ከብት ዘረፋና ግጭት በደቡን ሱዳን | አፍሪቃ | DW | 15.03.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ከብት ዘረፋና ግጭት በደቡን ሱዳን

ባለፈዉ ሳምንት ማለቂያ በደቡብ ሱዳኗ ጆንግሌ ግዛት በከብቶች ዘረፋ ምክንያት የተጫረ ግጭት ከሁለት መቶ በላይ ሰዎችን ህይወት ሲያጠፋ፤ ከመቶ የሚበልጡ ቆስለዋል። በግጭቱ ምክንያት የተሰዳጆች ቁጥር መበርከቱን ግብረ ሠናይ ድርጅቶች አመልክተዋል።

ከኢትዮጵያ በሚዋሰነዉ አካባቢ በሙርሌና ሉዎ ኙዌር ጎሳዎች መካከል የተጋጋለዉ ግጭት ያሳሰበዉ የጁባ አስተዳደር፤ የታጣቂዎችን መሳሪያ ለመሰብሰብ ተዘጋጅቶ እንደነበር ተዘግቧል። ትጥቅ የማስፈታቱ ርምጃ ግን እንደታሰበዉ በቀላሉ መከናወኑ ማነጋገሩ አልቀረም። 

ከብቶችን የመዘራረፉ ሙከራ እና የከረመ ቁርሾ የጎሪጥ የሚያስተያያቸዉ የሙርሌ እና የሉዎ ኙዌር ጎሳዎችን ባለፈዉ ሳምንት ዓርብም ዳግም ህይወት ላሳጣና ደም ላፋሰሰ ግጭት ዳርጓቸዋል። ከአካባቢዉ የሚወጡት መረጃዎች እንደምንጮቹ በመለያየታቸዉ ምክንያት የሟቾችና የተጎጂዎች ቁጥር በትክክል እስካሁን አልታወቀም። አኮቦ ዉስጥ የሚገኝ ግብረሰናይ ድርጅት ዓለም ዓቀፍ የህክምና ጓድበጥይት የቆሰሉና ስብራት የደረሰባቸዉ  63 ሰዎችን ማከሙን ገልጿል። ከዚህም ሌላ የጆንግሌ ግዛት አስተዳዳሪ ኩዎል ማንያንግ ለፈረንይ የዜና ወኪል  ወደሶስት መቶ የሚሆኑ ሴቶችና ህፃናት ተጠልፈዉ መወሰዳቸዉን አመልክተዋል።

ዓርብና ቅዳሜ በተካሄደዉ የከብት ዘረፋም አንድ መቶ ሺህ ላሞች ተሰርቀዋል። ባለፈዉ ጥር ወር ስምንት ሺህ የሚሆኑ የሉዎ ኑዌር ጠንካራ ወጣቶች ከጥቂት የዲንካ ጎሳ አባላት ጋ በመሆን ወደፒቦር ቀበሌ በመዝለቅ የሙርሌ ጎሳ መኖሪያ መንደሮችን በእሳት በማጋየት ኗሪዎቹ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። የተመድ በወቅቱ የሶስት ሺ ሰዎች ህይወት ሳይጠፋ እንዳልቀረ ነዉ ያመለከተዉ። በተጠቀሰዉ አካባቢ በጎሳና የከብት ዘረፋ ሰበብ የሚቀጣጠለዉን ግጭት የሚያባብሰዉ የጦር መሳሪያ በአካባቢዉ እንደልብ መዘራቱ እንደሆነ ነዉ የተገለጸዉ። ጉዳዩ ያሳሰበዉ የደቡብ ሱዳን መንግስት ለችግሩ መፍትሄ ይሆናል በሚል ትጥቅ ለማስፈታት መዘጋጀቱ ተሰምቷል። የቆዳ ስፋቱ ባንግላዴሽን ያህላል ያሏት የጆንግሌ ግዛት ደቡብ ሱዳን ዉስጥ ዉጥረት ከሰፈነባቸዉ ግዛቶች አንዷ መሆኗን ያመለከቱት  በቦን ዓለም ዓቀፍ የዉይይት ማዕከል ተመራማሪ ማሪዩስ ካህል ትጥቅ የማስፈታቱ ሂደት ቀላል እንደማይሆን ነዉ የሚገልጹት፤

«ጆንግሌ ግዛት መሠረተ ልማቱ እጅግ የተዳከመ ከመሆኑ ሌላ በጦር መሳሪያ ከተጥለቀለቁት የደቡብ ሱዳን ግዛቶች አንዱ ነዉ። በዚህ ግዛት የሚገኙ ሶስቱን ዋነኛ ጎሳዎች ትጥቅ ለማስፈታት ቅስቀሳ እንዲያደርጉ መንግስት ወደ15ሺህ የሚሆኑ ወታደሮቹን ወደስፍራዉ ልኳል። እንግዲህ በሲቪሉ ህዝብ ዘንድ እንዳለ የሚታመነዉን ወደ30ሺ የተገመተ ጠብመንጃ መሰብሰብ ምን ያህል ፈታኝ እንደሚሆን ማሰብ ነዉ። ይህን ማከናወኑ ቀላል አይሆንም።»

የጦር መሳሪያዉን ከተጠቀሰዉ አካባቢ ጎሳዎች የመሰብሰቡ ተግባር በራሱ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት ማሪዩር ካህል ቢገልፁም ትጥቅ ማስፈታቱ በራሱ መልሶ ያንን ጎሳ ለጥቃት መዳረግ አይሆንም ወይ የሚሉ ወገኖች አልጠፉም። ካህል በበኩላቸዉ ይህን ይላሉ፤

«የመንግስት ትጥቅ የማስፈታት ርምጃ ሶስቱንም ጎሳዎች ያካትታል። ከሁሉም መሳሪዎቹ ሲሰበሰብ አንዱ ቡድን ተለይቶ ባለፈዉ ጊዜ እንዳጋጠመዉ ዓይነት ለጥቃት አይጋለጥም። ቀደም ብዬ እንደገለፅኩትም ይህ እንደታሰበዉ ቀላል አይሆንም። ለመጠቆም እንደሞከርኩት መሠረተልማቱ በጣም ደካማ ነዉ፤ የግዛቱ ስፋት ራሱ በጣም ትልቅ ነዉ። መንግስት ሶስቱንም ቡድኖች ነዉ ትጥቅ ማስፈታት የሚፈልገዉ፤ ዋናዉ ነገር የህዝቡ ግንዛቤና የመለካከት ነዉ። አንዳንዶች ግን ትጥቅ ማስፈታቱ ሚዛናዊ አይደለም ጎሳን ያማከለና ለግጭት የሚዳርግነዉ የሚል ስሜት አላቸዉ። እኔ እንደማዉቀዉ ግን ይህ እንዳይሆን ማለትም አንዱን በማዳከም ሌላዉ ቡድን እንዳይጠናከር ብዙ ጥረት ተደርጓል።»

እንዲያም ሆኖ እሳቸዉም ትጥቅ በማስፈታቱ ዘመቻ ሊከሰት ይችላል በሚል የሚሰጉበት ችግር አለ።

«ዋናዉ ችግር ይሆናል ብዬ የማስበዉ ዘመቻዉን ለማከናወን የሚያስፈልገዉ መሠረታዊ ነገር ነዉ። እንዲያም ሆኖ ቆየት ብለን እንዴት እንደሚከናወን ማየት ይኖርብናል። አሁን መንግስት ህዝቡን በመቀስቀስና መረጃ በማዳረስ ስራ ተጠምዷል። መሳሪያዉን በፈቃዳቸዉ እንዲሰጡ፤ ሰዎችንም እንዲያግባቡ ነዉ ጥረቱ። ግን ምን ያህል ይሄ ሲቪሉን ኅብረተሰብ ሊያግባባዉ እንደሚችል ለእኔ ግልፅ አይደለም። ዋናዉ ፈተናም የሚመስለኝ ህዝቡን የማሳመኑ ተግባር ነዉ።»

ባለፈዉ ታህሳስና ጥር ወር በተጠቀሰዉ አካባቢ በጎሳዎች መካከል የተነሳዉ ግጭት ወደ120 ሺ የሚገመቱ ሰዎችን ኑሮ ማናጋቱን የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ጽህፈት ቤት አመልክቷል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ