅ፤ ከሶሪያ እስከ ሊቢያ የለኮሰችዉ ጦርነት ዛሬም ሚሊዮኖችን እያነደደ እየገደለ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ከሩሲያ ጋር የገጠመችዉ ሽኩቻ ዩክሬንን ከመካከለኛ ሐብታም ሐገርነት ወደ ተመፅዋችነት አሽቀንጥሯታል።

ዩናይትድ ስቴትስ ከ2001 (እጎአ) ጀምሮ በየስፍራዉ ዉጊያ ጦርነት ከመለኮስ ባለፍ የሰላም ዉል ያደረገችዉ አንድም ከኢራን ሁለትም ከኩባ ጋር ነበር።ፕሬዝደንት ትራምፕ እንደ ብርቅ ከሚታዩት ሰምምነቶች ከኩባ ጋር የተደረገዉን ለማፍረስ አንድ ሁለት እያሉ ነዉ።ከኢራን ጋር የተደረገዉን  ለማፍረስ የኢራን ገዢዎችን ማዉገዝ፤ መጎነታተሉን እንደ ጥሩ ፈሊጥ ይዘዉት ነበር።

ከሪያድ ቤተ-መንግሥት እስከ ኒዮርክ የጉባኤ-አዳራሽ፤ በየአደባባዩ ኢራንን አወገዙ፤አስፈራሩ፤ አስጠነቀቁ ተጨማሪ ማዕቀብ ጣሉ አሁን ደግሞ ዓለም የተስማማበትን ዉል ለማፍረስ ዛቱ።የኢራኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር መሐመድ ጃቫድ ዛሪፍ እንደሚሉት ሐገራቸዉ ስምምነቱን ለማፍረስ የመጀመሪያዋ አትሆንም።ሌላዉ ካፈረሰዉ ግን----ቀጠሉ ሚንስሩ።

                              

«ከስምምነቱ ለመዉጣት የመጀመሪያዎቹ እንዳንሆን ፅኑ አቋም ይዘናል።በስምምነቱ ላይ የተጠቀሰዉ ምጣኔ ሐብታዊ ጥቅማችን ተጠብቆ ኢራን ማግኘት የሚገባትን  ምጣኔ  ፋይዳ እስካገኘች ድረስ ስምምነቱን እናከብራለን።ኢራን እኒያን ጥቅሞች ማግኘቷ ከቆመ ግን ጉዳዩ ሌላ ነዉ የሚሆነዉ።አንዱ ከሌዉ ጋር መከባበርን እና የእኩልነት ስሜትን አንደኛዉ ወገን እያፈረሰ መደራደርን፤ የኢራናዊነት ክብር እና ኩራታችን እንደማይፈቅድልን ማረጋገጥ አፈልጋለሁ።»

የፕሬዝደንት ሐሰን ሩሐኒ መንግሥት የኑክሌር መርሐ ግብሩን ለሟቋረጥ መስማማቱን አክራሪ የሚባሉት የኢራን ፖለቲከኞች እና የኃይማኖት መሪዎች አጥብቀዉ ተቃዉመዉታል።ፕሬዝደንት ትራምፕ ስምምነቱን

ለማፍረስ መዛታቸዉ ለአክራሪዎቹ የኢራን ፖለቲከኞች ወትሮም «ያልነዉ ይሕን» ነበር የሚያሰኝ ነዉ።ታዛቢዎች እንደሚስማማበት ትራምፕ የሚፈልጉትን የኢራን አክራሪ ፖለቲከኞችም ከትራምፕ እኩል ይፈልጉታል።

ሁለቱም እንደሚፈልጉት ዩናይትድ ስቴትስ ከስምምነቱ ከወጣች የኢራን አክራሪ ፖለቲከኞች ከቻሉ ዩናይትድ ስቴትስን ካቃታቸዉ የዩናይትድ ስቴትስን ጥቅሞችና ታማኞች በጦር ኃይል መኮርኮማቸዉ የማይቀር ነዉ።ሠላም የናፈቃት ዓለምም ሌላ ጦርነት ማስተናገድ ግዷ ነዉ። እስኪ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች