1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከአገራዊው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማግስት አልረጋጋ ያለው ገበያ

ሰኞ፣ ነሐሴ 20 2016

የኢትዮጵያ መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ ከመንግስታዊ ተቋም እስከ ቸርቻሪ ነጋዴዎች የዋጋ ማሻሻያ ጭማሪ እያደረጉ ነው። እንዲህ አይነት የዋጋ ለውጥ የሚጠበቅ እንደሆነ የሚናገሩ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች የምርት እና አገልግሎቶች ዋጋዎችን ከመቆጣጠር ይልቅ አቅርቦትና ፍላጎቶችን ማጣጣም ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚሻል ይመክራሉ።

https://p.dw.com/p/4jwJk
Äthiopien Alltag l Dire Daw Market
ምስል Mesay Teklz/DW

ከአገራዊው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማግስት አልረጋጋ ያለው ገበያ

አገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃው የተወሰደው ሰፊ የንግድ ሚዛን ጉድለት ማለትም የወጪና የገቢ ንግድ አለመመጣጠን ጎልቶ ሰፊ ክፍተት በሚያሳይበት ወቅት ላይ መሆኑ የዋጋ አለመረጋጋቱ አይቀረ ለመሆኑ አብይ ምክንያት ነው የሚሉት የኢኮኖሚው ባለሙያና ተመራማሪው ዶ/ር ደግዬ ጎሹ፤ አሁን እየተስተዋለ ያለው በየዘርፉ የሚስተዋሉ የገቢያ ዋጋ አለመረጋጋቶች አስቀድሞም የተገመቱ ናቸው ብለዋል፡፡

“ሪፎርሙን ተከትሎ ዋጋ ጭማሪ እንደሚኖር ግልጽ ነው፡፡ ከፍተኛው የአጭር ጊዜው ፈተናውም የማክሮ ኢኮኖሚው አለመረጋጋት ነው” ይላሉ፡፡

በአዲስ አበባ ከማሻሻያው ወዲህ በምርቶች ወጋ ጭማሪ የተማረሩት ሸማቾች የገቢያው አለመረጋጋት ምርቶችን ሸምቶ መጠቀምንም ፈታን ማድረጉን ያስረዳሉ፡፡ ከዘይት ጀምሮ በተለይም ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ጭማሪ ለማድረግ ለነጋደው ጊዜም አልፈጀበትም ሲሉም የዋጋ ጭማሪውን ያማርራሉ፡፡

የገበያ ዋጋ ለማረጋጋት መንግስት ምን እያደረገ ይሆን ?

ከዚህ በፊት አስተያየታቸው ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና የኮሚዩኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ አብዱልቃድር ኢብራሂም፤ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የተፈጠረውን የዋጋ ጭማሪ በኢ-ሚክንያታዊነት ገልጸው የዋጋ ጭማሪውን ባደረጉት ላይ በሚከናወነው የሰላ ገቢያ ቁጥጥር እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለው ነበር፡፡

የምግብ ማብሰያ ዘይት
መንግሥት ምርቶች ደብቀዋል፤ ሕገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል የሚላቸው ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ ይገልጻል። ምስል Mesay Teklz/DW

በዚህም እንደ አገር አቀፍ 40 ሺኅ ገደማ የንግድ ድርጅቶች እና ሱቆች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አብራርተዋል፡፡ “ከጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ጀምሮ ሱቆችን እስከ ማሸግ ብሎም ከበድ ያለ ጥፋቶችን ያጠፉት ላይ እስከ እስራት እርምጃ ተወስዷል” ነው ያሉት፡፡

የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ መመራቱ እና የምሥራቅ ኢትዮጵያ ገበያ

የኢኮኖሚ ባለሙያና ተመራማሪው ዶ/ር ደግዬ ጎሹ ግን ይህ መፍትሄ ሆኖ በዘላቂነት ማገልገል ስለመቻሉ ይጠራጠራሉ፡፡ “ህጋዊ የዋጋ ጭማሪ ማለት ምን ማለት ነው፤ ከምን በላይ ነው ህገወጥ የዋጋ ጭማሪ የሚባለው፤ ዋናው ነገር ምንድነው አቅርቦቱ ላይ በደንብ መስራት ነው፡፡ የበዛ ቁጥጥሩ መፍትሄ አይደለም” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

መንግስት በነጋዴዎች ላይ የሰላ ቁጥትር እያደረገ መሆኑ በሚገለጽበት ባሁን ወቅት በመንግስታዊ ድርጅቶች በተለያዩ አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑ ይገለጻል፡፡ የፓስፖርት አገልግሎት፣ የአየር ትራንስፖርት፣ ኤሌክትሪክና ሌሎችም አገልግሎቶች ከዚህ አንጻር ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን የተከተለው የገበያ አለመረጋጋት

የኢኮኖሚው ባለሙያ ዶ/ር ደግዬ ኢኮኖሚው ላይ የሚደረጉ የዋጋ ለውጦች የዉጪ ሚንዛሪው ነጻ ገቢያ ላይ በተመሰረተ አኳሃን ሊሆን የሚገባው ነው ባይ ናቸው፡፡ “የመንግስት ተቋማትም ሆኑ የግል የገቢው ተዋናዮች በውጪ ምንዛሪ ሪፎርሙ መሰረት ነው ገቢያውን የሚተምኑት፡፡ ዋጋው ደግሞ በመንግስት ሳይሆን በራሱ በገቢያው መመራትና መወሰን ያለበት ነው” ብለዋልም። 

ሥዩም ጌቱ

እሸቴ በቀለ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ