ከኢትዮጵያ የራቀው ሙዚቀኛ-ደርብ ዘነበ | ባህል | DW | 06.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ከኢትዮጵያ የራቀው ሙዚቀኛ-ደርብ ዘነበ

"ባንቺው መጀን" በተባለው የወሎ ሙዚቃ እና ደግሞ በተጫወተው የአሰፋ አባተ "የማትበላ ወፍ" ተለይቶ የሚታወቀው ደርብ ዘነበ ከጠፋ ሰነባበተ። እሱ ራሱ "ርቄ ስለ ሔድኩኝ ሰዎች በቃ የተውኩት መሰላቸው" ሲል ይናገራል። አሁን ግን በኢትዮጵያ መድረኮች የመጫወት ከአገሩ ልጆች ጋር በትብብር የመሥራትም ውጥን አለው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:20

"ከኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ጋር መሥራት እፈልጋለሁ" ደርብ ዘነበ

"ባንቺው መጀን" በተባለው የወሎ ሙዚቃ እና ደግሞ በተጫወተው የአሰፋ አባተ "የማትበላ ወፍ" ተለይቶ የሚታወቀው ደርብ ዘነበ ከጠፋ ሰነባበተ። እሱ ራሱ "ርቄ ስለ ሔድኩኝ ሰዎች በቃ የተውኩት መሰላቸው" ሲል ይናገራል። አሁን ግን በኢትዮጵያ መድረኮች የመጫወት ከአገሩ ልጆች ጋር በትብብር የመሥራትም ውጥን አለው። ድምፃዊው ስድስት የራሱን አዳዲስ ሥራዎች እና እንደገና የተጫወታቸው የድሮ ሙዚቃዎች የተካተቱበትን አዲስ አልበም ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ብቅ ሊል ዝግጅቱን አጠናቋል።

"ቅንብሩ ያምራል፤ ድምፁ ያምራል፤ ድምፁ ለብዙ ዓመታት የሚቆይ ነው" ሲል የሚናገርለት አዲሱ አልበም በዓለም የሙዚቃ ወዳጆች ዘንድ ተቀባይነት እንደሚያገኝ ደርብ በልበ-ሙሉነት ይናገራል።

በአካልም በመንፈስም ለራቀው የአውስትራሊያ አድማጭ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በማስተዋወቁ ረገድ ስኬታ ከሆኑ ድምፃውያን መካከል ደርብ ዘነበ ቀዳሚው ነው።

ደርብ በሚኖርበት አውስትራሊያ Drums and Lions እና Dereb The Ambassador የተሰኙ ሁለት አልበሞች ሠርቷል።

"ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ መረጃ የላቸውም። የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ወይም ባሕል አያውቁትም" ለሚለው ደርብ በአውስራሊያ ገበያ Drums And Lions የመጀመሪያ ሥራው ነው። ሥራው ተወዳጅ ከመሆን ባሻገር በጃፓን፣ አውሮጳ እና አሜሪካ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ መድረኮች እንዲጫወት እድል ሰጥቶታል።

በአልበሙ የተካተቱት "የኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቃማ ዘመናት" ተብለው በሚቆጠሩት 1960ዎቹ እና 70ዎቹ የተሠሩ ናቸው። አልበሙ ግን በኢትዮጵያ ገበያ አልተሸጠም። የጥላሁን ገሠሠ፣ ማሕሙድ አሕመድ፣ አለማየሁ እሸቴ እና ሙላቱ አስታጥቄ እና የደርብ የራሱ ባሕላዊ ሥራዎች ተካተውበታል። ደርብ ዘነበ እንደገና የሠራው የአሰፋ አባተ "የማትበላ ወፍ" የተባለ ሙዚቃ Drums And Lions በተሰኘ አልበሙ ውስጥ የተካተተ ነው።

ደርብ አባቱ አኮርዲዎን ተጫዋች አጎቶቹም ሙዚቀኞች ናቸው። በልጅነቱ "ያዳመጠውን ሁሉ ከልብ ያስፈነደቀ፤ በመሰንቆ አገራረፉ ማንንም ያስደነቀ ፤ በግጥም አጣጣሉ ሴት ወንዱን ያሳቀ"ተብሎ ስለተሞገሰው አሰፋ አባተ ብዙ ሰምቷል። ሰምቶም ወዶታል፤ አድንቆታል። "በልጅነቴ ጀምሮ ስለአሰፋ አባተ ሰዎች ይነግሩኝ ነበር። ከሙዚቃውም ከሰውዬውም ፍቅር ነበረኝ" የሚለው ደርብ "አሰፋ አባተን እንዴት አድርጌ በሙዚቃ ላምጣው?" የሚል ሐሳብ እንደነበረው ይናገራል። ደርብ እንዳደነቀው አሰፋ አባተ ሁሉ መሰንቆ ይጫወታል። የወደደውን የማትበላ ወፍ የተሰኘ ሙዚቃ መልሶ ሲዘፍን ግን አላማው መዝፈን ብቻ አልነበረም። "ማሲንቆ በእኔ ትውልድ እንዲመለስ ፈልጌ ነበር። ማሲንቆን ማስተዋወቅ እፈልግ ነበር" ይላል ደርብ።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ ከታች የሚገኘውን የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ 

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic