ከአሸባሪው ቦኮሐራም ጀርባ | አፍሪቃ | DW | 21.04.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ከአሸባሪው ቦኮሐራም ጀርባ

ቦኮ ሐራም የተሰኘው እስላማዊ አክራሪ ቡድን ናይጀሪያ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ከባድ ጥቃቶችን ሲሰነዝር ቆይቷል። የናይጀሪያ ምርጫ በተቃረበበት በአሁኑ ወቅት ሰሞኑን ከፍተኛ እልቂት ያስከተለ የቦንብ ጥቃትም ሰንዝሯል። ለመሆኑ ቦኮሐራም ማን ነው? ከሽብርተኛ ቡድኑ ጀርባ የሰሜንና የደቡብ ናይጀሪያ ባላሥልጣናት እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

ቦኮ ሐራም፤ የናይጄሪያ እስላማዊ አክራሪ የሽብርተኛ ቡድን። ቦኮ ሐራም የሚለው የቡድኑ ስያሜ «የምዕራባውያን አስተምኅሮት ሀጢአት ነው» የሚል ትርጓሜን ይይዛል። ቡድኑ የምዕራባውያን ሲል በፈረጃቸው ተቋማት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር በስፋት መንቀሳቀስ የጀመረው እጎአ በ2009 ዓም ነው። ከእዚያን ጊዜ አንስቶ ቦኮ ሐራም ሠላማዊውን ሕዝብ በተደጋጋሚ እየፈጀ ነው። የናይጀጄሪያ መንግሥትም በአፀፋው ቦኮ ሐራምን ለማጥፋት በሚል ወደ ሰሜን እየዘመተ በርካቶችን መግደሉ ተዘግቧል። እስካሁን በግጭቱ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ጭዳ ሆነዋል፤ ከግማሽ ሚሊዮን የማያንስ ሕዝብ ቤት ንብረቱን ጣጥሎ ከቀዬው ተፈናቅሏል። ተንታኞች ሐይማኖታዊ ይዘት ብቻ የተላበሰ ከሚመስለው የናይጀሪያ ግጭት ባሻገር በሰሜኑና በደቡቡ መካከል የስልጣን ሽኩቻና የሀብት ክፍፍል የጎላ ሚና እናዳላቸው ይናገራሉ። «ቦኮሐራም የናይጀሪያ ስጋት»

ቦኮ ሐራም የተሰኘው እስልምና አክራሪ የሽብር ቡድን በዋናነት የሚንቀሳቀሰው በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ ውስጥ ነው። ይህ ቡድን የሽብር ጥቃቱን መጠነ-ሰፊ በማድረግ ጠንካራ ሆኖ የወጣው እጎአ በ2009 ዓም እንደሆነ ይነገርለታል። በወቅቱ በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ ድህነትና የአስተዳደር በደል ያስቆጣቸው ወጣቶች በቀሰቀሱት ነውጥ ቦኮ ሐራም ገኖ ለመውጣት ችሏል። ከእዚያን ጊዜ አንስቶ በርካታ የፈንጂ ጥቃቶችን በናይጄሪያ የተለያዩ ግዛቶች ሲፈፅም ቆይቷል። በዶቸ ቬለ ሐውሳ ክፍል ናይጀሪያዊቷ ጋዜጠኛ ፒናዶ አብዱ ከቦኮ ሐራም ጀርባ የእራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት ለማስፈፀም የሚፈልጉ አካላት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ገልጣለች።

የሽብር ጥቃት በናይጀሪያ መዲና አቡጃ፤ ነፍስ አድን ሠራተኞች

የሽብር ጥቃት በናይጀሪያ መዲና አቡጃ፤ ነፍስ አድን ሠራተኞች

«በእርግጥም ቦኮ ሐራም አለ። እየተንቀሳቀሰም እንደሆነ እናውቃለን። ሆኖም ማን ነው ቦኮ ሐራም? ማንስ ነው በእራስ ወዳድነት እየተጠቀመበት ያለው? ያ ነው ግራ አጋቢው ጥያቄ።»

የቦኮ ሐራም ዋነኛ የትግል ዓለማ ቡድኑ ትክክል ነው ብሎ በሚያምነው እጅግ ጥብቅ የሆነ የእስልምና መርኅ ናይጀሪያን ማስተዳደር ነው። ይህን ዓላማውን ከግብ ለማድረስም የመንግሥት የሚላቸውን፤ የጦር ኃይሉን፣ የፖሊስ መዋቅሩንና ትምህርት ቤቶችን የጥቃቱ ዒላማ አድርጎ ቆይቷል። በርካታ ህፃናትን የትምህርት ቤት መኝታ ክፍላቸው ድረስ በመዝለቅ ማረዱና ሴት ተማሪዎችን ከሚማሩበት ክፍል አግቶ መሰወሩም ተዘግቧል። መንግሥት ከታገቱት ተማሪዎች ኋላ ላይ የተወሰኑትን ነፃ ማውጣቱን ጠቅሶ ይፋ ያደረገው መረጃ የተሳሳተ ነው በሚል ትችትም አስከትሎበታል። የናይጄሪያ ጦር የቀድሞ ጀነራል የደኅንነት ጉዳይ ተንታኝ ያሃያ ሺንኩ ቦኮ ሐራም ከዕለት ዕለት የጥቃት ስልቱን እየቀያየረ እንደሆነ ይናገራሉ።

«የጥቃት ስልቱ መልኩን ቀይሯል። ጥቃት የሚሰነዘርባቸው አካባቢዎችም ጨምረዋል። ለአብነት ያህል፤ በሰሜን ምሥራቅ ብቻ ተወስኖ የነበረው ጥቃት አሁን ወደ ሰሜን ምዕራብና ሰሜናዊ አማካኝ የናይጀሪያ አካባቢዎችም ተዛምቷል።»

ቦኮሐራም ዋነኛ መቀመጫው ከሆነው የሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ ግዛት የጥቃት አድማሱን በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ማስፋፋት ችሏል። በቅርቡ እንኳን መዲናዋ አቡጃ አቅራቢያ ባደረሰው የፈንጂ ጥቃት ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል። በቦኮ ሐራም በቅርቡ እንደተከሰተየተጠቀሰው የፈንጂ ጥቃት ዓላማ በቀጣዩ ዓመት ሊካሄድ የታቀደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከወዲሁ ለማወክ ታስቦ የተፈፀመ እንደሆነ ያሃያ ሺንኩ ይገልጣሉ።

ናይጄሪያዊት ሴት በሽብር ጥቃቱ አዘኗን ስትገልጥ

ናይጄሪያዊት ሴት በሽብር ጥቃቱ አዘኗን ስትገልጥ

«ጥቃቱ በቅርቡ ሊካሄድ ከታቀደው ምርጫ ጋ የተያያዘ መሆኑን ነጥሎ መመልከት አያስፈልግም። እንዲህ አይነት ጥቃት በተሰነዘረባቸው አካባቢዎች ምርጫ ቦርድ ምርጫ ለማካሄድ ከባድ ነው የሚሆንበት። የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበሩ በእነዛ አካባቢዎች ምርጫ ለማካሄድ ቢወስን እንኳን፤ አንዳንድ የምርጫ ታዛቢዎች ፈቃደኛ እንደማይሆኑ፣ ፍንዳታው ወደ ተከናወነባቸው ቦታዎች በመሄድም እራሳቸውን መስዋዕት እንደማያደርጉ ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ።»

በአንዳንድ የናይጀሪያ ሰሜናዊ የገጠር መንደሮች ውስጥም ይኸው የሽብር ቡድን ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶችን ሰንዝሯል። በርካታ የክርስትና እንዲሁም የእስልምና እምነት ተከታዮች ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቱ ዒላማ ሆነዋል። የኮንራድ አደንአወር ተቋም የአቡጃ ቅርንጫፍ ኃላፊ ሂልደጋርድ ቤሬንድት ኪጎዚ

«የትኛውም አይነት የሽብርተኛ ቡድን ይሁን፤ ምንም አይነት ርዕዮተ-ዓለም ያራምድ በእንዲህ መሰሉ ጥቃት እራሱን እጅግ ሲበዛ እንዳይታመን ነው ያደረገው።»

ቦኮ ሐራም የእስልምና እምነትን ሽፋን አድርጎ የሚንቀሳቀስ ሽብርተኛ ቡድን ቢሆንም፤ የናይጄሪያ ግጭት ከሐማኖታዊ ይዘቱ ይልቅ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ እንድምታው የጎላ እንደሆነ ጋዜጠኛ ፒናዶ አብዱ ጠቅሳለች። እጅግ ከፍተኛ በጀት እንዳለው የሚነገርለት የናይጄሪያ ጦር ቦኮ ሐራም የሚፈጥረውን ችግር ማስወገድ እየቻለ ያን አለማድረጉ በናይጄሪያውያን ዘንድ እጅግ አስተዛዛቢ ነገር እንደተከሰተም ታመለክታለች።

«ጦሩ ይህን ችግር ለመፍታት የሚያስችለው የገንዘብ አቅም አለው። ሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖችን ጨምሮ ሌሎች መሣሪያዎችን የመግዛት አቅም አለው፤ ሆኖም ገንዘቡ ጥቅም ላይ ሲውል አይታይም።»

ለመጨረሻ ጊዜ በ2011 መዲናዋ አቡጃ ድረስ ሰተት ማለት ብቻ አይደለም የናይጄሪያ የፖሊስ ማዘዣ ክፍልና በዋና ከተማዋ የሚገኘው የተመድ ላይ ፈንጂ አጥምዶ ጥቃት መሰንዘር እንደተሳካለት የተነገረለት ቦኮ ሐራም ለዓመታት ከመዲናዋ ርቆ ነበር።

ሰሞኑን ግን ወደ መዲናዋ ዘልቆ የሕዝብ መጨናነቅ በሚታይበት ስፍራ ከፍተኛ የፈንጂ ጥቃት ሲያደርስ የሚያግደው ኃይል አልተገኘም ተብሏል። አንዳንዶች ከጥቃቱ ጀርባ የባለሥልጣናት እጅ አለበት ብለው እንደሚያምኑ ፒና አብዶ ገልጣለች።

የናይጄሪያ ጦር ዳማቱሩ ውስጥ ቦኮ ሐራም ላይ በዘመተበት ወቅት

የናይጄሪያ ጦር ዳማቱሩ ውስጥ ቦኮ ሐራም ላይ በዘመተበት ወቅት

ሰዉ ለእዚያ እንደምክንያት የሚያቀርበውም የናይጄሪያ ምርጫ እየተቃረበ መሆኑን ነው ስትልም ጠቅሳለች። የፈንጂ ጥቃቱ በሀገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተነግሮ ባለበት የተከሰተ መሆኑ ግራ እንዳጋባቸው አህመድ ዛናህ የተባሉ የአቡጃ ነዋሪ ለዶቸቬለ ተናግረዋል።

«እኔ እስከአሁን ምንም ልዩነት አላየሁበትም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተጣለም አልተጣለ ለእኔ ያው ነው። ምንም ያመጣው ፋይዳ የለማ። በእውነቱ ግራ ነው የገባኝ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተነገረው እኮ ሕዝቡን ከአደጋ ለመታደግ ነው። በተቃራኒው ግን ሁኔታው ከቀን ወደ ቀን እየከፋ ነው። ስለእዚህ ከአሁን በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘሙን እቃወማለሁ።»

የናይጄሪያ መንግሥት ቀደም ሲል በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስነግሮ ቦኮ ሐራም ላይ ዘመቻ መጀመሩ ይታወሳል። በወቅቱ ጦሩ ሰሜን ናይጄሪያ ውስጥ ከፍቶት በነበረው ዘመቻ ወደ 500 የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸውም ተዘግቧል። ግድያው አሁንም ድረስ እንዳወዛገበ ነው።

መንግሥት ለግድያው እጁ አለበት ሲል ጣቱን ቦኮ ሐራም ላይ ቀስሯል። ቦኮ ሐራም በጠራራ ጸሐይ ማይዱጉሪ ውስጥ የሚገኘውን የጊዋ ካምፕ ሰብሮ በመግባት ግድያ ፈጽሟልም ብሏል። አንዳንድ በቦታው የነበሩ የማይዱጉሪ አካባቢ የአይን እማኞች ግን ጦሩ ዘመቻውን ሽፋን በማድረግ እስር ላይ የነበሩ ወጣቶችን ለመፍጀት ተጠቅሞበታል ሲሉ መመስከራቸውን ዘ ኢኮኖሚስት ዘግቧል።

ጋዜጠኛ ፒና የክርስትና እምነት ተከታዮች በአብላጫው በሚገኙበት የናይጄሪያ ደቡቡ ክፍልና አብዛኛው ሙስሊም በሚኖርበት የሰሜኑ ክፍል መካከል ሆን ተብሎ ልዩነት ለመፍጠር ጥረት እንደሚደረግም ትገልጣለች። አያይዛም ቦኮ ሐራም ፈፅሞ እንዲጠፋ የማይፈልጉ አካላት ናይጄሪያ ውስጥ በብዛት አሉ ብላለች። የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ቦኮ ሐራም በመንግሥታችን ውስጥ ጭምር አለ ሲሉ በቅርቡ መግለፃቸውን ጠቅሳለች።

ናይጄሪያውያን ስደተኞች በጎረቤት ሰሜን ካሜሩን ሜናዎ መጠለያ ውስጥ

ናይጄሪያውያን ስደተኞች በጎረቤት ሰሜን ካሜሩን ሜናዎ መጠለያ ውስጥ

የነፍስ ወከፍ መሳሪያ አንግቦ ለግዳጅ ወደ ሰሜን ናይጄሪያ የሚላከው የጦር ሠራዊት እጅግ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች የታጠቀውን የቦኮ ሐራም ቡድን ለመደምሰስ ይከብደዋል ስትልም ከጀርባ የሚሰራ አሻጥር መኖሩን ጠቁማለች።

እንደ ጋዜጠኛ ፒና ገለፃ አንድ የጦር ሄሊኮፕተር ለቦኮ ሐራም ሽብርተኛ ቡድን በርካታ ጥይቶችን ማቀበሉ በናይጄሪያ ምክር ቤት መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ሆኖም ስለቦኮ ሐራም ማንነትለማብራራትና ከጀርባው ማን እንደሚገፋው ለመግለጥ ማንም ደፍሮ አይወጣም ብላለች። ለእዚያ ደግሞ ከእዚህ ቀደም የተፈፀሙ ክስተቶች ሰዉን ፍርሀት ውስጥ ሳይከተው አልቀረም።

«የቀድሞው የመከላከያ ሚንስትርን ብትወስድ፤ ቦኮ ሐራምን በሚገባ ጠንቅቀው እንደሚያውቁ፣ አንዳንድ ነገሮችን በድፍረት ነበር መናገር የጀመሩት። እናም ሚሥጥራዊ በሆነ መልኩ ሲጓዙበት የነበረው ሄሊኮፕተር ተከስክሶ ሞቱ። ልክ እንደእዛው ሁሉ ስለ ቦኮ ሐራም እናውቃለን ብለው ብቅ ያሉ ሰዎች በአጠቃላይ ሚሥጥራዊ በሆነ መንገድ ሞተዋል።»

170 ሚሊዮን ነዋሪ ባላት የምዕራብ አፍሪቃዊቷ ናይጄሪያ ቦኮ ሐራም ዛሬም ከሰሜን ደቡብ እየተንቀሳቀሰ ጥቃት ሲያደርስ የሚያስቆመው አልተገኘም። የሀገሪቱ መንግሥት ግን ቦኮ ሐራም ይንቀሳቀስባቸዋል ባላቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የዛሬ ዓመት ግድም የጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሁንም እንዳፀና ነው። ቦኮ ሐራም የናይጄሪያ ስጋት ነው እያለም መንግሥት ወደ ምርጫው እየገሰገሰ ነው። በእርግጥ ቦኮ ሐራም ከምርጫው በፊት አለያም በድኅረ-ምርጫው ከናዬጄሪያ ይወገድ ይሆን? ወይንስ የሰሜን ደቡቡ የፖለቲካ ትኩሳት ግለት በጨመረ ቁጥር የቦኮ ሐራም ጥቃትም በእዛው መጠን ይጨምር ይሆን?

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic