ከዐባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ | ባህል | DW | 21.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

ከዐባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ

ዓለም እንደዛሬው ሁሉ በየደጁ ሆስፒታሎች እና ሀኪሞች ሳይኖሯት፤ መድሃኒቶች በየበሽታው ዓይነት ተፈብርከው ሳይቀርቡለት፤ በልሳነ ግዕዝ በሊቃውንቶች በሸንበቆ ብዕር ተጽፈውና ገቢራቸው ተበትኖ የተቀመሙ መድሃኒቶች ትውልዱን ከጨለማው ዘመን ታድገው ወደ ብርኃን ዘመን አብቅተዋል። «ግእዝ ተሐተ ወህላዌ ተበሥረ ማለት ግዕዝ ተመረመረ፤ ሕልዉናዉም ተበሠረ»

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:47
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
16:47 ደቂቃ

«ግዕዝ ተመረመረ፤ ሕልዉናዉም ተበሠረ»

እነዚህ ጥንታዊ ባህላዊ እዉቀቶችን የያዙት የግፅዝ ጽሑፎች ሊተረጎሙ፤ ምርምር ሊደግባቸዉ ይገባል ሲሉ ባለፉት ሳምንታት ዉስጥ ባሕር ዳር ዩንቨርስቲ በተካሄደዉ የዘርፉ ምሁራን ተናግረዋ። ጣናን የተንተራሰችዉ ባሕር ዳር ከተማ ባለፉት ሳምንት የዓለም ፖለቲከኞችን ከማሰባሰቧ በፊት « ግዕዝ ተመረመረ፤ ሕያውነቱም ተበሠረ» ስትል የቅኔ ሊቃዉንትን፤ የከፍተኛ ትምህርት ተመራማሪዎችን፤ የቋንቋ ምሁራንና ጉዳዩ የሚመለካታቸዉን ሁሉ አሰባስባ ለሁለት ቀን ጉባዔን አካሂዳ ነበር።

ሀገር በቀል እውቀትን በመጠበቅና በመሰነድ ከትውልድ ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆን ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሚገልፀዉ በባህርዳር ዩንቨርስቲ «ዐባይ የባህልና ልማት ጥናትና ምርምር ማዕከል» ዕውቀትን፣ ባህልን የማስተላለፍ፣ የማዳበር እንዲሁም አዕምሯዊ ትንታኔ የመስጠት ተግባር እንደሚያከናዉን ሁሉ ተገልፆአል። ማዕከሉ ዘንድሮ መጋቢት 28 እና 29 ለሁለተኛ ጊዜ ያካሄደዉ የዓለም አቀፍ ግዕዝ ዓውደ ጥናት ላይ ከመዲና በርሊን ጀርመን ከሚገኘዉ የቋንቋ ጥናት የተጋበዙ ጀርመናዊ ምሁር በጉባዔዉ የጥናት ፅሑፋቸዉን አቅርበዋል። ዐባይ የባህልና ልማት ጥናትና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉቀን አንዷለም ለተሳታፊዎች ግዕዝ ይላሉ

« ግዕዝ ተመረመረ፤ ሕያውነቱም ተበሠረ» የሚል ነበር መሪ ቃሉ፤ ይህ የተመረጠበት ምክንያት ግዕዝ እኛ ሃገር ላይ እንደ ቋንቋ ብዙ ነገርን እንደሰራ ቢታወቅም ግን እንደተጠበቀዉ ጥናትና ምርምር የተካሄደበት ነገር አልነበረም። ወደ ዩንቨርስቲዎችም አልፎ ለዘመናዊ ትምህርት ተከታታዮች ያገለገለበት ሁኔታ አልነበረም። በዝያዉ በገዳማትና በአድባራት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ስር ነበር ለመንፈሳዊ አገልግሎት ይዉል የነበረዉ። ስለ ግዕዝ ቋንቋ ጀርመን ሃገር ምርምር እንደሚደረገዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ምንም ጥናት አልተካሄደም። አሁን ግን ከገዳም ወጣ ብሎ ወደ ዩንቨርስቲዉ በሰፊዉ እየገባ ነዉ።ቀደም ሲል ግዕዝን ኅብረተሰቡ በመግባብያ ቋንቋነት ይገለገልበት፤ እንደ ቋንቋ ይፅፍበት ይከስበት ይካሰስበት፤ ጥናትና ምርምር ያካሂድበት ሃገር በቀል እዉቀቱን በሰፊዉ ያካሂድበት የነበረ ቋንቋ ነበር። ኅብረተሰቡ ያንን ትቶ ባልታወቀ ምክንያት ለረጅም ዘመናት አማርኛ ቋንቋ ቦታዉን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ የግዕዝ ቋንቋ እስካሁን ድረስ ደብዛዉ ጠፍቶ ነበር ማለት ይቻላል። የዘመኑ ትዉልድ እየተጠቀመበትም አልነበረም። ጥናትና ምርምር በዩንቨርስቲዎች በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተካሄደበትም አልነበረም። ግዕዝ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ብቻ ነዉ፤ ለአገልግሎት ይዉል የነበረዉ፤ አሁን ወደ ዩንቨርስቲ ስላመጣ ነዉ በዩንቨርስቲ ተቋም እንዲከፈት ሁሉ ስለተባለ፤ ለቋንቋ ተማሪዎችም ትምህርቱ እየተሰጠበት ስለሆነ፤ ወደፊት የመጀመርያ ዲግሪ፤ ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት እንዲሰጥ የሚል ቀቅጣጫ ተይዞአል።

ግዕዝ ቋንቋን አዲሱ ትዉልድ የሚማርበት መንገድ እንዲዘረጋ ስለሆነ ፍላጎታችን «ግዕዝ ተመረመረ፤ ሕልዉናዉም ተበሠረ» ስንል ነበር ጉባዔያችንን የጠራነዉ ያካሄድነዉ። በጉባዔዉ ላይ የተጋበዙ ብዙ ተካፋዮችና እድምተኞች ነበሩ። ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ፤ ከደብረ ብርኃን ፤ ከወሎ ዩንቨርስቲ፤ ከወልድያ ዩንቨርስቲ፤ ከጎንደር ዩንቨርስቲ፤ ከደብረ ታቦር ዩንቨርስቲ፤ ከደብረማርቆስ ዩንቨርሲና ከጀርመን በርሊን ከሚገኘዉ ዩንቨርስቲም ተሳታፊዎች ነበሩን። ከበርሊን የመጡት ጀርመናዊዉ ምሁር ፕሮፊሰር ራይነር ፎግት በጉባዔዉ ላይ በሞክሼ ፊደላት ላይ ጥሩ የሆነ የጥናት ወረቀታቸዉን አቅርበዋል። ጀርመናዉያን በግዕዝ ቋንቋ ላይ ብዙ ምርምርና ጥናት እንደሚኢደርጉ የታወቀ ነዉ።»

የዚህ ጉባዔ ተካፋይና የግዕዝ ንባብና ቅኔ አስተማሪ መምህርት እማሆይ አመተማርያም አሰፋ በጉባዔዉ መድረክ ስለ ዋሸራ ቅኔ ምነት ትንታኔ ሰጥተዋል። እማሆይን ቃለ-ምልልስ ከሰጡን በኋላ እድሜአቸዉን ጠይቀናቸዉ ነበር። እማሆይ የመነኮሱት አስራ ስድስተኛ ዓመታቸዉን አገባደዉ ወደ አስራሰባተኛዉ ሊደርሱ ሲሉ እንደመነኮሱ፤ ከመነኮሱ ደግሞ ሃያ ምናምን ዓመት እንደሆናቸዉ በአጠቃላይ ወደ አርባዉ እየተጠጉ መሆኑን አጫዉተዉናል። መምህርት እማሆይ አመተማርያምን ግዕዝ ምንድነዉ ስል ነበር መጀመርያ የጠየቅናቸዉ።

« ግዕዝ ማለት ነፃ አዉጭ ማለት ነዉ። ግዕዝ ነፃ የወጣ ቋንቋ ነዉ። በሌላ በኩል ተጓዘ ብሎ ግዕዝ ጓዘኛ ማለት ይላል። ግዕዝ የኢትዮጵያዉያን ኃብት ነዉ። በተለይ ቅዱስ ያሬድ ቅኔን ቦታ ካስያዘ በኋላ፤ ተገልጾለት በሠማያዊዉ ምስጢር ግዕዝን ለማመስገኛ የተጠቀመበት ቅዱስ ያሬድ ነዉ። እናም የቅዱስ ያሬድ ምስጢር ለኢትዮጵያዉያን እንጂ ከሌሎች ቀዳሚነትን ይይዛል። ከሱ ወዲህ የመጡ ሊቃዉንት ግን በየጊዜዉ እየተነሱ ዜማዉን፤ ዜማ ልኩን አስተካክለዉ፤ ወረቡን ሰምና ወርቁን፤ ልኬታዉን፤ መንገዱን፤ በጣም ለየት ባለ መልኩ በየጊዜዉ የተነሱት ሊቃዉንት እዚህ እንዲደርስ አድርገዉታል። ዛሬም ግዕዝ ለኢትዮጵያዉያን ኩራት ነዉ፤ የማንነት መገለጫም ነዉ። ለኢትዮጵያዉያን የማንነት ኩራት ሞገስ ነዉ፤ ታሪክም ነዉ። ከየት መጣህ ሲባል የታሪካችን ማንነት መመኪያችን ነዉ። ከዚህ ሌላ መድር ላይ ብቻ ተግባብተንበት የምናልፈዉ ቋንቋ ብቻም

አይደለም። ከሰማያዊዉ አባታችን ፈጣርያችን ጋር የሚያገናኘን መስመር፤ ማለት ቋንቋም ነዉ። የግዕዝ ቋንቋን የመላዕክት ቋንቋ ነዉ የሚሉም አሉ። ስለዚህ ግዕዝ ቀዳሚ የሆነ ከእግዚአብሄር ጋር ማገናኘት የሚችል የመላዕክት ቋንቋ ነዉ። አዳምም ወደ ፈጣሪዉ ይገናኝ የነበረዉ በግዕዝ ቋንቋ ነበር። ለቅኔም በር ከፋች ግዕዝ ነዉ። ለኢትዮጵያዉያንም መመክያ ነዉ፤ ግዕዝ በአጠቃላይ ትልቅ ነፃነት ያለዉ ራሱን የቻለ ረዳት የማይፈልግ ቋንቋ ነዉ። »

ከባህርዳር አገረ ስብከት የተጋበዙት ሌላዉ የጉባዔዉ ተሳታፊ ቀኝ ጌታ ኤፍሪም መስፍን በግዕዝ «ተክሌ አቋቋም» ላይ የጥናት ጽሑፋቸዉን አቅርበዋል። የተክሌ አቋቋም ተብሎ የሚጠራዉ መነሻዉ ይላሉ፤

« ተክሌ አቋቋም ቀደም ሲል በ 14ኛዉና በ 15ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ይዘትና ቅርስ የለዉም ነበር። በዝያ ዘመን የጎንደር ንጉስ የነበሩት አፄ እያሱ በዘመናቸዉ ተክሌ አቋቋም ይዘትና ቅርፅ እንዲኖረዉ ለየብቻ አኖርዋቸዉ ነበር። «እዚህ ላይ አቋቋም ስንል ዜማ፤ ለእግዚአብሄር የሚቀርብ ምስጋና ማለታችን ነዉ።» ከዝያም አፄ እያሱ 300 ሊቃዉንትን ሰበሰቡና ሱባኤ አስገቡዋቸዉ። ከዝያ በኋላ አቋቋም የሚባለዉ አንድ ዓይነት ቅርስ እንዲኖረዉ ሆነ። ከዝያም ይህ አቋቋም

በቅብብሎሽ እስከ አለቃ ገብረሃና መምጣቱ ይናገራል። አለቃ ገብረሃና በኖሩበት ዘመን የነበሩት አፄ ቴዮድሮስ ስለነበሩ፤ አለቃ ገብረሃና ቁም ነገረኛ ቢሆኑም በቀልድ ወጋ ወጋ ስለሚያደርጉ አፄ ቴዮድሮስ ቀልዳቸዉን አልወደዱላቸዉም ነበር። አለቃ ገብረሃናን አፄ ቴዮድሮስ ስላልወደዱዋቸዉ ወደ ዉጭ እንዲሄዱ የተለያዩ ግፊት አድርገዉባቸዉ ወደ ጣና ገዳም ጣዳ ደሴቶች ዘጌ ዉስጥ ተክለ ሃይማኖት የሚባል ገዳም ዉስጥ ገብተዉ ነበር ይባላል። አለቃ ገብርሃና ተክለ ሃይማኖት ገዳም ዉስጥ ተሸሽገዉ ሳለ አንድ ባህታዊ የተለየ አቋቋም አስተምረዋቸዉ ነበር። አለቃ ገብርሃና ወደ ሃገራቸዉ ተመልሰዉ በሸንበቆ አቋቋም እጅ ስራዉን አራሳቸዉ ተምረዉ ለልጃቸዉ ለተክሌ ደብቀዉ አስተምረዉት ነበር። ለዚህ ነዉ « የተክሌ አቋቋም የተባለዉ። »

ያልተነካ ያልታየዉ ሃብታችን ግዕዝ ላይ ይገኛል፤ የግዕዝ ጥናት ያስፈልገናል ያሉት ቀኝ ጌታ ኤፍሪም በመቀጠል፤

« ግዕዝ በጣም አስፈላጊ ቋንቋ ነዉ ። የሃገሪቱ ያልተነካ ሃብት ያለዉ ግዕዝ ላይ ነዉ። በየዘመኑ የነበሩትን አሻራዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን እስካሁን ድረስ አስቀምጣለች። አብዛኞች ግዕዝን ከሃይማኖት ጉዳይ ጋር ያያዙታል። ግዕዝ ግን ጨርሶ ከሃይማኖት ጋር አይገናኝም። ልክ እንደ እንጊሊዘኛ እንደ አማርኛ ሁሉ የኢትዮጵያ የሥራ ቋንቋ ነበር። ግዕዝን የተካዉ አማርኛ ቋንቋ መሆኑ ይታወቃል። በጥንት ግዜ በግዕዝ ቋንቋ ብዙ መረጃዎች ተፅፈዋል። የፍልስፍና መጽሐፎች ፤ የመድሐኒት ቅመማ ፤ ማኅበረሰቡ ከጥንት ከሮማዉያን የሚገናኘዉ ሁሉ በግዕዝ ቋንቋ ነበር። እና ግዕዝ ዉስጥ ብዙ ያልተነኩ ሃብቶች እናገኛለን። ኢትዮጵያ ያልተነካ ሃብት እና የራስዋ ቋንቋ ያላት የራስዋ ፊደላት ያላት ናት። ይህን ስንልም ግዕዝን ማለታችን ነዉ። አማርኛ የተወለደዉ አሁን ነዉ። የግዕዝ ቋንቋ ጥናትን በተመለከተ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ተቋማት ልዩ ልዩ መረሃ-ግብሮችን አዉጥተዋል። ለምሳሌ ባሕርዳር ዩንቨርስቲ፤ አክሱም ዩንቨርስቲና ደብረማርቆስ ዩንቨርስቲ በሚቀጥለዉ ዓመት፤ የትምህርት ክፍል ተቀርፆለት ተማሪዎችን በማስተማር ማስመረቅ እንደሚጀመር ተነግሮአል።»

ሌላዉ የጉባዔዉ ተሳታፊ በምስራቅ ጎጃም አገረስብከት የትምህርትና ስልጠና ክፍል ሃላፊ ርዕሰ ማዕምራን ዮሃንስ ታምሩ ስላቀረቡት የአጫብር ዜማ ምንነት ተንትነዉልናል። ለመሰናዶ የተያዘዉ ሰዓት ባለማብቃቱ ልናቋርጥ ተገደድን እንጂ የግዕዝ ቋንቋ ምሁራኑ ስለተለያዩ አቋቋሞች፤ ቅኔና በግዕዝ ስለተፃፉትመፃሕፍት፤ ስለያዙት ምስጢራዊ ነገሮች በሰፊዉ ባጫወቱን ነበር። በሌላ መሠናዶ ሌሎችን የዝግጅቱን ተሳታፊዎች ይዘን ለመቅረብ እንሞክራለን። በባህርዳር ዩንቨርስቲ የዐባይ የባህልና ልማት ጥናትና ምርምር ማዕከል ጉባዔ ተሳታፊዎች ለሰጡን ቃለ ምልልስ እናመሰግናለን። ሙሉዉን ዝግጅት የድምፅ ማዕቀፉን በመከታተል እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic